>

ፖሊስ የባልደራሱ ኩራባቸው ገብሬን ሁከት በማስነሳት በሀሰት ወነጀለ

ፖሊስ የባልደራሱ ኩራባቸው ገብሬን ሁከት በማስነሳት በሀሰት ወነጀለ
ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 3 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
ጌጥዬ ያለው

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አባል የሆነው ወጣት ኩራባቸው ገብሬ ትናንት አርብ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ ፖሊስ ታፍኖ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ማለትም የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስዷል። ኩራባቸው ዛሬ ቅዳሜ፤ ግንቦት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ከጠበቃው ቤተማርያም አለማየሁ ጋር በአካል ቀርቧል።
በችሎቱ ከሳሽ የአዲስ አበባ ፖሊስ በአፋር፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች የአማራ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የሀሰት ውንጀላ አቅርቦበታል። “ተነሳ” ያለውን ሁከትና ብጥብጥ ያልገለፀው ፖሊስ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።
ፖሊስ የባልደራስ አባላትን በወል ውንጀላ በተደጋጋሚ እያፈነ እንደሚያስርና ኩራባቸውም በዚሁ ምክንያት የፖሊስ ኢላማ ሆኖ በተደጋጋሚ በሀሰት መታሰሩን የገለፁት ጠበቃ ቤተማርያም አለማየሁ ተከሳሹ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብቱ ተጠብቆ ከእስር ቤት እንዲወጣና በውጭ ሆኖ እንዲከራከር ጠይቀዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የስድስት ቀና የምርመራ ጊዜ የፈቀደ ሲሆን ለፊታችን ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ኩራባቸው ገብሬ በአድዋና በካራማራ የድል በዓላት ምክንያት በግፍ በአባ ሳሙኤል እስር ቤት ታስሮ ቆይቶ መፈታቱ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀደም ሲል ለእያንዳዳቸው በ8 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በእስር ፍ/ቤቱ የተወሰነላቸው 17 ወጣቶች ውሳኔው ውድቅ ተደርጎባቸዋል። በፖሊስ ጥያቄ መሰረት ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ነው ውድቅ ያደረገው። በማንኛውም የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀጠሮ የሚሰጠው ቢበዛ 14 ቀናት ብቻ እንደሆነ በሕግ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ የእስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሻረው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በሕገ ወጥነት የ16 ቀናት ቀጠሮ ሰጥቷል።
Filed in: Amharic