በረንዳ…!!!
(በእውቀቱ ስዩም)
ምኡዝ በዝግጀቴ መሳካት ደስታውን ለመግለጽ ግሮሰሪ መጣ
“ምን እየጠጣህ ነው ? “ አለኝ::
“ ስፐራይት” አልሁት:
“ ወንድ ልጅ ለስላሳ ሲጠጣ እንደማየት የሚዘገንን ነገር የለም፤ አይስክሬም የሚልስን ወንድማ ማጅራቱን ረግጦ አፈር ማስላስ ይገባል፤ ማስቲካ የሚያኝክ ወንድ ሳይ ፥ ጉንጬን በቡጢ ጠርምሸ መንጋጋውን ለቅልጥም ተመጋቢ ወንዶች ዶኔት ማድረግ ያምረኛል፤ ወንድ ልጅ ካገኘ ቅልጥም ሲከሰክስ ፥ ቢያጣ የተቀቀለ ሙሉ በቆሎ እንደ አርሞኒካ አፉ ላይ አጋድሞ ሲግጥ ነው እሚያምርበት ፤ ወንድ ልጅ ምግቡና መጠጡ እንደ ኑሮው ትንሽ ትግል ትንሽ ምሬት ካልታከለበት አይረባም”
ቢራ አዘዝኩ፤
ምኡዝ ጮክ ብሎ “ ጥብስ እፈልጋለሁ” አለ፤
“ ሳይድ ምን ይደረግልህ?” አለችው አስተናጋጂቱ
“ ጎረድ ጎረድ “
እየበላ፥
“እንደ አቅራቢ ዝግጅቱን እንዴት አየኸው?” ሲል ጠየቀኝ ፤
“ ሸጋ ነበር፤ እያነበብኩ ወደ ታዳሚው ስመለከት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ታዳሚ ይስቃል፤ ሌላው ደግሞ ፊቱ ላይ ማጭድ ማጭድ እሚያህል ፈገግታ ተስሏል፤ በዚህ ተበረታትቼ ንባቤን ዘለግ አድርጌ እየቀደደኩት እያለ መሀል ላይ ካንደኛ ክፍል ጀምሮ አብሮኝ የተማረ ሰውየ ጉብ ብሎ ሲያፈጥብኝ አየሁ፤ ፊቱ ላይ “ አናውቀህምና ነው? በጦጥማ ሜዳ ፤ አህያ ስት(ነ)ዳ “ የሚል መልክት ይነበባል፤ ፊቱን ሳየው ተደናግጨ አንድ አንቀጽ ዘለልሁ፤ “
አስተናጋጂቱ ሁለተኛ ቢራ እየከፈተችልኝ።
“ በውቄ፤ “ ቢያድግልኝ “ እሚለው ያንተ ታሪክ ነው?” አለችና በሀዘኔታ አየችኝ ፥
እንዴት ማስተባበል እንዳለብኝ በማሰብ ላይ ሳለሁ ምእዝ ቀደመኝ፥
“ በፍጹም! እሚገርምሸ እነገር የሆነ ጊዜ አብረን እንፋሎት ስንጠመቅ ፎጣ ተንሸራቶበት እቃውን ለማየት እድል አግኝቸ ነበር፤ እቃው ቦታ የቀየረ የጭላዳ ጅራት ነው እሚመስለው ፤ እንዲያውም እቃው ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ታከሲ ሲሳፈር ለእቃው ለብቻ ተጨማሪ ክፍያ ያስከፍሉታል”
ምእዝን አመሰግኘ አንድ ግማሽ ጠርሙስ ውስኪ አስወረድኩለት፤
“ ገቢው አሪፍ ይመስላል” አለኝ ወደ ጠርሙሱ በፍቅር እየተመለከተ፤
“ ተመስገን ነው፤ ቤት ኪራይ ከፍያለሁ፤ ለመንግስትና ለብሄራዊ ትያትር ዳጎስ ያለ ግብር አስገብቻለሁ፤ ትራፊክ ፖሊስ ዝግጅቱን ለመታደም የመጡትን ተመልካቾች መኪና ታርጋ ፈትቶ በማግስቱ የገንዘብ ቅጣት ጥሎባቸዋል፤ እንዲያውም፥ የትራፊክ ጽፈት ቤት ያልታሰበ ገቢ ስላስገባሁለት ሊሸልመኝ እየተዘጋጀ እንደሆነ ደርሸበታለሁ”
“በዝግጅትህ ታድሜ ነበር” የሚል ድምጽ ሰምቼ ዞር አልሁ፤ አንድ ትኩስ የተጣለ የሰጎን እንቁላል እሚመስል ራስ ያለው ደንበኛ ነበር፤
“ እንዴት ነው ፈታ አረግሁህ አይደል?” ስለው፥
“ ፈታ ታደርገኛለህ ብየ መጥቼ፤ ታርጋየን አስፈትቼ ተመለስኩ”::