>

ቧልተኛው ታሪክ ከ13 ዓመት በኃላ ተደግሟል... (ኤርሚያስ ለገሰ)

ቧልተኛው ታሪክ ከ13 ዓመት በኃላ ተደግሟል… 
ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ መጣል…!!!”
ኤርሚያስ ለገሰ

*… ከመቼ ጀምሮ ነው ከኤርትራ መንግስት ጋር መገናኘት ወንጀል ሆኖ በአገር ክህደት የሚያስከስሰው?  
 
“ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ መጣል” የዛሬው የብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ የተጠረጠሩበት ወንጀል። ልክ እንደ በፊቱ።
እኔ እምለው “ለውጡ!” “ለውጡ!” “ኢትዮጵያ ቤተ መንግስት ገብታለች” በማለት  የምትናገሩ ሰዎች ምን ተሰምቷችሁ ይሆን?
በሌላም በኩል ክሱ ” ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ መጣል” ከሆነ ለምን በፌዴራል ደረጃ አልታየም? ለምን ወደ አማራ ክልል ተወሰደ? ቁማሩ ያልገባው የአማራ ልሂቅ ይኖር ይሆን?
በብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ላይ የተሠጠው የጊዜ ቀጠሮ 
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ ላይ የ10 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
ዛሬ ጠዋት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ዛሬ ከሰዓት መልስ መቅረባቸውን ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል። ህገ መንገስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል በሚል ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም ነው ጠበቃው ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ለ14 ቀናት ታስረው እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ 10 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም አቶ ሸጋው ተናግረዋል። የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ ባሳለፍነው ሰኞ በአዲስ አበባ ባልታወቁ ሰዎች መታፈናቸው መገለጹ ይታወሳል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር ባደረገው ጦርነት በፌደራል መንግስት ጦር እዝ ስር በመሆን ውጊያ ሲመሩ፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ መቆየታቸው አይዘነጋም።
በስለላ መስራያ ቤቱ የተቋቋመውና ተቋሙ ቅርጾ የሚሰጠውን አጀንዳ እንደወረደ የሚያራምደው “የኔታ” የሚባለው የድረ ገጽ ሚዲያ ጄኔራል ተፈራ ማሞ የአገር ክህደት ፈጽሟል በማለት አስቀድሞ ክስ አቅርቧል። ጂኔራሉ የአገር ክህደት የፈጸሙት ደግሞ ከኤርትራ መንግስት ጋር በተለይም ከኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ፊልጶስ ጋር የፈጠሩት ሚስጥራዊ ግንኙነት ነው ይላል።
እኔም እጠይቃለሁ፣
ከመቼ ጀምሮ ነው ከኤርትራ መንግስት ጋር መገናኘት ወንጀል ሆኖ በአገር ክህደት የሚያስከስሰው?  
፩. የስለላ መስሪያ ቤቱ የጄነራል ተፈራን እስር ለምን ከኤርትራ ጋር ያውም ከኤርትራው ኢታማዦር ሹም ጋር  እንዲያያዝ ፈለገ?
፪. ድርጊቱ ተፈጽሞ እንኳን ቢሆን ከመቼ ጀምሮ ነው ከኤርትራ መንግስት ጋር መገናኘት ወንጀል ሆኖ በአገር ክህደት የሚያስከስሰው?
፫. ሚዲያው አስቀድሞ ብያኔ ለሰጠበት የአገር ክህደት ክስ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣ የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን መስሪያ ቤት ምን ምላሽ ይሰጣል?
Filed in: Amharic