>

ላለፉት 31  አመታት በተለይም  ያለፉት 4 ፣ ኦሮሞ በጣም ተጎዳ እንጂ አልተጠቀመም. . !!!  (ግርማ ካሳ)

ላለፉት 31  አመታት በተለይም  ያለፉት 4 ፣ ኦሮሞ በጣም ተጎዳ እንጂ አልተጠቀመም. . !!! 

ግርማ ካሳ


እስቲ ለኦሮምኛ ተናጋሪ፣ ኦሮሞ ነን ለሚሉ የኦሮሞ ልጆች ጥያቄ ላቅርብ፡፡

ይኸው ላለፉት 4 አመታት ከኦሮሞ ድርጅት የመጡ፣ ኦሮሞ ነን የሚሉ፣ የኦሮሞ ክልልንም የፌዴራል መንግስትንም እያስተዳደሩ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ ለ27 አመታት፣ በሕወሃት ዘመን ፣ ምንም እንኳን ከላይ ላይ የሕወሃት ሞግዚት ቢሆኑም፣ ቢያንስ የኦሮሞ ክልልን ያስተዳደሩ የነበሩት ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ በሁሉም የኦሮሞ ክልል ዞኖች፣ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ በሁሉም የኦሮሞ ክልል ከንቲባዎች ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ እንግዲህ በድምሩ 31 አመታት ማለት ነው፡፡

መሰረታዊ በሆኑ የሰላም፣ የፍትህ፣ የልማት፣ የእኩልነት፣ የስራ እድል፣ የመሻሻል ጥያቄዎች ዙሪያ ኦሮሞ አሁን ነው የሚሻለው ወይንስ ከ31 አመት በፊት  ?

እርግጥ ነው ከ31 አንድ አመት በፊት የነበረ አሁን ያለ መልካም ነገር አለ፡፡ በብዙ ቦታ ኦሮሞ በኦሮምኛ አገልግሎት እንዲያገኝ እንዲማር ፣ ባህሉን ቅርሱን እንዲያዳብር ተደርጓል፡፡ ያ በፊት አልነበረም፡፡

እርሱም ቢሆን ግን በተሳሳተ መንገድ ተግባራዊ ስለሆነ በአንድ በኩል ጥቅም ሲያስገኝ በሌላ በኩል ጉዳት አምጥቷል፡፡ “ኦሮሞ ኦሮምኛ ይማር” በሚል ኦሮምኛ ተምሮ፣ አማርኛንም እንዲማር ማድረግ ሲገባ፣ ኦሮምኛ ብቻ ተምሮ አማርኛ እንዳይማር በመደረጉ፣  ጉዳት ደርሶበታል፡፡

ኦሮሞ አገልግሎት በኦሮምኛ ያግኝ በሚል የክልሉም፣ የዞኖንና ወረዳዎች፣ ከተሞችም የስራ ቋንቋ ኦሮምኛም አማርኛ ማድረግ ሲገባ፣ ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆን በመደረጉ፣ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖች  ተገፍተዋል፡፡ ያም ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑ ባለሃብቶች ሃባታቸውን ይዘው እንዲወጡ አድርጓል፡፡ ሌሎች ባለሃብቶችም ወደ ኦሮሞ ክልል የመሄድ ፍላጎታቸውን ቀንሷል፡፡ ይሄም በኦሮሞ ክልል በብዙ ቦታዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጓል፡፡

ለዚህም ነው እነ መቱ፣ ነቀምቴ፣ ጂማ፣ ጎባ ወዘተ ከእርሻ ማሳዎችን ከማሳየት በቀር ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ቱሪዝዝም ወዘተ  ብዙ የማይታይባቸው፡፡ ለዚህ ነው የኦሮሞ ወጣትም ስራ ፍለጋ ወደ ሸገር የሚመጣው ?????? ለምን በአካባቢው ስራ የሚፈጥርለት  ስለሌለ፡፡

በኔ እምነት ኦሮሚያ የሚባል ክልል መፈጠሩ ፣ ለጥቂቶች  የኦሮሚያ ክልል እንወክላለን ለሚሉ፣ በኦሮሞ ስም አዲስ አበባና ናዝሬት ተቀምጠው ብዙ ጥቅም እያገኙ ላሉ  ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በስተቀር ፣ ለተራው ኦሮሞ ምንም የፈየደለት ነገር የለም፡፡  ላለፉት ሰላሳ አንድ አመታት ፣ በተለይም ላለፉት አራት አመታት ኦሮሞ፣ ከሰላሳ አንድ አመት በፊት ከነበረው ሁኔታ በጣም በባሰ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡

እስቲ አንዲት ምሳሌ ላቅርብ፡፡ ላለፉት አራት አመታት በኦነግና በኦህዴድ መካከል እየተደረገ ባለው የስልጣን ጦርነት፣ በግማሹ የኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ፍዳዉን እየበላ ነው፡፡ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች ታስረዋል፣ ታፈነዋል፡፡ ከ6 ሺህ በላይ ተገድለዋል፡፡  ከዚያ በፊት ለ27 አመታት ኦነግ ናችሁ በሚል እስር ቤቶች የተሞሉት በኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ በደርግ ጊዜ ያ ነበ? በንጉሱ ጊዜ ያ ነበር ???

ይሄን ሁሉ ያደርገው፣ የአማራ ማህበረሰብ፣ ወይንም ፋኖ፣ ወይንም እምዬ ሚኒሊክ ከሞት ተነስተው አይደለም፡፡ ኦሮሞ ስቃዩን እየበላ ያለው በዘረኛው የኦሮሙማ አጥፊና ጎጂ ፖለቲካ፣  ኦሮሞን እንወክላለን በሚሉ የኦሮሞ ፖለቲካ ነጋዴዎችና የኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቴክኞች ነው፡፡

Filed in: Amharic