>

ስንታየሁ ቸኮል እና ያለለት ወንድዬ ሕገ መንግሥቱን በኃይል በመናድ ተወነጀሉ !! (ባልደራስ)

ስንታየሁ ቸኮል እና ያለለት ወንድዬ ሕገ መንግሥቱን በኃይል በመናድ ተወነጀሉ !!

ባልደራስ


*… ለሰኔ 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ ወህኒ ወርደዋል!!

ከሃያ ቀናት ገደማ በፊት  በባሕር ዳር የታፈኑት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊው ስንታየሁ ቸኮል እና የቀድሞው የአማራ ሳተላይት ራዲዮና ቴሌቪዥን(አሥራት) ባልደረባ ጋዜጠኛ ያለለት ወንድዬ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ ተወንጅለዋል።

ውንጀላውን ያቀረበው የፌዴራል ፖሊስ ሲሆን፣ ዛሬ ረቡዕ፤ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በአማራ መስተዳድር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ፖሊስ ከስንታየሁ እና ያለለት ጋር ዋሴ በመረሳው እና ደምስ አያሌው የተባሉ በአካባቢው በሚያደርጉት ንቁ የማሕበረሰብ ተሳትፎ የሚታወቁ ወጣቶችን በአንድ መዝገብ ወንጅሏል።

ሁሉም ተከሳሾች ሕዝብን ለተቃውሞ የሚያነሳሳ ፅሁፍ በፌስቡክ ሲያሰራጩ እንደነበር ከሳሽ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅሷል።

ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ፣ ባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደነበር እና ጉባኤውን ለማደናቀፍ የተደረገ አፈና እንደሆነ ተናግሯል። ውንጀላው የፖለቲካ ተሳትፎውን ተከትሎ የመጣ ፖለቲካዊ ጥቃት እንደሆነ ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብተው ጠይቋል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ 12 የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አራቱም የኅሊና እስረኞች ከየነበሩበት ፖሊስ ጣቢያ ወደ ባሕር ዳር ሰባታሚት ወህኒ ቤት ተወስደዋል።

/

Filed in: Amharic