>
5:21 pm - Thursday July 20, 7437

"ሕግ መከበር አለበት!  ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸብር ግን ሊሆን አይገባም...!!!"  (ክርስቲያን ታደለ)

“ሕግ መከበር አለበት!  ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸብር ግን ሊሆን አይገባም…!!!”

ክርስቲያን ታደለ


በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ላይ ለክቡር ጠ/ሚኒስቴሩ የቀረበ ጥያቄ

**

አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈጉባዔ፣

አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

መንግስት ግጭትን በበላይነት በመቆጣጠር ብቸኛ ሥልጣኑና ሕግን በማስከበር ሊኖረው ስለሚገባ ዝቅተኛ መንግስታዊ ግዴታው ላይ አንዳችም ልዩነት የለኝም።

ባለፉት አራት ዓመታት ንጹኃን ዜጎች ላይ ያለመታከት  የጅምላ ግድያ እና ማፈናቀል ሲፈፀም፤ የመንግስት ያለህ ስንል የኖርነው ሕግ ማስከበር  የመንግስትነት ስነ-ፍጥረት መሆኑን ስለምንረዳ ነው።

ሕግ ማስከበር ሲባል ዜጎች በአገራቸው በማንነታቸው ቤተኛና ባይታዋር ሳይደረጉ የሚኖሩባት ሰላማዊ አገር መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለደረሰ ጥፋትም ተጠያቂነት ማስፈን ሲቻል ነው።

ይሁንና መንግስት ሕግ ያስከብር ማለት መንግስት ሕግ እየጣሰ ዜጎችን ያሸብር ማለት አይደለም።

መንግስት ሕግ የማስከብር መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት ሲባል ማስከበርና መጠበቅ ያለበትን ሕግ የመጣስና  የማፍረስ መብት አለው፤ ይኑረው ማለት አይደለም።

ባለፈት ሦስት ሳምንታት «ሕግ  ለማስከበር»  በሚል በከፈተው ዘመቻ ዜጎች በሕገመንግስቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት መከበር ስምምነቶች ጭምር ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶቻቸውን የጣሰ፤ ከሕግ ማስከበሩ ይልቅ ሕጋዊ ሂደቶችን ያልተከተለ መሆኑ ከአፈፃፀሙ ተገንዝቤያለሁ።

ሕግ ለማስከበር  በሚል ሕግ እየተጣሰ ሕፃናትን ጨምሮ 35 የሚደርሱ ዜጎች ያለፍርድ  በፀጥታ አካላት ተገድለዋል። 40 የሚጠጉ የድርጅታችን መዋቅር አመራሮችና አባላት ታስረዋል።  አስሮ መመርመርን የአገሪቱ ሕግ ባይፈቅድም ከ20 በላይ ጋዜጠኞች ታስረዋል። በርካታ ሺዎች ያለፍርድቤት ትእዛዝ በቀንና በሌሊት በፀጥታ አካላት እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደው ተሰውረዋል። እስካሁንም ፍርድቤት ያልቀረቡና ቤተሰብ የማይጠይቃቸው፤ የት እንዳሉም የማይታወቁ ዜጎች አሉ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ የሚመሩት የፀጥታ መዋቅር ጦርነት በሚመስል መንገድ በመረጠኝ ሕዝብ ላይ በተለያዩ አካላት የመግለጫና ፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ጭምር  የተቀናጀ ዘመቻ በመክፈት ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዳይከውን እያጉላላው ይገኛል።

ዛሬ በአማራ ክልል ተፈናቃይ ያልተጠለለበት ከተማና ወረዳ ማግኘት በማይቻልበት ደረጃ ሚሊዮኖች ውዶቻቸውን አጥተው፤ ወረታቸውን ተነጥቀው ባሉበት መንግስታዊ ካሳና ማቋቋሚያ ሲጠብቁ፥ እጅግ የተጋነነ ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል።

(በተመረጥኩበት አካበቢ ብቻ 300ሺህ የሚጠጋ ተፈናቃይ የእለት ደራሽ እርዳታ የሚሰጠው አጥቶ እንዳለ ማሳወቅ እወዳለሁ።)

መንግስት ከጠላት ማርከህ ታጠቅ ያለውን የአማራ ወጣት ከማነጋገር ይልቅ በያዘው ማባረር በተለያዩ ክልሎች ታጥቀው መንግስትን እየተዋጉ ያሉ ቡድኖችን መሰል ቅራኔ በሌሎች አካባቢም የሚያዋልድ ዘመቻ ላይ እንዳለ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ሕግ መከበር አለበት!  ሕግ በመጣስ እና ሕዝብን በማሸብር ግን ሊሆን አይገባም…!!!

ታፍነው ደብዛቸው የጠፉ ተማሪዎቹን መጨረሻ ያልተነገረው ሕዝብ፥  ዛሬ እንደገና ዜጎችን በማፈን ፣ ከሕግና ከቤተሰብ በመሰወር የተጀመረው ዘመቻ ሌላ አደገኛ ወንጀል እያለማመደ  እንደሆነ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፤

► በሕግ ማስከበር ሽፋን የመንግስት ተቺዎችንና የተቃውሞ ድምፆችን በማፈን፣ ስጋትና ፍርኃት የሰፈነበት የሙያ ምኅዳር በመሻት መንግስትዎ የዴሞክራሲ ግንባታን እንዴት እውን ሊያደርግ የፈቀደ መንግስት እየመሩ ነው?

► የታፈኑና ከፍርድ ውጭ በኮንሰንትሬሽን ካምፕ ያሉ ዜጎችና አባሎቻችን አስቸኳይ ፍትኅ እንዲሰጣቸው መጠየቅ እፈልጋለሁ።

► ትናንት የታገልንለት ለውጥ ወደኋላ ተቀልብሶ ወደነበርንበት አፈና መመለሱን በማወቅ መንግስትዎ በሕዝባችን ላይ ለሚፈፀመው ግፍ በራሱ ላይ ተጠያቂነት የሚወስደው መቼ ነው?

አመሰግናለሁ!

Filed in: Amharic