>
5:29 pm - Thursday October 10, 2165

የኢትዮጵያውያን እናቶች እና ሴቶች የዕርቀ-ሰላም ጥሪ!! (ተረፈ ወርቁ ደስታ)

የኢትዮጵያውያን እናቶች እና ሴቶች የዕርቀ-ሰላም ጥሪ!!

ተረፈ ወርቁ ደስታ

የዓለም ዕርቅና ሰላም ሀገር በቀል ግብረ ሠናይ ድርጅት ምቹ ቤት ከተባለ የሚዲያ ዝግጅት ክፍል ጋር በሀገራችን ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ ለግማሽ ቀን የዘለቀ ስብሰባ አድርገን ነበር፡፡ ይህን የዕርቀ-ሰላም ስብሰባ የተጠራው በኢትዮጵያውያን እናቶችና ሴቶች አማካኝነት ነበር፡፡ ‘‘ልጆቼ በጡቴ፣ ልጆቼ በሞቴ፣ ልጆቼ አፈር ስሆን!!’’ በሚል የኢትዮጵያውያንን የቆየ ባህልና ወግ መሠረት ባደረገ የተማሕጽኖ ቃል የተካሄደው ይህ የሰላም ጉባኤ፤ ‘‘ኢትዮጵያን እናድናት፤ ሕዝባችንን ከዳግመኛ ጦርነት፣ ሰቆቃ፣ ስደትና መፈናቀል እንታደግ!’’ በሚል ቅንአትና ቁጭት በብርቱ እንባ ጭምር የታጀበ፣ የሰላም ጥሪ የተካሄደበት ዝግጅት ነበር፡፡

በእውቋና አንጋፋዋ ደራሲ ፀሐይ መላኩ፤ ‘‘ኢትዮጵያ ልጆቿን ለሰላም፣ ለፍቅርና ለዕርቅ ትጣራለች!’’ በሚል በቋጠሩት ግጥም የተጀመረው የኢትዮጵያውያን እናቶችና ሴቶች የዕርቀ-ሰላም ጥሪ፤ አስከትሎም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሐረገወይን ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት- በእናቶች፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ መከራና ሰቆቃ በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ዶ/ር ሐረገወይን በዚሁ ገለጻቸውም፤ ሀገራችን አሁን እንዳለችበት ፈታኝ ሁኔታዎች ሲከሰቱና ሰላም ሲጠፋ፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭቶች ሲከሰቱ፤ ‘‘እኛ እናቶች፣ እኛ ሴቶችን ምን ማድረግ እንችላለን?!’’ በሚል ያቀረቡት በምስል ጭምር የታጀበው ገለጻ/ፕሬዜንቴሽን ያለንበት እውነታ አሳዛኝ መሆኑን፤ በሀገራችን የሆነውና እየሆነ ያለው ነገር እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ አንገታችንን በሃፍረት እንድንደፋ ያደረገን መሆኑን በእንባ ጭምር የገለጹበት፤ የስብሰባውን ተሳታፊዎች ስሜት የነካና ያስለቀሰ ጥናታዊ ገለጻ ነበር፡፡ ታሪክ እንደሚመሰክረውም ሀገራችን ኢትዮጵያ፤

  • በሺሕ ዘመናት የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ- ለአፍሪካውያን፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራትና የነጻነት ትእምርት/ሲምቦል የሆነች፤
  • የሰው ልጆች ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ምንጭ፣ ከአይሁዳዊው ሊቀ-ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ መሐመድ አንደበት ስሟ በምስጋና፣ በአድናቆት ከፍ ያለ፤
  • በግሪካውያኑ ፈላስፎችና ጠቢባን- በእነ ሆሜርና ሄሮዱተስ ሥራዎች ውስጥ ትልቅ የክብር ስፍራን የታደለች ሀገር- ኢትዮጵያ፤
  • የፓን አፍሪካን ፍልስፍናን አቀንቃኞች – ከዊልያም ዱቦይስ እስከ ማርከስ ጋርቬይ፣ ከኬንያው የነጻነት አባት ጆሞ ኬንያታ እስከ ጋናው የነጻነት አባት ዶ/ር ክዋሜ ንኩሩማ፣ ከደቡብ አፍሪካዊው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የዕርቀ-ሰላም ሰው ኔልሰን ማንዴላ እስከ ዚሙባቡዌው የነጻነት አርበኛ ሮበርት ሙጋቤ ድረስ በልባቸው ጽላት ውስጥ የታተመች የነጻነት ቀንዲልና ኩራት የሆነች ሀገር … ኢ-ት-ዮ-ጵ-ያ!!

ከኮንጎ እስከ ላይቤሪያ፣ ከሶማሊያ እስከ ሱዳን፣ ከዩጋንዳ እስከ ሩዋንዳ ከአፍሪካ ምድርም አልፋ ኮሪያ ልሣነ-ምድር ድረስ ዘልቃ የሰላም አስከባሪ ጦርን ያዘመተች፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ኅብረት፣ ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ ተባበሩት መንግሥታት የሰላምና የአንድነት ዘብ ሆና የቆመች ሀገራችን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ግን ሰላም ርቋት ‘‘የሰላም ያለ!’’ እያለች ነጋ ጠባ የምትጮኽ ሀገር ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ ልጆቿ በዘር/በጎሳ፣ በሃይማኖት ልዩነት እርስ በርስ የሚጋደሉባት ምድር የመሆኗ ነገር በጣሙን የሚያሳፍር፣ ልብን በኀዘን ጦር የሚወጋ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የሀገራችን ወቅታዊና አሳዛኝ እውነታ ክፉኛ ልባቸውን የሰበራቸው ኢትዮጵያውያን እናቶች አንጀታቸውን በመቀነታቸው አስረው፤ ‘‘እባካችሁ ልጆቼ በጠባችሁት ጡቶቻችን፣ ባዘላችሁ በጀርባችን፣ እረ በሞታችን፣ እረ አፈር ስንሆን… ዳግም በኢትዮጵያ ምድር የጦርነት ነጋሪት አይሰማ፣ ለሞትና ለእልቂት ከሰገባቸው ሰይፍን የመዘዙ የአንድ አብራክ ከፋይ የሆኑ ልጆቻችን ሰይፋቸውን ወደ ሰገባቸው መልሰው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ለሰላም፣ ለዕርቅ ይዘምሩ!’’ በማለት ነበር የእናትነት ተማሕጽኖአቸውን ያቀረቡት፡፡ 

በዚህ የእናቶች የሰላም ጥሪ መድረክ ላይ ጥሪያቸውን ካስተላለፉ እናቶች መካከልም፣ ከሁለት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል ተከስክሶ በወደቀው አውሮፕላን ሆስቴስ ልጃቸውን ያጡት የሆስተስ አያንቱ እናት ወ/ሮ ክበብዋ ለገሠ አንዷ ነበሩ፡፡

ወ/ሮ ክበብዋ በኦሮሚፋ ቋንቋ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ባስተላለፉት የሰላም ጥሪ መልእክታቸው እንዲህ ነበር ያሉት፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በተከሰከሰው አውሮፕላን ያለቁ ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎችን- ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሳይል እንደ ባህሉ አልቅሶ እንደ ሃይማኖቱ አርባና ሙት ዓመት አውጥቶ ለዓለም ሕዝብ ሰብአዊነቱን፣ ርኅራኄውንና ፍቅሩን የገለጸ ማኅበረሰብ አካል የሆንን እኛ ኢትዮጵያውያን በምን ምክንያት ነው እንዲህ ወዳለ የጭካኔ ሥራ ውስጥ የገባነው?!

እንዴትስ ነው የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት አጥር ሳይገድባቸው እነዛን በምድራችን ላይ በዚህ አሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸው የተቀጠፈ ሰዎችን የፈጣሪ አምሳል፣ ክቡር የሰው ልጆች ናቸው ብለው እንባቸውን ያፈሰሱ የሰብአዊነትንና የርኅራኄን ልክ በታየበት በሀገራችን ምድር፣ የእኛው ልጆች የገዛ ወገናቸው ላይ ጨክነው ዘቅዝቀው ለመስቀልና እንደ ማገዶ እሳት ውስጥ ማገደው ፌሽታና ደስታ ሲያደርጉ ለማየት ፈቀዱ?! ይህ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እናቶች ትልቅ ሰቆቃና የልብ የስብራት ነው፡፡

እናም እባካችሁ ልጆቻችን በጠባችሁት ጡቶቻችን ባዛላችሁ ጀርባችን ስንሞት አፈር ስንሆን የፍቅር፣. የዕርቀ-ሰላም ጥሪያችንን ስሙን በማለት ተማሕጽኖቸውን አቅርበዋል፡፡ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ በብሔረሰብ የመጡ ኢትዮጵያውያን እናቶችም በየቋንቋቸው ተመሳሳይ የሆነ የዕርቀ-ሰላም ጥሪያቸውን ለመንግሥት፣ ለተፋላሚ ኃይሎችና ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው አስተላልፈዋል፡፡

‘‘ሰላም የሚጠፋው አንዳንችን ለሌላችን አለኝታ፣ የአንደኛችን መኖር ለሌላው ህልውና መሆኑን ሙሉ በሙሉ ስንዘነጋው ነው፡፡ የፍቅር ኃይል የበላይነት በያዘበት መንደር በሰላም መኖር አይቸግርም፤ እውነተኛ ፍቅር ካለ [የትኛውም] ዓይነት ልዩነት ሰላም እንዲጠፋ ምክንያት አይሆንምና፤’’ የዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረ-ሠናይ ድርጅት ሁላችንም ኢትዮጵያውን ለሰላማችን፣ ለአብሮነታችን በአንድነት ዘብ እንቁም እንላለን፡፡

https://youtu.be/z3w6_BbiZTo

ሰላም ለሀገራችን ይሁን!!

Filed in: Amharic