>
5:18 pm - Saturday June 16, 8485

አማራዊነት ያሸንፋል፤ ኢትዮጵያም በልጆቿ ትነሣለች! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

አማራዊነት ያሸንፋል፤ ኢትዮጵያም በልጆቿ ትነሣለች!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


እንግዲህ “ሽልም ከሆነ ይገፋል፤ ቂጣም ከሆነ ይጠፋል” እንዲሉ ሆነና ሽሉም ገፍቶ ቂጣውም ጠፍቶ የምናይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ጊዜ መስታዎት ነው፡፡ ሁሉን ያሳያል፡፡ የነበረ እንዳልነበረ፣ ያልነበረም እንደነበረ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ በአንድ ጉባኤ አርባ ጊዜ “ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ” እያለ የኢትዮጵያ ስም በመሪዎቿ አንደበት መጠራት የብርቅ ያህል ይናፍቀው ለነበረ ሕዝብ የዓዞ ዕንባውን ይረጭ የነበረው ይሁዳም እውነተኛ ይሁዳዊ ማንነቱን አሳይቶ ኢትዮጵያን በመሳም ለጠላቶቿ አሳልፎ ሸጧታል፡፡ ባህር ዳር ላይ ሄደው “ኢትዮጵያ ሱሴ”ን የዘመሩ ሁሉ ዝማሬያቸው ለተወሰነ ጊዜ ብዙ ፍሬ ቢያስገኝላቸውም የመጨረሻ ዓላማቸው በመገለጡ ግን አሁን ተነቅቶባቸዋል፡፡ የኦሮሙማው ኢምፓየር አጋፋሪ አቢይ አህመድ፣ ሆዳምና ነፈዝ አማሮችን በገንዘብና በማይሠሩበት ሽርፍራፊ ሥልጣን እየደለለ አጃቢዎቹ አድርጎ ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ከቀን ተግቶ ሠርቷል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የት እንዳለ እንኳን በውል የማያውቅን ገዱ አንዳርጋቸውን “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” አድርጎ እንደመሾም ያለ ዐይን አውጣነትና አስመሳይነት በዓለማችን ታይቶ አያውቅም – እኔማ የዚህ ሰውዬ ምትሃታዊ ተግባራት ከማስገረም አልፈው ያስቁኛል፤ የሚያምነው ሰው ደግሞ መሙላቱ፡፡ ይህ ሰውዬ የሚመራት ሀገር ዜጋ መሆን በራሱ በእጅጉ ያበሳጫል፡፡ ይህ ልጅ በርግጥም ከታችኛው ዓለም ስለመላኩ መጠራጠር አይገባም፡፡ ለዚሁ እርኩስ ዓላማው ስኬት ሲል ቤተሰቡን እስከመበተን በደረሰ ጭካኔና ኢሞራላዊነት የ120 ሚሊዮን ሕዝብ የጋራ እናት የሆነችን ሀገር በጣጥሶ ለመጣል የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ግን አይሳካለትም፡፡ ኢትዮጵያ የተለዬች ሀገር ናት፡፡ ታሪክን ጎብኙ፡፡ እንጎብኝ፡፡ 

አሁን ኢትዮጵያ የመዳን ዕድሏ – እውነቱን ለመናገር – በአማራው እጅ ውስጥ ይገኛል፡፡ አማራዊነትና ኢትዮጵያዊነት ተወራራሽ ስለመሆናቸው ብዙ ጊዜ ይወሳል፤ ምክንያቱም አማራዊነት ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ባለፈ ወደጎጥና ሸጥ ወርዶ አይወተፍም፡፡ ይህም እውነት ባለፉት ሦስትና አራት አሠርት ዓመታት በገሃድ ታይቷል፡፡ ወደፊትም ከዚህ የተለዬ ነገር አይኖርም፡፡

ሰፊው የአማራ ሕዝብ በተሠራበት ደባ ምክንያት እስካሁን ድረስ አፉንም ክንዱንም ፀጥ ረጭ አድርጎ እየሆነ ያለውንና ሲሠራበት የነበረውን ግፍና በደል ሁሉ በዝምታ ሲመለከት ቆይቷል፡፡ ይህን ዝምታውን እንደፍርሀት የቆጠሩት ወገኖች በደስታ እየፈነጠዙ አማራውን እደጁ ድረስ ሄደው አንገቱን እየቀሉት ነው፤ ንብረቱን እያወደሙና ዘሩንም እያመከኑት ነው፡፡ ግፍ ሲበዛ ከተኙበት መባነን ያለና የነበረ ነውና አሁን አማራው ለማንም ወደማይመለስበት ደረጃ እየተቃረበ ነው፡፡ ግን አሁንም ቢሆን ገና ነው፡፡ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህ ሥራ ደግሞ በአማራው በራሱ ብቻ ሳይሆን ይበልጡን በጠላቶቹ እየተሠራ ነውና አማራው መንቃትና ማምረርም ጀምሯል – ቢዘገይም ጥሩ ነው፡፡ ለወትሮው “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” የሚል ብሂል የነበረው አማራ የነካው ሳይታወቅ ለበርካታ አሠርት ዓመታት የጠላቶቹ ሰለባ ሆኖ ከርሟል፡፡ በዚያም ምክንያት ከስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የወጡ ወሮበሎች የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው በአርባና ሃምሳ ሚሊዮኑ አማራ ሲዘባነኑበትና መከራ ፍዳውን ሲያሳዩት ታዝበናል፡፡ ይህ ትግስትም ፍራቻም ሊባል የሚከብድ ታራካዊ አጋጣሚ እንዴት እንደተከሰተ ታሪክ ራሱ ይድረስበት፡፡ ግን ግን እውነት ነው – “የናቁት ያደርጋል ራቁት!”

የአሁኑ ይባስ ደግሞ በርግጥም የአሁኑ ይባስ ሆኗል፡፡ ኦሮሙማዎች እጅጉን ታውረዋል – “ኦሮሞዎች” አላልኩም!! ማንም ጠግቦ በማያውቀው ደረጃም ጠግበዋል፡፡ በዚያም ምክንያት አይነጋ መስሏት ወፍጮዋን እንዳበላሸችው ሴት ሆነዋል፡፡ ይህ ለወደፊቱ የአብሮነት ሕይወት አሳዛኝ ጠባሳ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ጥጋብን መቆጣጠር የአንድ ሰውም ይሁን የአንድ ድርጅትና ቡድን የመጀመሪያ ኃላፊነት መሆን ሲገባው ኦሮሙማዎች ግን ለታዛቢ እስከሚያስደነግጥ ድረስ ጥጋባቸውና ዕብሪታቸው ለከት አጥቶ ይሠሩትን ቀርቶ ይናገሩትን አሳጥቷቸዋል፡፡ አንዳንዴ ለነሱም አዝናለሁ፡፡ “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” መባሉም እኮ ለዚህ ነው፡፡

ለዚህ ጥጋባቸው ግን ተጠያቂው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ እዚህ ላይ አማራ ትግሬ ኦሮሞ ማለት አያስፈልግም፡፡ በዘር የማያምን፣ በጎሣዊ የነገድ ልክፍት ያልተጠቃ፣ በሃይማኖትና በመሳሰለው ልዩነት ያልተመረዘና ራሱን ከፍ ሲል እንደሰው – ዝቅ ሲልም እንደኢትዮጵያዊ የሚቆጥር ማንኛውም የዚህች አገር ዜጋ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህን የወል ስሜት ያጠፉት ወያኔና ኦነግ/ኦህዲድ ናቸው፡፡ ከዚህ በመለስ በቋንቋውና በነገዱ የሚኮፈስ ቢኖር ከሰው ተራም የሚገባ አይደለምና መጥፋት ያለበት አራሙቻ ነው፡፡ አማራን እስካሁን አቆርቁዞ ያቆየው እንግዲህ እንደሌሎች ወርዶ በአማራነቱ አለመደራጀቱ ነው፡፡ ይህም ለበጎ ነው፤ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ አማራም እንዳንዳንድ ነገዶች  ኢትዮጵያዊነቱ ያከትምና ወይም በእጅጉ ይቀዘቅዝና ሀገራችን ወደማትወጣው ችግር ትገባ ነበር፡፡ ትልቅ መሆን በትንሾች ያስጠቃል፡፡ ትልቅ ሆነህ ትንሽ ልሁን ብትል ትኅትናህን እንደፍርሀት ይቆጥሩና ይበልጥ ያላግጡብሃል፡፡ ለአብነት የአርባ ዓመት ጎልማሳን የአምስት ዓመት ታዳጊ ጮርቃ በሣማ ቢገርፈው ትልቁ ይሸሻል እንጂ አይገጥመውም፤ ለተመልካች ፍርድም ያስቸግራልና እንዲህ ያለ ነገር አያድርስ ነው፡፡ እንጂ የአራትና አምስት ክፍለ ሀገር ሕዝብ – መለያየቱና ከዘረኝነት መጽዳቱ ለጠላቶቹ የጥቃት ዒላማነት እንዳመቻቸው በታሳቢነት ተይዞ – አስተባባሪና ጥሩ አመራር ቢኖረው ኖሮ ወያኔም ሆነ ኦነግ/ኦህዲድ ባልተጫወቱበት፣ ሀገሩንም ለጊዜውም ቢሆን ባልበታተኑበት ነበር፡፡ ግዴለም፡፡ ይሁን፡፡ መሆን ያለበት ይሆናልና ላለፈው አንቆጭ፡፡ ስላለንበትና ስላለፍነው ጨለማ ሳይሆን ስለወደፊቱ ብርሃን እናስብ፡፡ ኢትዮጵያ ወደነበረው ክብሯ ትመለሳለች፡፡  

ወንድሞችና እህቶች ሆይ! የወደፊቱ አያሳስባችሁ፡፡ ጠላቶቻችን ከደገሱልን የዕልቂት ብፌ ይልቅ ፈጣሪያችን ያዘጋጀልን የነፃነት ወርቃማ የብርሃን ቀንዲል ይበልጣል፡፡ ነገ ነገር ሁሉ በጎ ይሆናል፡፡ ነገ መልካም የሚሆነው ግን ስለተመኘን ብቻ አይደለም፡፡ የክፉዎች መጨረሻ በምድርም ሆነ በሰማይ ስለማያምር እንጂ የታሰርንበት የእሳት ሰንሰለት በራሱ ለቆን ስለሚጠፋ አይደለም፡፡

አሁን ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ የሚታይበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብያለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ገና ለ30 እና 40 በመቶ ለምንሆነው ዜጎች ነው፡፡ ቀሪው አሁንም ገና ዳፍንት ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ የጠላቶቻችን ፍጥነት በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ችግሩ ሲከሰት ሁሉም ይባንናል፡፡ በናቡከደነፆር አቢይ አህመድ ግራኝና በሂትለር ሽመልስ አብዲሣ ተመልምሎ በመቶ ሽዎች የሰለጠነው ኦነግ-ሸኔ አዲስ አበባ ገብቶ በየበርሽ በጥይት ሲቆላሽ ያኔ እያንዳንድሽ የዛሬ ጩኸታችን ይገባሻል፡፡ ያኔ ነው ጉዱ፡፡ አሁንም አዳሜ ለሽ ብለሽ ተኚ፡፡ “የሚፈለገው ፋኖ እንጂ እኔን ማን ይፈልገኛል” እያልክ እንደከብት ያገኘኸውን እያመነዠክህ የምትተኛ ሁሉ የምትተርፍ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ ዛሬ የጎረቤትህን በር ያንኳኳ ችግር ነገ ያንተንም ያንኳኳል፡፡ ዘረኝነት ደግሞ ዳፋው ለሁሉም ነው፡፡

የዕንቁራሪቶቹን ታሪክ ላስታውስህ፡፡ አንድ ኮረብታማ ላይ በነበረ መንደር ውስጥ እሳት ይነሳል፡፡ የአካባቢው ሰው ተረባርቦ እሳቱን ለማጥፋት በኅብረት ይነሳል፡፡ በዚያ ጥረታቸው የየቤቱ ውኃና አፈርን ጨምሮ ቅጠላ ቅጠል ሁሉ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚያን ወቅት ታዲያ ከመንደሩ ዝቅ ብሎ ይገኝ በነበረ አንድ ኩሬ ውስጥ ከሚኖሩ ዕንቁራሪቶች አንዷ ቀበጥ ዕንቁራሪት በሚቃጠለው ቤትና እሳቱን በሚያጠፉት ሰዎች እያላገጠች ታንቋርር ያዘች፡፡  ከዚያም የዚህች ቀበጥ ዕንቁራሪት እናት ትሁን አክስት “ኧረ ተይ አንቺ ልጅ ግፍ አትሥሪ! አያድርስ ከማለት በሰው ታሾፊያለሽ?” በማለት ትገስጻታለች፡፡ እርሷም መልሳ “እኔ ምን እሆናለሁ? ያለሁት ውኃ ውስጥ” ትላታለች፡፡ እሳት አጥፊዎቹ የአካባቢያቸውን ማቴሪያል ተጠቅመው እሳቱን ማጥፋት ባለመቻላቸው ቅል ያለው ቅሉን፣ ባልዲ ያለው ባልዲውን፣ እንሥራ ያለው እንሥራውን ይዞ ውኃ ለመቅዳትና እሳቱን ለማጥፋት ወደዚያ ኩሬ ይወርዳል፡፡ ሌሎች ዕንቁራሪቶች ወደታች ወርደው  ሲደበቁ ያቺ በሰዎቹና በእሳት ቃጠሎው እየተዝናናች ታሾፍ የነበረች ዕንቁራሪት በአንደኛው እንሥራ ውስጥ ተጠልፋ እሳት ማጥፊያ ሆነች፡፡ የቀባጭ ምሷን በማግኘቷ እስከወዲያኛው አንቀላፋች፡፡ ነፍስ ይማር አይባል ነገር፡፡ በኔ አይደርስም ብሎ በሌሎች ስቃይና መከራ መቀለድና ማሾፍ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከዚህ ታሪክ መማር አግባብ ነው፡፡

ለማንኛውም እነአቢይ መግቢያ ቀዳዳ የሚያጡት ሁሉም ነቅቶ ወደአልሞትባይ ተጋዳይነት ሲለወጥና ላለመሞት መላው ዜጋ ነብር ሲሆን ነው፡፡ አሁን ባለው አጠቃላይ የከተሞች ሁኔታ ካየን ግን የኦነግ/ኦህዲድ ዓላማና ፍላጎት ብዙ ሰው የገባው አይመስልም፡፡ ኦነግ/ኦህዲዶችም ዛሬና አሁን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነላቸው መስሏቸዋል፡፡ በዚያም ምክንያት አማራ የተባለን ሁሉ እያፈኑ ወደማይታወቁ ሥፍራዎች ወስደው እያጎሩ ነው፡፡ የአማራ ክልል ኦሮሚያ እስኪመስል ድረስ የኦሮሞ ልዩ ኃይሎችን እያሰማሩ አማራ የተባለን ሕዝብ እያሰቃዩ ነው፡፡ ጥሩ፡፡ በዚሁ ይቀጥሉ፡፡ ብአዴንም ትብብሩን ይቀጥል፡፡ የቀባጭ ምሳቸውን ማግኘታቸው ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀር የሰማይና የምድር ፍትኃዊ ፍርድ ነው፡፡

ወገኖቼ የናቁት ወንድ ያስረግዛል፤ ይህንን እውነት ይበልጥ እንገነዘብ ዘንድ በሀገራችን ብዙ ሆነ፡፡

በኢትዮጵያ ምድር መናናቅ ትልቁ ባህል ነው፤ አስጠሊታ ባህል፡፡ የመናናቅ ውጤት ግን እንዳየነው ሀገርን እስከማፍረስ ይደርሳል፡፡ ጉንዳን እንኳን ሱሪ ታስወልቃለች፡፡ ዓለም የናቃት ጽዮናዊቷ  እስራኤል በጥቅሉና በዓለም ዙሪያ ጭምር 18 ሚሊዮን አካባቢ የሚገመት ሕዝብ ይዛ ዓለምን በቁጥጥሯ ሥር እንዳደረገች ለምንረዳ የተናቀ ማስረገዙን በቀላሉ እናስተውላለን፡፡ 

ሰባት ሰባራ ክላሽ ይዘው የተነሱ ወያኔዎች “ምንም አያመጡም” እየተባሉ ሲናቁ ከርመው ታላቁን የምሥራቅ አፍሪቃ መንግሥት ገለበጡ፡፡ እነዚያ ጥቂት ወያኔዎች ብዙውን አማራና ኦሮሞ እንዲሁም ሌላ ነገድ ለ27 ዓመታት እንደሰም አቅልጠው እንደብረት ቀጥቅጠው ገዙ፡፡ አዎ፣ “የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል” ነውና ምድርና ሰማይ የማይችሉትን ወንጀልና የክፋት ሥራ በተለይ በአማራው ላይ አድርሰው እነሱም በተራቸው ሒሣባቸውን አገኙ፡፡ ገናም ያገኛሉ፡፡ የሙሽቱን ቀምሰዋል፤ ዋናው ይቀራቸዋል፡፡

ከነሱም በፊት እዚህ ግባ የማይባል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የተባለ የመስመር መኮንን በመፈንቅለ መንግሥት ወደሥልጣን ወጥቶ ሀገራችንን ለ17 ዓመታት በዕውር ድምብር ሲገዛ ቆዬ – ልክ እንደአቢይ አህመድ ሁሉ ሥልጣኔን ይቀናቀናሉ ብሎ የሚጠራጠራቸውን የተማሩና የበቁ ዜጎችን ሁሉ በጥይት እያጨደ፡፡ ጓደኞቹ ከአካባቢያችን ይራቅ ብለው በኮሚቴነት መርጠው የላኩት ያ ሰው ድንገት ሳይታሰብ ላይ ወጣና ሀገርን መቀመቅ ከተተ፡፡ ቁጭ ብለን የምንሰቅለው ሁሉ ቆመን ማውረድ እያቃተን ብዙ ጊዜ ጉድ ተሠራን፡፡ ያ ሰው ልክ እንደኔ አሁን ድረስ ለጉድ ጎልቶት እዚህ ግባ የማይባል መሽረፊት(ማራገቢያ) ሻጭ ሀገርን እንደከብት እየገረፈ ሲነዳ ለማየት በቃ፡፡ በመሠረቱ መሽረፊት መሸጥ ነውር ሆኖ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ቤተሰባዊ አስተዳደግም ትልቅ ስንሆን በሚኖረን የስብዕና ይዘትና ጥራት ወሳኝ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ለሀገር አመራር አስተዳደግና ሃይማኖታዊ የሞራል ዕሤቶች ዳራ ወሳኝ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ የዐይኑን ቀለም የሚጠላውን ዜጋ ሁሉ ባልተወለደ አንጀት በጥይት የሚቆላ ዐረመኔ መሪ፣ መሪ ሊሆን አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ ሀብታም ሀገር ናት፡፡ ሰው አላጣችም፡፡ ግን ሾተላይ አለባት፡፡ ሊጠቅሟት የሚችሉ ልጆቿን ቅርጥፍ አድርጋ እየበላች ከይሲዎቹን ወደላይ ታወጣለች፡፡ ያኔ ሀገር ትጫጫለች፤ ሕዝብም ይጎሳቆላል፡፡ ያደላቸው ሀገራት ሕዝባቸውን በቀን አምስትና ስድስቴ ከመመገብ አልፈው ተረፈ ምርታቸውን ለባህር ዓሣዎች ይደፋሉ፤ ለድሃ ሀገራትም ይልካሉ፡፡ የኛዎቹ እርጉማኖች ግን በቀን አንዴም መመገብን ይከለክሉንና ከሰው በታች ያደርጉናል – እነሱ እየጠገቡ፡፡ ይህን መሳይ ድሃ ሕዝብ መምራት እንዴት እንደሚያረካቸው ባላውቅም እነዚህ ሰዎች የሌሎች ሀገራትን የሕዝብ አስተዳደር ጥበብና ችሎታ መረዳትና ራሳቸውን ከዓለም ጋር ማስተካከል የማይፈልጉ በመሆናቸው ሥነ ተፈጥሯቸውን ለማወቅ በጣም እጓጓለሁ፡፡ መቼም ቢሆን እነዚህ ሰዎች – ሰዎች ማለት ከተቻለ ነው ለዚያውም – ጤነኛ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ የተራበንና የተጎሳቆለን ሕዝብ መምራት እንዴት ሊያኮራ ይችላል?

ለማንኛውም መጪውን ዘመን መልካም የነጻነት ዘመን ያደርግልን፡፡ አማራው በርታ፡፡ የኢትዮጵያ ፋኖ በርታ፡፡ በነገራችን ላይ ከጨለማው የአቢይ አህመድ ትብታባም የዲያቢሎስ መንግሥት የሚወጡ ዜጎችን አናሸማቃቸው፤ በፍቅር እንቀበላቸው፡፡ ከጥፋት ወደ ልማት ለመመለስ የጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ዋናው ክልብ ተፀጽቶ መመለሱ ነው፡፡ ስለሆነም ከክፋትና ከድግምታዊ አንደርብ  በየትኛውም ጊዜ ቢሆን ነጻ መውጣት ይቻላልና እነሱን ማሳቀቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እርግጥ ነው – ከአቢይ ጎራ የሚኮበልሉ ወገኖችን የሚነቅፉ ሰዎች በጠላት ወገን የሚላኩ ተከፋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠራጠር አይከፋም፡፡ በትግል ወቅት አጋዥ አይጠላም፡፡ እውነት መሆኑን ግን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ለአፍራሽ ተልእኮ ከመጡ ችግር ነው፡፡ ውስጥን ማጥራት እንዳለ ሆኖ አዳዲስ መጪዎችን ጤናማነታቸውን ማጣራት መጥፎ አይደለም፡፡ በተረፈ በኔ ይሁንባችሁ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!! በቅርብም ነጻ እንወጣለን፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ እንኳን ከፎከረ ከወረወረም ያድናልና በዚህ አንጠራጠር፡፡ ይሁንና – ልድገመው – ይሁንና በከተሞች በስፋት የሚታየው ሶዶም ወገሞራዊ አስረሽ ምቺው እንዲቀር፣ ከቤተ መንግሥትና ከቤተ አምልኮቶች ጀምሮ ከላይ እስከታች በምዕራባውያን የተዘረጋው የሴቴኒዝም እምነት እንዲጋለጥና ሕዝባችን ከጥፋትና ከሙስና እንዲታቀብ አጥብቀን እንጸልይ፡፡ ሀገራችን የቀራት ብቸኛ የነጻነት መንገድ ፈጣሪ ነውና ሁላችንም ከየገባንበት የክፋት አዘቅት ወጥተን ወደላይ እንጩህ፡፡ ይህን የምለው በነፃነታችን መምጣት ተጠራጥሬ ሳይሆን የመከሰቻው ጊዜ እንዲያጥርና በቶሎም እንዲመጣልን ከማሰብ አንጻር ነው፡፡ እንጂማ ዐውሬው አንገቱ ሊያዝ የቀረው ጊዜ በጣም ትንሽ  ነው ፡፡ ምኞት አይደለም፤ እውነት ነው፡፡ በጣም የተንቀዠቀዠውም ዘመኑ አጭር መሆኑን ስለተረዳ ነው፡፡….


 

Filed in: Amharic