>

ታሪክ ራሱን ደገመ...!!!  (ጌጥዬ ያለው)

ታሪክ ራሱን ደገመ…!!!

ጌጥዬ ያለው


*…  ፋኖ መስዋዕትነት ከፍሎ በዚያው እንዲጠፋ ሲባል ትጥቅ እንኳን ሳይሰጠው እንዲዘምት ተደገ። ሆኖም የአባቱ ልጅ ነውና እንደ ካሳ ኃይሉ እየማረከ ታጠቀ!!!

የቋራው ካሳ ኃይሉ አነሳስ ያስፈራቸው የዘመኑ መኳንንት በአፈሙዝ ገጥመው አዩት፤ አልቻሉትም። በጋብቻ ሊያስሩት ሞከሩ፤ ሚስቱም ለጀግና ሟች፤ ጀግና ነበረችና ሊታሰር አልቻለም።

የመጨረሻው አማራጭ የውጭ ወራሪ ሲመጣ እምብዛም ያልታጠቁ ጥቂት ወታደሮቹን ይዞ ብቻውን እንዲዘምት ማዘዝ ነበር። ትዕዛዙ መስዋዕት ሆኖ እንዲጠፋ መሆኑ እየገባው ካሳ አንዳች ሳያቅማማ ዘመተ። እስከ አፍንጫው ታጥቆ በቋራ በኩል የገባውን የግብፅ ወራሪ በጨበጣ ውጊያ መሀሉ ገብቶ በማራወጥ ትጥቁን እየማረከ ራሱ ታጠቀው።

በመስዋዕትነት ይጠፋል የተባለው የካሳ ጦር እንዳውም ይበልጥ ደረጀ። ዘመነ መሳፍንት አብቅቶ የካሳ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ህልምም እውን ሆነ።

በዚህ ወቅት በፋኖ ላይ እየደረሰ ያለውም ተመሳሳይ ታሪክ ነው። ከትግራይ ወራሪ ሃይል ጋር ጦርነቱ ሊጀመር ጥቂት ሲቀረው የገዥው ፓርቲ ሰዎች ፋኖዎችን በቄስ በመነኩሴ ከየጫካው እያስጠሩ፤ ግፋ ሲልም ራሳቸው ግማሽ መንገድ እየሄዱ ታረቁ። የክብር እውቅናና ሽልማትም ሰጡ። በዚያው አፍታ “ወያኔ የሕልውና ችግር ሆኖብናል። ድረሱልን” ተባሉ።

ፋኖ መስዋዕትነት ከፍሎ በዚያው እንዲጠፋ ሲባል ትጥቅ እንኳን ሳይሰጠው እንዲዘምት ተደገ። ሆኖም የአባቱ ልጅ ነውና እንደ ካሳ ኃይሉ እየማረከ ታጠቀ። ራሱን ይበልጥ አደረጀ። ከአባቱ ታሪክ የሚለየው ካሳ በመሳፍንት የተከፋፈለች ኢትዮጵያን አንድ ያደረገ ሲሆን ፋኖ በብሔር የተከፋፈለች ኢትዮጵያን አንድ የማድረጉን ሥራ ገና ያልጨረሰ በመሆኑ ነው።

እነሆ ዛሬም እንደገና ሊጠነክር የምስራቅ አማራ ፋኖ ከትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር ሊፋለም በሕዝብ አጀብ ተሸኝቷል። ጀግኖች ሆይ በድል ተመለሱ!

Filed in: Amharic