>
5:33 pm - Saturday December 5, 0082

ምርኩዝ የሆነው ትውልድ ኢትዮጵያን ይታደጋት! (ደረጀ መላኩ)

ምርኩዝ የሆነው ትውልድ ኢትዮጵያን ይታደጋት!

አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም

ደረጀ መላኩ



ህይወት የተደበላለቀች ቦርሳ ናት፡፡ ኢትዮጵያም የተለየች ሀገር መሆን አይቻላትም፡፡ ከጓደኞቻችሁ፣ከዘመዶቻችሁ፣ ቤተሰቦቻችሁ እና በታክሲ ተሳፍራችሁ ስትጓዙ ከታክሲ አሽከርካሪዎችና እንደረሶው ተሳፋሪ ከሆኑ ሰዎች  ጋር አብራችሁ ተነጋገሩ፣ተወያዩ፣ በሃሳብ ተፋጩ፡፡ በመጨረሻ ላይ የምትደርሱበት ድምዳሜ መጪው ግዜ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ነው፡፡ የነገው ከዛሬው እጅጉን አስፈሪ ስለመሆኑ ለመገንዘብ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ የሀገሪቱን ብሔራዊ ኬክ ለብቻቸው ለመግመጥ የቋመጡ ጥቂቶች በስልጣን ማማ ላይ የተቀመጡ ተስፋችን ተስፋ ሆኖ እንዲቀር ሌት ተቀን ሴራ እየጎነጎኑ ነው፡፡ እያለን የለንም፡፡ በርግጥ የነገይቱን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሙሉበሙሉ ለመተንበይ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ የህልውና ፈተና የገጠማት ሀገር ስለመሆኗ ለመናገር ወይም ለመጻፍ አይከብድም፡፡ እጅግ አደገኛውና ዛሬም ያልሞተው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት አደገኛ ህልምና ቅዠት ፣ ኦነግ ሸኔ በሚባል የዳቦ ስም የሚታወቀው ቡድን ታጣቂዎች ጎሳና ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽመው ግፍ፣ መዳረሻው የማይታወቀው ስር የሰደደ ንቅዘትና ዝርፊያ ፣ በአስገምጋሚ ሁኔታ እየተምዘገዘገ ያለው የኑሮ ውድነት፣የገንዘብ ግሽፈት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ አሳሳቢው የወልቃይት ጸገዴ፣ ሰሜን ወሎ አላማጣ፣አበርገሌና የአካባቢው ጉዳይ፣ ያለ ህጋዊ አግባብ የሚፈጸሙ እስሮችና አፈናዎች፣ ጸረ አንድነት አቋም እየተጋጋመ መምጣቱ፣ሃሳብን በነጸናት የመግለጽ መብት ከባድ ፈታና ውስጥ መዶሉ ( ይህ ጽሁፍ በሚዘጋጅበት ግዜ ከ19 በላይ ጋዜጠኞች በመንግስት የታጣቂዎች ወደ ወህኒ አምባ ተወርውረዋል፡፡) ወዘተ ወዘተ ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል አደጋ ደቅነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በብሔራዊ ሀዘን ውስጥ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ የሶስት አመት ህጻን መያዣ በሚል ሰበብ ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት እንዲቆይ የሚደርግባት ሀገር ሆና መታየቷ( ወሎ ይመስለኛል አንድ ፋኖ የተባለን ግለሰብ ቤቱ ሂደው ሲፈልጉት ያጡት የመንግስት ታጣቂዎች ከመበሳጨታቸው የተነሳ ቤት ውስጥ ያገኙትን ህጻን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ውሰደው ለቀናት ያቆዩት ስለመሆኑ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተሰማ ጉዳይ ነው፡፡)  ፣ የ13 አመት ህጻን በጠራራ ጸሃይ የሚገድልባት ሀገር ሆና ማየት ልብን ያደማል፣ህሊናን ያቆስላል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

  ከላይ የዘረዘርኳቸው አንኳር ጉዳዮች አድካሚዎች፣እንዲሁም በሀገራችን ተስፋ ሊያስቆርጡን የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይህቺ የእኛ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ያለችን አንድ ሀገር ናት ፡፡ ይህቺም ኢትዮጵያ ናት፡፡ በበብዙ ውጣውረዶች ብናልፍም፣ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ብንከበብም በኢትዮጵያ ተስፋ መቆረጥ አይገባም፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንዶልም፣ መከራችን ቢበዛም ተስፋ መሰነቅ አለብን፡፡ በብሔራዊ ኩራት ተሞልተን ኢትዮጵያን ከወደቀችበት ለማንሳት እንትጋ የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ 

በብዙ የአዲስ አበባ ዋና ዋና አውራ መንገዶች ስጓዝ በርካታ ህንጻዎች፣ ዘመናዊ አውራ መንገዶች ተሰርተው ተመልክቼአለሁ፡፡ እነኚህ የሚያምሩ ህንጻዎችና መንገዶች እንዴት ፣ በማን ገንዘብ ተገነቡ ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ምን እንደሆነ የሚያስረዳኝ ሁነኛ ሰው አላገኘሁም፡፡ ወይም መረጃው የለኝም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋ መሆን ይችሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ቤታቸው አስፋልት ዳር በላስቲክ በተሰራ ጎጆ ውስጥ፣ ወይም አውላላ መንገድ ላይ ነው፡፡ ይህ በእውነቱ ልብን ያደማል፣ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡ እኔ ለመናገር የምፈልገው በንቅዘት ስለተሰሩ ህንጻዎች ወይም ምርታማ ስላልሆኑ ህንጻዎች በተመለከተ አይደለም፡፡ ከውጭ በሚገቡ ጥሬ ሀብቶች በሚገቡ ጥሬ እቃዎች  ማምረት ስለሚችሉ ኢንዱስትሪዎችም አይደለም፡፡

እኔ ማውራት የምሻው ስለ ሰብዓዊ ካፒታል ነው፡፡ ሰብዓዊ ካፒታል የአንድ ሀገር ትልቁና እጅግ ጠቃሚው ሀብት መሆኑን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ዛሬ ይሄን የሚገነዘቡ ጠንካራና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥቂትም ቢሆኑም አሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደማ ልብ ያላቸው፣ለሰብአዊነት መከበር የሚተጉ ወጣቶች አሉ፡፡

 እነኚህን ወጣቶች በአዲስ አበባ ሻይና ቡና ቤቶች ስለ የእለት ኑሮአቸው ሲያወጉ እነርሱም መመለከት ብርቅ አይደለም፡፡ በጂንካ፣ድሬዳዋ፣ባህርዳር፣ነቀምት፣ ሀረር፣ ጅግጅጋ፣ ሃዋሳ ወይም በውጭ ሀገር በሚገኙ ከተሞች  ሻንጋይ፣ ኢስታንቡል፣ ዋሽንግተን ዲሲ ባንኮክ፣ሎንዶን፣ ሙኒክ፣ብራስልስ፣ በብዙ የአለም ከተሞች ውስጥ ወዘተ ወዘተ ኑሮአቸውን መስርተው ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ 

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመልካች በርካታ የተማሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ትርፍ እና ጥቅም ያስገኛል ብለው ወደሚገምቱት   የኮንስትራክሽንና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ስለመሆኑ ታዝቤአለሁ፡፡ ወረት ያላቸው ደግሞ የራሳቸውን የግል ኢንዱስትሪ ከፍተው ትርፍ እያገኙ ነው፡፡  ይህ ሲባል ግን ኪሳራ የለም ማለት አይደለም፡፡ በተለይም የጎሳ ፖለቲካ ስርአቱን የማይደግፉ ብዙዎች በመንገድ ተቋራጭነት ሙያም  ሆነ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለወረቶች ከጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የቢሮ ሰራተኛ ሆነው ተቀጥሮ በመስራት የሚከፈለው ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑ ሌላ የስራ እድል ያገኙ እድለኞች ስራቸውን ለቀው ነጋዴዎችና ደላላ መሆንን የሚመርጡበት አሳዛኝ ግዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ሞራልና ስነምግባር አፈር ድሜ የጋጠበት ግዜ ላይ እንገኛለን፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በብርሃና ጨለማ መሃከል ውስጥ እንዲሁም  ኢትዮጵያ ሰላምም ጦርነትም በሌለበት አውድ ውስጥ ብትገኝም በኢትዮጵያ ወጣት ላይ ተስፋ አልቆርጥም፡፡

ኢትዮጵያ ከወደቀችበት አዘቅትና መከራ ወጣቱ ትውልድ ነጻ ያወጣታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በጎሳ ፖለቲካ ያበዱ የጎሳ ኤሊቶች ደጋፊ የሆናሁ ወጣቶች ሆይ በፍጥነት ከእንቅልፋችሁ ነቅታችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ የህብረት ችቦ እንዲለኩስ ለማድረግ መትጋቱ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡የፖለቲካ ኤሊቶችን ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት መንፈሳዊና ህሊናዊ ሀይል እንድትታጠቁ እማጸናለሁ፡፡ ወጣቱ ትውልድ አሸናፊና ተሸናፊ ያለበት ስርዓት ስር እንዲሰድ ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሆኑበት ስርዓት በኢትዮጵያ እንዲጎመራ፣ ዘላቂ ሰላ እንዲሰፍን፣ ለህዝብ የሚጠቅም ስርዓት እውን እንዲሆን፣ ለህዝብ ታዛዥ የሆነ መንግስት እንዲቆም መተኪያ የሌለው ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አፋጀሽኝ ከሆነው የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያ የምትገላገልበትን የሰለጠነ ዘዴ መፈለግም አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ግደይን በጋቢሳ የተኩ፣ከወያኔ እጅጉን የተማሩት ዘረኞች መከራችንን አበዙት እንጂ አልጠቀሙንም፡፡  ዝባድን ከውሻ እምነትን  ከባለጌ ፈጽሞ አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ ተላላነት መሆኑን ወጣቱ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ እንክርንዳዱን ከስንዴው መለየት ብልህነተ ነው፡፡ አያውቁንም፣ ለካ አያውቁንም፣ ላላወቁን ኢትዮጵያዊ መሆናችንን በዋነኝነት ማሳወቁ የወጣቱ ትውልድ ሃላፊነት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ መጠለፉ ማብቃትም አለበት፡፡ በመጨረሻም ይሄ ትውልድ ከችግር ፈጣሪዎች ጋር ህብረት መፍጠሩን አቁሞ ሀገሩን እና ህዝቡን እንዲታደግ በማሳሰብ እሰናበታለሁ፡፡

Only the youth is capable of making win-win deals and charting new directions free of ethnic and religious shenanigans. The day of the antediluvian politicians needs to be over.

Filed in: Amharic