>
5:21 pm - Wednesday July 20, 9278

በወቅታዊ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ....!!! (ባልደራስ)

በወቅታዊ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ….!!!

ባልደራስ


ተረኛው ኦህዴድ መራሹ መንግሥት፣ በሃሰት ክስና ውንጀላ በተደጋጋሚ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አባላትንና መሪዎችን በግፍ ማሰሩን እንደቀጠለ ነው። በአሁኑ ወቅት ከ12 የማያንሱ የባልደራስ አባላትና የአዲስ አበባ ወጣቶች ያለምንም ወንጀል በእስር ላይ ይገኛሉ።

መንግሥት ሌሎች የባልደራስ አባላትንም ለማሰር በማሳደድ ላይ ይገኛል። ባልደራስ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን በተለያዩ ክልሎች በጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻም ላይ እንቅፋት የመፍጠር ሂደቱ እንደቀጠለ ነው። በወሎ፣ በጎጃምና በጎንደር በአርባምንጭ፣ በድሬደዋ፣ በሐረር የፊርማ ማሰባሰቡን ሥራ እየሰሩ በሚገኙ አባላት ላይ ወከባ እንግልት እና እስራት እየተካሄደባቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ እስሩና አፈናው በነፃ ሃሳባቸውን በሚገልፁ ወታደራዊ አዛዦች፣ ጋዜጠኞችና የታሪክ እና የፖለቲካ ምሁራን ላይ ተፋፍሞ ቀጥሏል። ታዋቂው ጀነራል ተፈራ ማሞ፣የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ም/ል ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታቸዉ፣ታዋቂው የታሪክ እና የፖለቲካ ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ፣ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ መምህርት እና የፖለቲካ ተንታኝ መስከረም አበራ የዚሁ ዘመቻ ሰለባ ከሆኑ ቀናቶች አልፈዋል። ከዚህ ቀደምም ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይም ተመሳሳይ አፈናና እስር ደርሶባቸው እንደ ነበርም ይታወሳል።

ይህ የመንግሥት የማናለብኝነት አካሄድ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ቡድኖችንና ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን እንዲኹም መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ተስፋ በማስቆረጥ፣ ህዝቡን ወደ ህዝባዊ አመጽ እንዲሸጋገር እየገፋው ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦህዴድ መራሹ የብልፅግና መንግሥት በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በፋኖ ላይ የከፈተው የመግደለና የማሳደድ ዘመቻ ቀይ መስመር ያለፈ አደገኛ አካሄድ መሆኑንና መጨረሻው እንደማያምር ሊታወቅ ይገባል። ፋኖና የአማራ ህዝብ የሚነጣጠሉ አይደሉም። ፋኖ ላይ የተነጣጠረ ማንኛው እርምጃ በአማራ ህዝብ ላይ ብሎም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው። ፋኖ ለአማራ ህዝብ ህልውና ብሎም ለሀገሩ አንድነት ደሙን የገበረ ህዝባዊ ኃይል እንጅ አሸባሪ አይደለም። ፋኖ ከልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያና፣ መከላከያ ጎን በመቆም አገር አፍራሹን የትህነግን ኃይል ግምባር ለግምባር ገጥሞ የተዋደቀ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነትን የከፈለ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ መመኪያና የኢትዮጵያ አንድነት  እውነተኛ ተምሳሌት ነው። ፓርቲያችን ባልደራስ ኦህዴድ ብልጽግና በፋኖ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የህወሓት- የኦነግ እና የኦህዴድ ብልጽግና እስተራቲጃዊ ግብ የሆነውን ኢትዮጵያን በማፈራረስ ታላቂቷን ትግራይ እና ነጻ ኦሮሚያን ለማዋለድ በኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ እየተውጠነጠነ ያለውን ደባ ለማሳካት እየተደረገ ያለ እርምጃ እንደሆነ ይገነዘባል። በአጠቃላይ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ የኦህዴድ ብልጽግና መንግስት በተለይ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ እየወሰደ ያለው አምባገነነዊ የግድያ የአፈና እና የእስር አገርን የማተራመስ እርምጃ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት አገራችን ከገባችበት የታሪክ እና የፖለቲካ ስብራት በእጀጉ የከፋ እንደሆነ አርጎ ይመለከተዋል። በመሆኑም የአገራችንን የወቅቱን ሁኔታ አስመልክቶ ፓርቲያችን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1.መንግስት በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አባላት ላይ፣ በጋዜጠኞች፣ በጦር መኮንኖች፣ ድምፃቸውን በሚያሰሙ የታሪክ እና የፖለቲካ ምሁራን ላይ የሀሰት ክሶች በመጠቀም እያደረሰ ያለውን እስርና አፈና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በፅኑ እያወገዘ፣ መንግሥት ከዚህ አሳፋሪ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆጠብና ያለአግባብ ያሰራቸውን ንፁሃን የህሊና እስረኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታ ይጠይቃል፤

2.በሀገራችን ውስጥ ትልልቅ ያልተፈቱ ችግሮችን (ማለትም ሱዳንን፣ትህነግን፣ ሸኔን) ወደ ጎን ትቶ የብልጽግና መንግሥት ለአማራ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ መከታ በሆነው በፋኖ ላይ የተከፈተውን አገርን የሚያፈርስ አደገኛ የክህደት ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆም ይጠይቃል፣

3.የመከላከያ ሰራዊቱ፣ ልዩ ኃይሉና፣ ሚሊሻው ለአንድ ዓላማ በጦር ሜዳ ላይ አብሮት ሲዋደቅ እና በጀግንነት የአገሩን ህልውና ለመጠበቅ የህይወት መስዋዕትን ሲከፍል የቆየዉን እና እየከፈለ ባለው ፋኖ ላይ ቃታ እንዳይስብ፤ ይልቁንም ፋኖን እንዲጠብቀው እና ከጎኑ እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፤

4.መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የአማራው ማህበረሰብ ከአብራኩ ከወጡት ከጀግኖች ልጆቹ ከፋኖ ጎን በመቆም የአማራን የህልውና ትግል እንዲደግፍ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ እንዲታደጋት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፣

5.ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝቡ አንድ በመሆን ይህን ዘረኛና ከፋፋይ የብልፅግና መንግሥት እንዲታገለው ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለዲሞክራሲ!                                                                           

 ግንቦት 15/2014 ዓ.ም.

ድል ለአገር አንድነት ተፋላሚው ፋኖ!                                                                     

አዲስ አበባ   መንግሰታዊ ግድያ፣እስር እና አፈና ይቁም!!!   

Filed in: Amharic