አሳዬ ደርቤ
እንደ ደረጀ ሃብተ-ወልድ ያሉ ደካማ ካድሬዎች ሆድ እንጂ ኅሊና ያልፈጠረባቸው በመሆኑ ‹‹አትንኩኝ›› የሚለውን የአማራ ሕዝብ ቁጣ መንግሥትን ከመገርሰስና ህውሓትን ከመመለስ ፍላጎት ጋር ሊያገናኙት ሲፍገመገሙ ‹‹በዚህ ልክ መዝቀጥ የሚቻለው እንዴት ነው›› ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ፋኖ የተደራጀው ‹‹የትሕነግ ወረራ እና ጥቃት መደገም የለበትም›› በሚል አቋም መሆኑ እየታወቀ የሚታፈኑትን የፋኖ መሪዎችና የጦር አመራሮች የትሕነግ አጋሮች ሊያደርጓቸው ሲሞክሩ “የጅል ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ” የሚለውን አባባል አስታውሳለሁ።
በህውሓት ሕልውና ላይ ዙፋኑን ያደላደለ መንግሥት ተሸክመው ሳለ የሕልውና ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ሦስት ዓመት ሙሉ በተባለበት ‹‹ጁንታ›› የሚል ፍረጃ ዛሬም ለማሳቀቅ ሲጣጣሩ ‹‹ባይበላስ ቢቀር›› እላለሁ፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን….
➔ኬንያ ድረስ ሄዶ ከወያኔ ጋር ሲደራደር የነበረው አፋኙ ፊልድ ማርሻል እንጂ የታፈነው ጄኔራል አልነበረም፡፡
➔ከደብረ ጽዮን ጋር በድብቅ ሲዳራ የከረመውም የእናንተው መንግሥት እንጂ በእነ ጌታቸው ረዳ አንደበት ‹‹ተስፋፊ›› ሲባል የከረመው የአማራ ኤሊት አይደለም፡፡
➔ፋኖም ትጥቅህን ፍታ ለሚለው ትዕዛዝ ተገዢ ያልሆነው ‹‹ጠላት አለኝ›› ብሎ እንጂ እንደ ትሕ-ኦነጎች ‹‹መንግሥት ነኝ›› ብሎ አይደለም፡፡
ሆኖም ግን የካድሬዎች የፌስቡክ ፖስት ከጭንቅላት የሚፈልቅ ሳይሆን እንደ በጀት ከመንግሥት የሚለቀቅ በመሆኑ መንግሥትና ህውሓት ሲደራደሩ ‹‹ከሰላም የሚልቅ ነገር›› አለመኖሩን ያስረዱኻል፡፡ እነ ጄኔራል ተፈራ ሲታሰሩ ደግሞ ‹‹ከህውሓት ጋር በመደራደር ወንጀል እንደተጠረጠሩ›› ይነግሩኻል፡፡
መንግሥት በጠላት ላይ አምርሮ ወደ ጦር ሜዳ ሲገሰግስ ‹‹ልበ-ቆፍጣና›› መሆኑን ይተርኩልኻል፡፡ ድርጎ ሰፋሪው አካል በአገር ላይ ቆምሮ ትግሉን አቋርጦት ሲመለስ ደግሞ ‹‹ልበ ሰፊ›› መሆኑን ይገልጹልኻል፡፡