ከባሕርዳር ታፍነው ንፋስ መውጫ (ጎንደር) የተወሰዱ እስረኞች እየተደበደቡ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ !!
ባልደራስ
*….የስንታየሁ ቸኮል ባለቤት ከአዲስ አበባ ባህርዳር ሄደው ጠየቁ… !!
አገዛዙ በፋኖ ላይ የከፈተውን የማሳደድ ዘመቻ ተከትሎ በባሕር ዳር ታፍነው ከቆዩ በኋላ ወደ ደቡብ ጎንደር፤ ጋይንት፤ ነፋስ መውጫ የተወሰዱ የግፍ እስረኞች ለፌዴራል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል።
ከትናንት ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየጠበቋቸው የሚገኙ ፖሊሶች መካከል በርካቶቸኡ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውንም የእስረኞች ቤተሰቦች ተናግረዋል።
ቤተሰቦች እስረኞችን ለመጠየቅ ከባሕር ዳር ተነስተው ነፋስ መውጫ ቢገኙም፣ ጥየቃውን ተከልክለዋል። እስረኞቹ በፖሊስ እየተደበደቡ መሆኑንምቤተሰቦቹ እየተናገሩ ናቸው።
በሥፍራው በግፍ ከታሰሩት ወጣቶች መካከል፣ አክቲቪስት ቲና በላይ እና የአማራ ሕዝባዊ ሃይል (ፋኖ) የባሕር ዳር አባላት የሆኑት ፋኖ አሳዬ እውነቱ፣ ፋኖ ሰሎሞን አብዩ እና ፋኖ ጌታቸው ሙጨ ይገኙበታል። ፋኖ ሰሎሞን ከህወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት በጋሸና ግንባት ብዙ ጀብዱ ሰርቶ የቆሰለ ነው። አሁንም የጥይት ሽራፊ ከሰውነቱ አልወጣለትም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባሕር ዳር የታሰረው ጋዜጠኛ ያለለት ወንድዬ የት እንደተወሰደ አልታወቀም።
በሌላ በኩል፣ ላለፋት ሁለት አመታት በቃሊቲ እና ቂሊንጦ እስር ቤት ሲንገላቱ የቆዩት የአቶ ስንታየሁ ቸኮል ባለቤት ወ/ሮ ውዴ ስንቄ ወደ ባህርዳር በማቅናት ባለቤታቸውን ጠየቁ።
የባልደራስ የድርጅት ጉዳይ ኋላፊ እና የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል ፣”ለምን የግፉሀን ድምፅ ይሆናሉ?” በሚል በህግ ማስከበር ሰበብ ተይዘው በባህርዳር አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ከቀናት በፊት መታሰራቸው ይታወሳል።
ወ/ሮ ዉዴ ስንቄ ላለፋት ሁለት ዓመታት በቂሊንጦ እና ቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች አቶ ስንታየሁ ቸኮልን እና የባልደራስ የግፍ እስረኞች የነበሩትን ለመጠየቅ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ውዴ ስንቄ፣ አሁንም እርቀቱ እና አንግልቱ ሳይገድባቸው የገዢዉ ፓርቲ የግፍ እስረኛው ባለቤታቸውን አቶ ስንታየሁ ቸኮልን በባህርዳር አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ጠይቀዋል።