>
5:29 pm - Monday October 10, 2788

ፍትሕ አልባ ሕጎች....!!! (ቀለብ ስዩም)

ፍትሕ አልባ ሕጎች….!!!

ቀለብ ስዩም


*….. ጥጋብ ትእቢትንና እብሪትን ይወልዳል፤ ትእቢትና እብሪት ሲመጣ ደግሞ ህሊና ይደድባል፡፡ ያኔ ሁሉም ነገር የጨለማ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ደግሞ ወንጀለኛና የአመፅ ሰው ይበዛል፡፡ ሚዛነዊነት፣ ፍትሃዊነት፣ አስተዋይነት፣ እግዚአብሔርን መፍራት ይጠፋሉ፡፡ ሸፍጥ፣ ተንኮል፣ መጠላለፍ፣ ጥቃትና ውድመት ይንሰራፋሉ፡፡ አዎ! በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁሉ የሰቆቃ፣ የበደልና የግፍ አይነቶች ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ህግን የሚረግጥ ህግ ያስከብራል!?

—————————–

ሁላችንም እንደምናውቀው በእዚህች አገር በወረቀት ላይ ያልሰፈረ ህግ የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡትን አውራና ገዢ የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራት ነፃነት የማያስከብር፣ የአገርና የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ዋስትና መሆን የማይችል፣ ፍትህና እኩልነትን የማያሰፍን፣ ህዝብን ከወንጀለኞች የማይታደግ፣ ስለ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች መከበር ደንታ ቢስ የሆነ መንግሥት ነው ያለን፡፡ ከእዚህ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ደግሞ መንግሥት ራሱ የዜጎቹን መብትና ጥቅም የሚረግጥ፣ የሚጨፈልቅ የመሆኑ ጉዳይ ይሆናል፡፡

የኢህአዴግም ሆነ ብልፅግና ተቀብሎ ሲመቸው ብቻ የሚሰራበት ሕግ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንደማይያዙ ይደነግጋል፡፡ ወንጀል ሲፈጽሙ እንጅ ከፈንጅ እስካልተያዙ ድረስም ይህ ያለመያዝ መብት ያገለግላል፡፡ አሁን ግን እየሆነ ያለው በተገላቢጦሹ ነው፡፡ መንግሥት ዜጎችን ያለምንም ህጋዊ አካሄድ ያሰራል፣ በሺህዎች የሚገመቱ ሰላማዊ ሰዎችን አፈና አካሂዶባቸዋል፡፡ ከእነዚህም ምክንያት ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ሚስቶች የባሎቻቸውን አድራሻ ሳያውቁ ሌት ተቀን በሥጋት ሲሸበሩ ውለው ያድራሉ፡፡

በእዚህ መልኩ እውነትን የዘገቡና መንግሥታዊ ሽፍጦችን ያጋለጡ በርካታ ጋዜጠኞች፣ የአገር አድባር የሕዝብ መካሪ የሆኑ የተከበሩ አዛውንቶች ለምን አልደገፋችሁንም እየተባሉ ቁም ስቅላቸው ያያሉ፡፡

ቅዱስ መፅሐፍ “የማይታወቅ የተሰወረ – የማይገለጥ የተከደነ የለም” እንዲል ፀሐይ ያየችውን ሁሉ ሰው መስማቱ አልቀረም፡፡ በጨለማ ከለላ የተሰራውም በቀን በብርሃኑ ይጋለጣል፡፡ የህወሓት መንበረ ሥልጣንን የተረከበው የኦህዴድ ተረኛና ባለጊዜ ሆኖ እነሆ ፍትህ ሲጥስ የዜጎችንም መብት ሲረግጥ ይስተዋላል፡፡ እናም የብልፅና ግፍና በደል ማቆሚያው የት ነው!?  ሕዝቡስ በደልን በግዴታ እየተጋተ በዝምታ ለመቀጠል የትእግስት ወሰኑ ከምኑጋ ነው!? እውነት እውነት እላችኋለሁ! ይህ ርዕሰ ጉዳይ የማያስጨንቀን ለምን እንደሆነ መገመት ያስቸግራል፡፡ ብንፈልግም – ባንፈልግም በሁሉም አቅጣጫ ከድጡ ወደማጡ እየገባን እንገኛለን፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንትን የመዘንጋት ችግር 

ጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዛሬ አራት አመት የነበረውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የዘነጉት ይመስላል፡፡ ያኔ ሴት – ወንዱ፣ ህፃን ሽማግሌው …. ለጠቅላይ ምኒስትሩ የነበረው ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የትግራይ ወጣቶች እንኳን የእሳቸውን ወደ ሥልጣን መምጣት በደስታ ነበር የተቀበሉት፡፡ ትንሽ ትልቁ “አብይ! አብይ!” ያለበት ምክንያት የተሰወረም የተወሳሰበም አልነበረም፡፡ ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሉአላዊ አንድነት ያስከብራሉ፣ የሕዝቡን አብሮ የመኖር ባህል ያጎለብታሉ፣ ሰላምና ፍቅርን ያነግሳሉ፣ አንቀጽ 39”ን ከህገ መንግስቱ እንዲሰረዝ ያደርጋሉ፣ ፍትህና ዲሞክራሲን ያሰፍናሉ፣ የሕግ የበላይነትን ያረጋግጣሉ ….. ተብሎ ተስፋ በመደረጉ ለአርባ አመታት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ ሰዎች ሳይቀሩ በሰላማዊ መንገድ ለመታገደል ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ይታወቃል፡፡ እነርሱ እንኳ ሳይቀሩ ለጠቅላይ ምኒስትሩ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አሳይተዋል፡፡ በእዚህም ምክንያት በጠቅላይ ምኒስትሩ ላይ የሚሰነዘርን ጥቃት ፊት ለፊት ተጋፍጠው ውድ ህይወታቸውን መስዋእት ለማድረግ የተዘጋጁ ወጣቶች በቁጥር እጅግ በርካታዎች ነበሩ፡፡

ዛሬስ!? እንደዚያ ሲንሰፈሰፍሎት የነበረው ህዝብ ኮ ዛሬ ላይ ለምን የጠላዎት ይመስሎታል!? ….. በእርግጠኝነት በርካታ አማካሪዎችን ያሰባሰበ ቁንጮ ባለሥልጣን ይህ እውነትና እንቅጩ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡ የቅርብ ሰዎችም መልካሙን ነገር ለማማከር ካልታደሉ እኔ ልነግርዎት እችላለሁ፡፡ አዎ! እውነታውን በመናገሬ በጠላትነት ካልፈረጁኝ በስተቀር እኔ ለመግለፅ አልቸገርም፡፡

ወደ ሥልጣን መጥተው ከሰነባበቱ በተለይም የአምስት አመቱን ምርጫ ተብየውን አሸነፍኩ ባሉበት ማግስት የተደበቁ ማንነቶች ገሀድ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ኦሮሞነት አሸንፎሆታል፡፡ የጎጠኝነትን ካባ ያጠለቁ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞዋ ታላቅነቷ እመልሳለሁ ሲሉ ቃል የገቡለትን ህዝብ ክደውታል፡፡ ስለወደደዎት ጠልተውታል፣ ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሳትባልዎት ቁጥር ደፍረው ለመተቸት በሞከሩት አገርና ህዝብ ወዳጆች ላይ ዘምተዋል፡፡

ይህን ምስኪን ህዝብ በሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነቶች አድቅቀውታል፡፡ ትናንት የነበሩ አይነኬ ሰዎች ዛሬም እንዳሻቸው ሲሆኑ እንመለከታለን፡፡ ምናልባትም አዳዲስ ነጋዴ ባለስልጣናት ተጨምረዋል፡፡

በልጆች የብሽሽቅ ጨዋታ አይነት እንከሰላንቲያ አገር እንዴት ይመራል? ደግሞስ አንድ የአገር መሪ እንዴት እታማለሁ፣ እተቻለሁ፣ እሰደባለሁ የሚል ምሬት እንዴት በአደባባይ ይሰማል! እኔ እስከማውቀውና እስከሚገባኝ ድረስ አንድ ሰው ወደ ሥልጣን ሲመጣም ሆነ ዝነኛ ሲሆን “የግል ሕይወት” የሚባል ነገሩኮ ይቀንሳል፡፡ ያ ሰው የህዝብ ሀብት ነው ተብሎ ስለሚታመን በአንድም በሌላም መልኩ የግል ገመና (ምስጢር) የሚባሉ ነገሮች በተወሰነ ደረጃ አይኖሩትም፡፡ ይወደሳል – ይወቀሳል፤ ይተቻልም፡፡ ይህን እውነት ሳይገነዘቡ ወደ ስልጣን መጥተው ከሆነ ስህተቱ የእርስዎ የራስዎ ብቻ ነው፡፡

ሌላም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ ያልተዋጠልኝ ነገር አለ፡፡ አበው “ለቀባሪው አረዱት!” እንዲሉ፡- በኮሮና በጦነትና በሌሎችም ችግሮች ውስጥ ሆነንም እንኳ አገር አሳድገናል፣ ወይም ደግሞ እድገት አስመዘግበናል … ይላሉ፡፡ እኛ በረሀብና    በኑሮ ውድነት እየተቆላን ያለን ሕዝብ ነን፡፡ የተለጠጠ የኢኮኖሚክስ ፍልስፍናም አይገባንም፤ ደግሞም የስታቲስቲክስ ቁጥር ሁሉም እውነት አይደለም፡፡ በግልፅ ቋንቋ እንነጋገር ከተባለ የአገራችን የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በእኛ የእለተ ተእለት ሕይወት ውስጥ እየተመለከትነው እንገኛለን፡፡ ለምን ይዋሻል፡፡

ከእዚህ ይበልጥ ጨርሶ ያልገባኝ ነገር አገሪቱ አሁንም ከጎሰኝነት አዙሪት ያለመውጣትዋ ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የራስዋ የብሔረሰቦች ስብጥርን የያዘች ትንሽዋ ኢትዮጵያ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ እናንተ ግን የኦሮሚ ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፍርድ ቤት፣ የኦሮሚያ መስተዳድር፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ አበባ አቋቁማችኋል፡፡ ይህ እድል ለአማራ፣ ለአፋር፣ ለትግራይ ፣ ለደቡብ ህዝቦች….

አልተሰጠም፡፡ ከእዚህ በላይ አድሎአዊነት ምን ይኖራል!??? ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠሪያዎች ናቸው፡፡ ብሔራዊ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲይዙ የሚደረግውም እዚህ ነው፡፡ እናንተ ግን በእብሪተኝነት መንፈስ በአዲስ አበባ በሚገኙ የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር እንዳይዘመር አድርጋችኋል፡፡ በምትኩም የኦሮሚያ ክልላዊ መዝሙር ነው የሚዘምረው በማለት ትገኛላችሁ፡፡ ይህ ራሱን የቻለ የአገር ክህደት ወንጀል አይደለምን!?

ከእዚህ ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ ለእዚህ ትችት የሰጡት ምላሽ ይሆናል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲጠየቁ “ስለ አልባንያ…” የሚያወሩ አስቸጋሪ ሰው ነበሩ፡፡ አሁንም ዶክተር አብይ አህመድ ከምክር ቤታቸ፡- “የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር አይዘመርም…” የሚልና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን ሲነሱ በፈረንሳይ በግሪክ…. ትምህርት ቤቶችም የሚዘምሩት የአገራቸውን መዝሙር ነው…. የሚል አይነት ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ ታድያ በእዚህ አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ተወካይ? ወይስ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው እንበል!? ነገሩ ሁሉ “ፍየል ወዲህ . ቅዝ ምዝም ወዲያ!” እንደሚባለው ሆኖብኛል፡፡

ለነገሮች አፅንኦት ሰጥቼ ስመረምራቸው ሰውየው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ያለመክሊታቸው ይመስለኛል፡፡ ጨርሶ የመሪነት ሚና እንደሌላቸው ነው የምገነዘበው፡፡ ጠቅላይ ምኒስትሩ አገር የመምራት ዋነኛውን ጉዳይ  ትተው፣ ባብዛኛው አትክልተኛ፣ አናፂ ፣ ግንበኛ፣ ….  ላይ ነው ጊዜያቸውን የሚያጠፉት፡፡ አስፈላጊ ከሆነ እንዲህ አይነት ነገሮችን የሚያከናውን አንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማቋቋም ይችላሉ፡፡ እርሳቸው ፓርክና ቤተ መንግስት ግንባታ ላይ ተጠምደው ዜጎች ይበደላሉ፣ አገር ይወረራል ሰዎች ይገድላሉ፣ ይታፈናሉ…. እናስ ምን ይበጀናል ትላላሁ!?

-ፈጣሪ አምላክ ሆይ! ኢትዮጵያ አገራችንና ህዝቦችዋን አንተ ጠብቅልን! አሜን፡፡

Filed in: Amharic