>

"ጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑ አሳስቦናል... (ኢሰመኮ) !!"

“ጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑ አሳስቦናል…!!!”

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)


እነዚህ ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመታሰራቸው ባሻገር የተወሰኑቱ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና በቤተሰቦቻቸው ያልተጎበኙ መኖራቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።

ተቋሙ ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ “ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል” ብሏል።

የተወሰኑት ተጠርጣሪ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው እንደተጎበኙና በተለያየ የጊዜ መጠን ወደ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ የሚጠቁመው የኢሰመኮ፤ መገለጫ አያይዞም “በርካታ ታሳሪዎች [ግን] ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን” እንደተገነዘበ አስፍሯል።

በተለይም በአማራ ክልል “በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጭ ጭምር በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ ተቸግረዋል” ሲል መግለጫው ያክላል።

በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች “ሕግ የማስከበር” ያሉትን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እየተሰማ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ መሰወራቸው የተነገረው የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ” ሞክረዋል በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙና በባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በባሕር ዳር ጠቅላይ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል።

በማኅበራዊና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት በመተቸት የምትታወቀው መስከረም አበራ ቅዳሜ ግንቦት 13/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጦርነቱን በመቃወም እንዲሁም የሰላምና ድርድር መንገዶች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬም መታሰሩ ተዘግቧል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዘጠኝ አባላትም ግንቦት 10/2014 ዓ. ም. በሁለት ከተሞች መታሰራቸውን ሮይተርስ በአሜሪካ የሚገኘውን የአማራ ማኅበር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች “ሕግ የማስከበር” ያሉትን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ ጎጃም በሰሜን ወሎ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ጠቅሶ ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች “ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች” እንደሚገነዘብ ጠቁሞ፣ ሆኖም ግን “የዚህ ዓይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” አስታውቋል።

የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ እንደሚገባም መግለጫው ያሳስባል።

መግለጫው አክሎም “በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ ሊደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በድንገተኛ ጉብኝት ለመከታተል በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት፣ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቅሶ፣ ሁሉም የፌደራል እና የክልል መንግሥት አካላት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቋል።

Filed in: Amharic