>

ስለ አስጨናቂ (ስንታየሁ) ቸኮል ጥቂት አንቀጾች..??? (ጌጥዬ ያለው)

ስለ አስጨናቂ (ስንታየሁ) ቸኮል ጥቂት አንቀጾች..???

ጌጥዬ ያለው


አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ ጎንን ማሳረፊያ ፍራሽ፣ መታጠቢያ ውሃ እና ዓይንን መክፈቻ መብራት በሌለው ተባያማ  ክፍል ውስጥ ታጉሮ እንደሚገኝ ሰምቻለሁ። ይህንንም በመቃዎም የርሃብ አድማ ላይ ነው።

አዲስ አበባ በ1993 ዓ.ም. ወያኔን አሽቀንጥራ ለመጣል የፖለቲካ ለብታ ላይ ነበረች። ለ1997ቱ ግለት እየተዘጋጀች ነበር። ስንታየሁ ቸኮል በዚህ ወቅት ከአብዮት ቅርስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ገባ። ፓርቲው በወቅቱ በዶ/ር አድማሱ ገበየሁ መሪነት ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። ስንትሽ የወረዳ 20 አመራር አባል በመሆን በልጅ እድሜው ከወያኔ ሀገር አፍራሽ በትር ጋር ተናንቋል። በተለይም ፓርቲው በሚያደርጋቸው ሕዝባዊ ቅስቀሳዎች ላይ ከፊት ነበር። ከዚህ በኋላም በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ እየታገለ መጥቷል።

በ1997 ዓ.ም. በቅንጅት ውስጥ አዲስ አዲስ አበባ ላይ ጥሩ ውጥት እንዲገኝ ካደረጉ የቅንጅቱ አባላት መካከል አንዱ ነው።

በዘጠና ሰባቱ ምርጫ የተዘረረው ወያኔ ስንታየሁ ቸኮልን በ1998 ዓ.ም. ለስምንት ወራት ያህል በዝዋይ ወህኒ ቤት አጉሮት ቆይቷል። ወያኔ ለዚህ ሁለት ምክንያቶች አሉት። አንደኛው መጀመሪያውኑም በምርጫው እንዲሸነፍ ካደረጉት ታጋዮች መካከል ስንትሽ አንዱ መሆኑ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የምርጫውን ውጤት መገልጡን ተከትሎ አገዛዙ ለገጠመው ሕዝባዊ ቁጣ አንዱ ወጣቱን ቀስቃሽና አደራጅ መሆኑ ነው።

በ2001 ዓ.ም. አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሲቋቋም መስራች አባል ነበር። የአዲስ አበባ ወጣቶች ተጠሪ በመሆንም እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ታግሏል።

ይህ ሁሉ ሲሆን እስር አልተለየውም። ከዘጠኝ ጊዜ በላይ በማዕከላዊ፣ በሸዋሮቢት እና አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስሯል። ሕዝባዊ ቁጣው በጋለ ቁጥር ወያኔ ቀድሞ ከሚያስራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ስንትሽ ነው።

በተለያዩ ምክንያቶች አንድነት በደከመ ጊዜም በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ሰፊ የትግል አስተዋፅኦ አድርጓል።

ስንታየሁ ቸኮል በወራሪው የኦሮሙማ አገዛዝም ብዙሃኑ በሚያውቀው መልኩ ይኸው ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ በሽብር ተከሶ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በቃሊቲ እና ቂሊንጦ ሲታሰር በከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ይቀርቡበት ከነበሩት ክሶች መካከል አንዱ “ከንቲባ ታከለ ኡማን ማስጨነቅ” የሚል ነው። የእርሱም መልስ “ኦሕዴድ-ብልፅግናን ማስጨነቅ ሥራዬ ነው” የሚል ነበር። ይህንን የሰማው የችሎት ታዳሚ ከዚህ ዕለት ጀምሮ አስጨናቂ ቸኮል እያለም ይጠራዋል።

 

ስንትሽ በአሁኑ ጊዜ በባሕር ዳር 1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታግቶ ይገኛል። በዚያ ፍርድ ቤት እንኳን ሳይቀርብ በአደራ እስረኛነት ከታጎረ ዛሬ 12ኛ ቀኑ ነው ነው። እየደረሰበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሀብ አድማ እያደረገ ይገኛል።

ከ/ፍርድ ቤት በጋዜጠኞቹ ጉዳይ የቀረበለትን ይግባኝ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐሙስ  ቀጠረ…!!!

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ መዓዛ መሐመድ እና ሰለሞን ሹምዬ ላይ የቀረበውን ይግባኝ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ሐሙስ ሰኔ 2፤2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ችሎት፤ ለሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደው ዋስትና ውድቅ እንዲደረግ እና 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የፖሊስ ኮሚሽኑ መርማሪዎች በዛሬው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተጠረጠረበት “ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት” ወንጀል ወደ “ሽብር ወንጀል” ሊቀየር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። መርማሪዎቹ ይህን ያሉት ተመስገን የተጠረጠረበት ወንጀል ውስብስብ መሆኑን ለፍርድ ቤት ባስረዱበት ወቅት ነው።

መርማሪ ፖሊሶቹ ተመስገንም ሆነ ሌሎቹ ሁለት ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል “ውስብስብ፣ በሀገር ላይ እና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ ጠቅሰዋል። ከዚህ አንጻር ምርመራው “ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ” በመሆኑ እና ምርመራውን በስፋት እስኪያጣሩ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው የስር ፍርድ ቤት መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 30፤ 2014 በዋለው ችሎት ለእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የ10 ሺህ ብር ዋስትና መፍቀዱን እንደሚቃወሙ መርማሪዎቹ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ገልጸዋል። መርማሪ ፖሊሶቹ የምርመራ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ይረዳቸው ዘንድ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የፖሊስን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ አጥብቀው የተቃወሙት የተጠርጣሪ ጠበቆች፤ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን የዋስትና ትዕዛዝ እንዲያጸና ጥያቄ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ይግባኝ እና የጠበቆችን ምላሽ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ሐሙስ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል።

Filed in: Amharic