>

ለመስከረም አበራ ከ/ፍ/ቤት  አጽንቶላት የነበረውን የዋስትና መብት ፖሊስ ድጋሚ ይግባኝ እጠይቅባታለሁ አለ...!?! (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ለመስከረም አበራ ከ/ፍ/ቤት  አጽንቶላት የነበረውን የዋስትና መብት ፖሊስ ድጋሚ ይግባኝ እጠይቅባታለሁ አለ…!?!

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በስር ፍርድ ቤት የተወሰነላትን የ30 ሺህ ብር ዋስትና በዛሬው ውሎው አጽንቶላት የነበረችው መስከረም አበራ፤ በፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ተጠይቆባት ከእስር ሳትለቀቅ ቀረች። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “የህግ ስህተት አለ” በሚል ይግባኝ የጠየቀው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሆነ ጠበቃዋ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የዛሬውን የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ፤ የመስከረም ቤተሰቦች የ30 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘቡን ከምሳ ሰዓት በፊት ከፍለው፤ ሂደቱን ጨርሰው እንደነበር ባለቤቷ አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ሆኖም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች “ይግባኝ እንጠይቃለን” በሚል ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይዘዋት መሄዳቸውን አክለዋል።

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት በሆነችው መስከረም ዛሬ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብትወሰደም፤ ፖሊስ ለጠየቀው ይግባኝ “ፋይል ባለማደራጀቱ” ጉዳዩ ለነገ ረቡዕ መቀጠሩን ጠበቃዋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፖሊስ በመስከረም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ይግባኝ የጠየቀባት ትላንት ሰኞ ከሰዓት ሰኔ 6፤ 2014 ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስገባው አቤቱታ ነበር።

መርመሪ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰደው፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለተጠርጣሪዋ የዋስትና መብቷን ማስጠበቁን ተከትሎ ነው። የይግባኝ አቤቱታው ዛሬ ማክሰኞ ረፈዳ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ የፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን  ማጽናቱ ይታወሳል።

Filed in: Amharic