>

የማኦ ዜዶንግ ትምህርት ለፋኖ (መስፍን አረጋ)

የማኦ ዜዶንግ ትምህርት ለፋኖ!

መስፍን አረጋ


“በጥበበኛ የጦር አዛዥ የሚመራ ሠራዊት ሳይታሰብ ግድቡን ጥሶ በሚጎርፍ ደራሽ ውሃ ይመሰላል፡፡  ደራሽ ውሃ ከፍተኛ ቦታን እየለቀቀ፣ ወደ ዝቅተኛ ቦታ እያዘቀዘቀ፣ ዝቅዝቅ በመጉረፉ በሚያገኘው ጨማሪ (እየጨመረ የሚሄድ፣ increasing) ኃይል እንቅፋቶቹን እየጠራረገ ረባዳን ያጥለቀልቃል፡፡  በጥበበኛ የጦር አዛዥ የሚመራ የጦር ሠራዊትም የጠላትን ጠንካራ ጎን እየራቀ፣ ደካማ ጎኑን እየሰነጠቀ፣ እየጎለበተ በመትመም፣ የጠላት ጦር ያልሰፈረበትን የጠላት ግዛት እንበለ ውጊያ በመቆጣጠር ይንቦራቀቅበታል፡፡  ደራሽ ውሃ ወደ መዳረሻው የሚወንዘው አወናነዙን ከመልክዓምድሩ ጋር እያዛመደ ፍጥነቱን፣ ስፋቱንና ጥልቀቱን በመለዋወጥ እንደሆነ ሁሉ፣ በጥበበኛ የጦር አበጋዝ የሚመራ ሠራዊትም ወደ ድል የሚያመራው የጠላቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ስልቱን እንዳስፈላጊነቱ በመለዋወጥ ነው፡፡”   ሰንሹ (Sun Tzu)

“የውጊያ እቅድ ከውጊያ በፊት አስቀድሞ ቢዘጋጅም፣ ውጊያው በሚካሄድበት ወቅት ከሁኔታወች ጋር እየተገናዘበ ሊሻሻል የሚችል፣ ካስፈለገ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ የሚችል ኋሽ (dynamic) (ማለትም ተቀያያሪ) እቅድ መሆን አለበት፡፡  የውጊያ እቅድን ድንጋይ ላይ እንደተጻፈ ኗሚ (static) (ማለትም ቋሚ) መመርያ ሙጥኝ ማለት ትርፉ የሽንፈት ጽዋን መጎንጨት ብቻ ነው፡፡  የውጊያ ሂደት የውሃ ላይ ኩበት ስለሆነ፣ ሁኔታወች እየተገናዘቡ ማጥቃት ወደ መከላከለ፣ መከላከል ወደ ማጥቃት፣ መግፋት ወደ ማፈግፈግ፣ ማፈግፈግ ወደ መግፋት ባስፈላጊው ፍጥነት መለወጥ መቻል አለበት፡፡  ይከላከል የነበረ ጦር ሊያጠቃ የሚችልበት ቀዳዳ ላጭር ጊዜ ሊከፈትለት ይችላል፡፡  ያጠቃ የነበረ ጦር ደግሞ ወደ መከላከል እንዲዞር ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊገደድ ይችላል፡፡”   ማኦ ዜዶንግ (Mao Zedong)

የቻይናው ቻንግ ካይሸክ (Chiang Kai-shek) የቻይናን ሕዝባዊ ሠራዊት በማጥፋት የቻይና ብሔርተኞችን  ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ የኮሚንታንግ (Kuomintang) ጠቅሊሞ (generalissimo) እንደነበረ ሁሉ፣ ዐብይ አሕመድም የአማራን ሕዝባዊ ሠራዊት በማጥፋት የአማራን ሕዝብ ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ የኦነግ ጠቅሊሞ (generalissimo) ሁኗል፡፡  ቻንግ ካይሸክ የቻይና ብሔርተኞችን ጨፍጭፎ ቻይናን ለምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች (neocolonialists) እንዲያመቻች  ስንቅና ትጥቁን ያቀርቡለት የነበሩት ምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ እንግሊዞችና አሜሪቃኖች) እንደነበሩ ሁሉ፣ ዐብይ አሕመድም የኢትዮጵያ ብሔርተኞ የሆኑትን አማሮችን ጨፍጭፎ ጦቢያን ለምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች እንዲያመቻች ስንቅና ትጥቁን የሚያቀርቡለት ምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ እንግሊዞችና አሜሪቃኖች) ናቸው፡፡    

የቻይና ሕዝባዊ ሠራዊት በቻንግ ካይሸክ የኮሚንታነግ ሠራዊት ዙርያውን ተከቦ ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ላይ እንደነበረ ሁሉ፣ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊትም በዐብይ አሕመድ ኦነጋዊ ሠራዊት ዙርያውን ተከቦ ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ላይ ነው፡፡  የቻንግ ካይሸክን ከበባ በርግዶ፣ ወደ ሰሜን ረዥም ጉዞ (Long March) ተጉዞ፣ ወገን ቀጠና ደርሶ፣ ከቻንግ ካይሸክ ምት አገግሞ፣ ቻንግ ካይሸክን መልሶ አጥቅቶ፣ የኮሚንታንግን ሠራዊት እየገረፈ አባሮ ታይዋን ላይ በመሸከፉ እልህ አስጨራሽ ሂደት፣ የቻይና ሕዝባዊ ሠራዊት መሪ (ማኦ ዜዶንግ) እንደተወለደ ፣ የዐብይ አሕመድን ከበባ በርግዶ፣ ወደ ሰሜን ረዥም ጉዞ (Long March) ተጉዞ፣ ወገን ቀጠና (ኤርትራ ደንበር) ደርሶ፣ ከዐብይ አሕመድ ምት አገግሞ፣ ዐብይ አሕመድን መልሶ አጥቅቶ፣ የኦነግን ሠራዊት እየገረፈ አባሮ ነገሌ ቦረና ላይ በመሸከፉ ሂደት የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት መሪ ይወለዳል፡፡ 

 የዐብይ አሕመድን ኦነጋዊ ከበባ እየበጣጠሱ ወደ ሰሜን ተጉዞ ወገን ቀጠና ለመድረስ የሚደረገውን ረዥም ጉዞ ለማሳለጥ ደግሞ የማኦ ዜደንግ በተግባር የተፈተኑ ምክሮች ፍቱን ናቸው፡፡  ከነዚህ ፍቱን ምክሮች ውስጥ ደግሞ ዋናወቹ ሦስቱ ስልታዊ ትእዛዞች (The Three Tactical Commandments) እና አሥሩ ስነስርታዊ ትዕዛዞች (The Ten Disciplinary Commandments) ናቸው፡፡

የማኤ ዜደንግ ሦስቱ ስልታዊ ትዕዛዞች (The Three Tactical Commandments)  የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ጠላት ሲበረታ አፈግፍግ
 2. ጠላት ሲዳከም አጥቃ
 3. ጠላት ሲያርፍ አውክ

የማኦ ዜዶንግ አሥሩ ስነስርዓታዊ ትዕዛዞች (The Ten Disciplinary Commandments) ደግሞ የሚከተሉ ናቸው፡፡

 1. ያለቃህን ትእዛዝ ቅንጣት ሳትጠራጠርና ላፍታ ሳታንገራግር ፈጽም፡፡
 2. የሕዝብን ንብረት አትንካ፣ መርፌም ብትሆን፡፡
 3. ከሕዝብ ስጦታ አትቀበል፣ ክርም ብትሆን፡፡
 4. ከሕዝብ ምንም ነገር አተዋስ፣ የግድ መዋስ ካለብህ ደግሞ የተዋስከውን ወዲያውኑ ተጠቅመህ በተዋስክበት ሁኔታ መልስ፣ ካበላሸህም ትክክለኛ ዋጋውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
 5. ከገበያም ሆነ ከየትም ቦታ ለምትገዛቸው ወይም ለምትሸምታቸው ነገሮች ሁሉ ተገቢ ዋጋቸውን ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
 6. በውጊያ ወቅት ላወደምከው ወይም ላጠፋኻው ወይም ለጎዳኻው የሕዝብ ሐብት፣ ንብረትና ሂወት ተገቢውን ካሳ ሙሉ በሙሉ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
 7. የውጊያ ግርግር ለዘራፊ ያመቻልና፣ በግርገሩ የተዘረፈን፣ የተበዘበዘን ወይም የተመዘበረን የሕዝብ ሐብትና ንብረት አስመልስ፣ ማስመለስ ካልቻልክ ደግሞ ተገቢውን ካሳ እራስህ ክፈል (አልቀበልም ብትባል እንኳን በትሕትና አሳምነህ ሳትከፍል አትንቀሳቀስ)፡፡
 8. ሴት፣ ወንድ፣ ሕጻን፣ አረጋዊ ሳትል ማናቸውንም ሰው ስታናግር ሁልጊዜም በትሕትና አናግር፣ በተቻለህ መጠን ደግሞ እርዳ፡፡
 9. ልጃገረድ፣ ኮረዳ፣ ባለትዳር፣ ፈት፣ ጋለሞታ፣ ሴታአዳሪ ሳትል ሴትን አክብር እንጅ በጭራሽ እንዳትደፍር፡፡  ግዳጅ ላይ እስካለህ ድረስ ከሩካቤ ሥጋ ፈጽሞ ታቀብ፡፡
 10. ምርኮኛም ሆነ እስረኛ አታጎሳቁል፣ በተቻለህ መጠን ተንከባከብ፡፡

ሦስቱ ስልታዊ ትእዛዞች እና ካሥሩ ስነስርታዊ ትዕዛዞች በተጨማሪ ደግሞ ማኦ ዜዶንግ ያረቀቃቸው የተለያዩ መመሪያወች ነበሩ፡፡  ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 

 1. የአካል ብልቶች ብዙ ቢሆኑም፣ የአንድ በአንድ ለአንድ ናቸው፡፡  ዓይን ጆሮን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የደንቆሮ ዓይን ይሆናል፡፡  ጆሮ ዓይንን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የእውር ጆሮ ይሆናል፡፡  እጅ እግርን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የቆማጣ እጅ ይሆናል፡፡  እግር እጅን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የጉልድፍ እግር ይሆናል፡፡  የጦር መሪ የመጀመርያው ተግባር ሁሉም የሠራዊቱ ክፍሎችና አባሎች ላንድ ዓላማ ባንድነት የቆሙ አንድ መሆናቸውን በማሳመን በመካከላቸው ሠራዊታዊ ፍቅርና መከባበር እንዲያደር በማድረግ አንተ ትብስ አንቺ ትብስን ማስፈን ነው፡፡  መናናቅ አብሮ ለመወደቅ፣ መከባበር አብሮ ለመናር፡፡ 
 2. ጠቢብ የጦር አዛዥ ንግግር የማያበዛ ጭምት ነው፣ በቀላሉ የማይበሳጭ ሆደ ሰፊ ነው፣ የሚተማመነው በልቡ ሳይሆን ባይምሮው ነው፣  በእቅድ እንጅ በደመነፍስ አይመራም፣ ደንብና ስርዓትን አክብሮ ያስከብራል፣  ለሂወቱ አይሳሳም፣ ለንብረት አይጓጓም፡፡  ሞት ጅብ ነው፣ የደፈረውን ይፈራል፣ የፈራውን ይደፍራል፡፡  ዘጠኝ ሞት መጣ ሲለሁ አንዱን ግባ ካልከው ዘጠኙም ይመለሳል፡፡  
 3. አንዳንድ ሰወች የራሳቸውን ማንነትና ምንነት አብጠርጥረው ሲያውቁ፣ ስለባላንጣቸው ማንነትና ምንነት ግን ፍንጭ እንኳን የላቸውም፡፡  አንዳንዶቹ ደግሞ የነዚህ ዓይነት ሰወች ተቃራኒወች ናቸው፡፡  ሁለቱም ዓይነት ሰወች ለጦር አመራር ብቁ አይደሉም፡፡  ጠላትህን መርታት የምትችለው ያንተን ብቻ ሳይሆን የጠላትህን ማንነትና ምንነት አብጠርጥረህ ስታውቅ ብቻ ነው፡፡   

ስለዚህም ፋኖ የጠላቱን የዐብይ አሕመድን ምንነትና ማንነት አብጠርጥሮ ማወቅ አለበት፡፡  ዐብይ አሕመድ ወተት ነጭ ነው ቢል መታመን የሌለበት ውሸታም ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ የሆኑ አጭበርባሪ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ የሚፈልገውን ለማግኘት እስካስፈላጊው ለመዝቀጥ ቅንጣት የማያቅማማ ዝቃጭ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ በእኩይ ባሕሪ የተጨማለቀ ነውረኛ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ጥላው የሚያስበረግገው ፈሪ ነው፡፡  ፊሪ ስለሆነ ደግሞ የፈሪነቱን ያህል ጨካኝ አረመኔ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ለዚሁ ሁሉ የተዳረገው ደግሞ በከረረ የማንነት ቀወስ ክፉኛ የሚሰቃይ የስነልቦና በሽተኛ ስለሆነ ነው፡፡ 

ዐብይ አህመድ ግማሽ አማራ (በዚያ ላይ ደግሞ ከአማራ ጋር የተጋባ) ነው ተብሎ በኦነጋውያን ስለሚጠረጠር፣ ባይነ ቁራኛ እንደሚጠበቅና እያንዳንዷ ድርጊቱ ባጉሊመነጽር (microscope) እንደምትመረመር አሳምሮ ያውቃል፡፡  ትንሽ ቢሳሳት ግዙፍ ውለታው መና ቀርቶ ከሃዲ እንደሚባል ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡  እስከጣፈጠ ድረስ ተላምጦ የሚተፋ አገዳ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ የሂወቱ አልፋና ኦሜጋ የሆነው ብቸኛው ጥረቱ ጥፍጥናው አልቆ እንዳይተፋ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ኦነጋውያን ትናንት ከሚያምኑት የበለጠ ዛሬ እንዲያምኑት፣ ትናንት ካደረገው የከፋ ዛሬ ማድረግ አለበት፡፡  ስለዚህም በአማራ ሕዝብ ላይ የበለጠ እና የበለጠ ጭራቅ እየሆነ መሄድ አለበት፣ እየሄደም ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር ዐብይ አህመድ በማንነቱ ምክኒያት መቸም ከማይወጣበት እኩይ አዟሪት (vicious circle) ውስጥ የገባ ኦነጋዊ አውሬ ነው፡፡  

 ስለዚህም፣ ፋኖ የራሱን ሕልውና በመታደግ የአማራን ሕዝብ ሕልውና መታደግ የሚችለው ጫንቃው ላይ የተከመረበትን ይህን ኦነጋዊ አውሬ በተቻለው ፍጥነት አሽቀንጥሮ በመጣል ብቻ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድን አሽቀንጥሮ መጣል የሚቻለው ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተደግፎ የቆመባቸውን የግራና የቀኝ ምርኩዞቹን በመቀማት ብቻ ነው፡፡  እነዚህ ሁለት ምርኩዞቹ ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆኑ ልክ እንደራሱ እንደ ዐብይ አሕመድ በከፍተኛ የማንነት ቀውስ የሚሰቃዩት ደመቀ መኮንን እና ተመስገን ጡሩነህ ናቸው፡፡  

የአማራ ሕዝብ ለዚህ ሁሉ ውርደት የተዳረገው ደመቀ መኮንንን፣ ተመስገን ጡሩነህን፣ ሰማ ጥሩነህንና፣ አበባው ታደሰን የመሳሰሉት፣ አማራዊ ስም እንጅ አማራዊነት የሌላቸው የአማራ ለምድ የለበሱ የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች፣ የአማራን ሕዝብ በገፍና በግፍ እያስጨፈጨፉ በራሱ በአማራ ሕዝብ መኻል ዝንባቸው እሽ ሳይባል ተኩራርተው እንዲኖሩ ስለተፈቀደላቸው ብቻና ብቻ ነው፡፡   

Email: መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic