ሰለሞን ሹምዬ በዋስትና ከእስር ተለቀቀ…!!!
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
“ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን ሹምዬ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀቀ። ሰለሞን ከእስር የተለቀቀው፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ አርብ ሰኔ 10፤ 2014 ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ነው።
ሰለሞን ዛሬ አምስት ሰዓት ተኩል ገደማ አካባቢ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወጥቶ ከቤተሰቦቹ ጋር መቀላቀሉን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። ግንቦት 12፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ሰለሞን፤ ያለፉትን 28 ቀናት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ አሳልፏል።
“ሻይ ቡና” በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ይበልጥ የሚታወቀው ሰለሞን፤ 10 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በፍርድ ቤት የተወሰነለት ከአስር ቀናት በፊት ግንቦት 30፤ 2014 ነበር። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ይህን ውሳኔ በመቃወም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የዚያኑ ዕለት ይግባኝ ጠይቋል።
ይግባኙ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ተጨማሪ ስምንት የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ነበር። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት የተጠርጣሪው ጠበቆች ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 3፤ 2014 አቤቱታ አስገብተው ነበር። ይህንኑ የይግባኝ አቤቱታ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በነበረው የችሎት ውሎ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በመሻር የተጠርጣሪው የዋስትና መብት እንዲጠበቅ አድርጓል። (