>
5:13 pm - Monday April 19, 4354

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  የዛሬው ግንቦት 29/2014 የፍርድ ቤት ውሎ ...!!! (ታሪኩ ደሳለኝ)

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ 

የዛሬው ግንቦት 29/2014 የፍርድ ቤት ውሎ …!!!

ታሪኩ ደሳለኝ


መርማሪ ፖሊሶቹ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የጠረጠሩበትን  የክስ ጉዳይ ለማጣራት “ተጨማሪ 14  ቀን ይሰጠን ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅረበዋል”

ግንቦት 19/2014 በዋለው የመጀሪያው ቀን ችሎት፣ ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

“ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በዩቱብ ኢንተርቪዎችን በመስጠት ቀስቅሷል” በሚል እንደሚጠረጥረው መግለፁ ይታወሳል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ፖሊስ ደንበኛቸውን የጠረጠረበት መንገድ ተጨባጭነት እንደሌለው፣ ደንበኛቸው ላለፉት አራት ዓመታት በዩትዩብ ምንም ዓይነት ኢንተርቪው ሰጥቶ እንደማያውቅ ለችሎቱ በማስረዳታቸው ፖሊስ የቀደመ የክስ ሀሳቡን ለመተው ተገዷል።

መርማሪ ፖሊሶቹ  በዛሬው ግንቦት 29/2014 በዋለው ችሎት “ዩቱብን ወደ ፍትሕ መፅሔት ቀይረው “ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ ፅሁፎችን በፍትህ መፅሔት ይጠቀማል” ብለዋል።

የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ “ከመጀመሪያው ጀምሮ በዩትዩብ በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ይስራል ለዚህም የሰነድና የሰው ማስረጃ አለኝ ብሎ ይሄን ሁሉ ቀን የወሰደ ቢሆንም ፖሊስ፦ ሰነድም፣ ማስርጃም፣ ማቅረብ አልቻለም ይልቁን ወንጀል ፍለጋ ዛሬ ዩቱዩብን ትቶ በፍትሕ መፅሔት በመጠቀም የሚል አዲስ ክስ ይዞ ቀርቧል። ፍርድ ቤቱ፣ ፖሊስ  ከዩትዩብ ወደ መፅሔት የዞረበትን ሁኔታ ተመልክቶ አዲስ ክስ እንዳይቀበለውና ተመስገንን በዋስ እንዲያሰናብተው ጉዳዩንም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንዲመለከተው እንጠይቃልን” በማለት ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ ይሄንና በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ስለ ተፈፀመው ድብደባና የሰብዓዊ አያያዝ ጉድለት በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ግንቦት 30/2014 ጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል::

የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013

አንቀፅ 86 (1) “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ክሱ በቀጥታ ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት።” ይላል።

ኾኖም ግን ፖሊስ፣ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ከአዋጁ አግባብ ውጭ ለሁለተኛ ጊዜ፣ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆበታል። በተመሳሳይ በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ አያያዛቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ሕጉ ቢያስቀምጥም፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፖሊስ መደብደቡ ይታወሳል።

ቤተሰቦቹና የፍትሕ መፅሔት ባልደረቦች

Filed in: Amharic