>

ፖሊስ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱን ባለሥልጣናትን በመስደብ ወነጀለ (ጎንደር ታይምስ)

ፖሊስ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱን ባለሥልጣናትን በመስደብ ወነጀለ

ጎንደር ታይምስ
 
ፍርድ ቤት ቀርበው ለግንቦት 26 ተቀጥረዋል
 
አንጋፋው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ዛሬ አርብ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። ከሳሽ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአገዛዙ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን መስደብ፣ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጬ ትንታኔዎችን ማቅረብ፣ አንድን ብሔር መጥላት  እና ሕገ ወጥ በሆነ መገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ መተንተን የሚሉ ከንቱ ውንጀላዎችን አቅርቧል። ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲያውላቸው የነጠቃቸውን፤ በወረቀት ደረጃ ያለ ረቂቅ መፅሐፍ እና ሌሎች ለሀሰተኛ ውንጀላው የሚያመቹትን ጉዳዮች እስከሚመረምር የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ሙሉ በሙሉ ተፈቅዶለታል።
የጋሽ ታዴዎስ ጠበቃ ታለማ ግዛው የኅላና እስረኛው ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር ቤት እንዲወጡና ዶሴውን በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በመሆኑም ለግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል።
ጠበቃ ታለማ ውንጀላው አገዛዙ በሚመራበት ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 መሰረት ኃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንዲሁም የፕሬስ ነፃነት አዋጁን የሚጥስ መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል። “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚያዩ ባለሥልጣናት ሲመከሩ የተሰደቡ እየመሰላቸው እንጂ አልተሳደቡም።  ስድብም እንኳን ቢሆን ግለሰባዊ ጉዳይ ስለሆነ የግል ተበዳዩ ነው መክሰስ ያለበት” በማለትም አስረድተዋል።
ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሲሆኑ፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሐቀኛ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ ይታወቃሉ።  በተለይም በራስ ሚዲያ ተከታታይ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ትንታኔዎች ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ያቀርባሉ። “‘የአማራ ደም ደሜ ነው” ብለሃል” በሚል ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጣስ ወንጀል ተከሰው ለወራታ እስር ቤት መቆየታቸውም ይታወሳል። በተመሳሳይ በሌላ እስር ለወራት አድራሻቸው ጠፍቶ ታፍነው ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ተለዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ በአብዮታዊ ጦር ሃይሎች ዋና የፖለቲካ አስተዳድር ስር በነበረው ‘ታጠቅ’ ጋዜጣ ከ1975 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላም በዛሬይቱ ጋዜጣ፣ በኢትዮጲስ ጋዜጣ፣ በአስኳል ጋዜጣ፣ በፍትሕ ጋዜጣ፣ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ እና በሌሎች የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች በአምደኝነትና በአዘጋጅነት ለረጅም ዓመታት በነፃው  አገልግለዋል።
የኅሊና እስረኛው የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ፣ ደመላሽ (ቁጥር 1 እና ቁጥር 2)፣ ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ የተሰኙ መፅሐፍትን ለአንባቢያን አበርክተዋል።
Filed in: Amharic