ጸረ ሰሜን ኢትዮጵያ የኦህዴድ/ ብልጽግና የባጀት ቀመር…!!!
ግርማ ካሳ
የአብይ አህመድ ኦህዴድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለክልሎች የሚመድበውን የባጀት ድጎማ ይፋ አድርጓል፡፡
የኦሮሞ ክልል ባጀት ከ69 ወደ 71 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋ፣ የሲዳማ፣ የሃረሬ፣ የጋምቤላ ባጀቶች ብዙ አልተለወጡም፡፡
እዚህ ጋር ጥቂት ነጥቦችን ላስቀምጥ፡፡
1ኛ የትግራይ፣ ደቡብ ፣ የአፋርና የአማራ ክልል ብዙ ጥፋት ያስከተለ ጦርነት የተደረገባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ መልሶ ለማቋቋም ያስፈልጋል ብሎ ነበር፡፡ በመሆኑም ለነዚህ ሶስት ክልሎች እጅግ በጣም ከፍ ያለ ባጀት መመደበ ነበረበት፡፡ ቢያንስ ለዚህ አመት፡፡ ያ አለመሆኑ እጅግ በጣም አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ነው፡፡ ከሌሎች ክልሎች ተቀንሶ ወደነዚህ ክልል ገንዘብ መመደብ ነበረበት፡፡ የአብይ መንግስት ያንን አለማድረጉ የሰሚነ የኢትዮጵያ ግዛት እንደ ደኸየ፣ እንደ ወደቀ እንዲቀር፣ ደካማ ሆኖ እንዲቀጥል ከመፈለግ የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰሜን ከተዳከመ ለስልጣናችን ስጋት አይሆንም ከሚል፡፡
በፊት የሶማሌ ክልል ባጀት ከትግራይ ክልል እኩል ሲሆን በሕዝብ ብዛት ለትግራይ 12 ቢሊዮን ብር ሲመደብ፣ ለሶማሌ ክልል እጥፍ መመደቡ፣ በሶማሌ ክልል ለረጅም ጊዜ አለመረጋጋት ስለነበረ ብዙ ስራዎች እዚያ መሰራት ስለነበረባቸው ነው በሚል ይሁን ብለን ነበር፡፡ አሁን ግን ከሶማሌ ክልል ይልቅ ብዙ ገንዘብ መመደብ የነበረበት ለትግራይ ነበር፡፡ ግን ያ አልሆነም፡፡
ከኦሮሞ ክልል ቢያንስ 15 ቢሊዮን መቀነስ ነበረበት፡፡ እንኳን ሊቀነስ እንደውም 2 ቢሊዮን ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ከሲዳማና ደቡብና ክልሎችም እንደዚሁ መቀነስ ነበረበት፡፡ የአማራ ክልል አሁን የተመደበለተ 44 ሳይሆን ቢያንስ 70፣ የፋር ክልል አሁን የተንመደበለት 6 ሳይሆን ቢያንስ 10 ቢሊዮን ብር ሊመደብላቸው ይገባ ነበር፡፡
ሌላው የአብይ አህመድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትግራይ ውጭ ያሉትን እነ ወልቃይት ጠገዴን ሙሉ ለሙሉ ነው IGNORE ያደረጋቸው፡፡ እነ ወልቃይት ጠገዴ በአየር ላይ እየተነሳፈፉ ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በአብይ መንግስት ሙሉ ለሙሉ የተረሱ፣ ወይንም የትግራይ አካል ተደርገው የተቆጠሩ፡፡