>

ይቺ ያንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት ዋጋዋ ስንት ቢሆን ነው ፓርላማው የቆጠባት? (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ይቺ ያንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት ዋጋዋ ስንት ቢሆን ነው ፓርላማው የቆጠባት?

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ጆሮ ፀጥታን፣ አንደበትም ዝምታን አይወዱምና ስለሀገራችን ጥቂት እናውራ፡፡ የሚሆነው ሁሉ ከመሆን የሚያግደው ነገር ባይኖርም በወቅዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትንሽ መብሰክሰካችንን እንቀጥል፡፡ ለነገሩ ተስፋ በመቁረጥም ይሁን በሌላ ምክንያት በጣም ብዙው ሰው ስለሀገሩ መከታተልን ጅባት ብሎ የተወ ይመስለኛል፡፡ ሁኔታው ያስፈራል፤ ስለኛ ካለኛ ማን ሊጮህልንና ሊደርስልን እንደሚችል አላውቅም፡፡ ዝምታችን አስደንጋጭ ነው፡፡ የግዴለሽነታችን መጠን ለኅልውናችን መቀጠል ራሱ አሳሳቢ ነው፡፡ ለማንኛውም ጥቂቶችም ብንሆን ተስፋችንን በአንድዬ ላይ የጣልን ዜጎች አንዴውኑ ፈርዶብናልና እስካሁን ጩኸታችንን አልተውንም፤ ወደፊትም አንተውም፡፡ አንባቢና አድማጭም ቢጠፋ ለታሪክ ፍጆታ በየደረጃው ተሰንዶ የሚቀመጥ በመሆኑ ስለምናየውና ስለምንሰማው ግፍና በደል እንጮሃለን፡፡

የሀገራችን ጉዳይ ከድጡ ወደማጡ እየገባ ስለመሆኑ በየቀኑ ከምንሰማቸው ጉድ የሚያሰኙ ገጠመኞች መረዳት እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ በምን መሰል እጆች ውስጥ እንደገባች ልናምነው በሚቸግረን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ “በጌታዋ የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ ሆኖ ሰሞኑን የአቢይ ፓርላማ ተብዬ አፈ ጉባኤ ያደረገውን ስንሰማ ደግሞ በእጅጉ ተገርመናል፡፡ አብኖች ወለጋ ውስጥ ሰሞኑን በሸኔ ለተገደሉ በሽዎች የሚቆጠሩ ወገኖች የኅሊና ጸሎት እንዲደረግ ቢጠይቁ የገዳዩ አቢይ ዕንባ ጠባቂ የሆነው ወያላው ታገሰ ጫፎ በቁጣ እንደከለከለ ሰማን፡፡ አንዲት ደቂቃ የኅሊና ጸሎትም እንደቁም ነገር ተቆጥራ በዚያ መልክ በንዴት ጦፎ መከልከሉ በርግጥም “ስልብ አሽከር በጌታው ብልት መፎከሩ”ን አረጋገጠልን፡፡ “ያዝልቅለት፤ መጨረሻውንም ያሳምርለት”  ከማለት ውጪ ምን ሊባል ይችላል?

ይህ የኅሊና ጸሎት ክልከላ ብቻውን እጅግ ብዙ ነገሮችን ይናገራል፡፡ ሲጀመር የኅሊና ጸሎት ለማንም ሊከለከል የማይገባውና በፈጣሪ የሚያምን ሁሉ ለጠላቶቹም ሳይቀር የሚቸረው ምንም የማይከፈልበት ነገር ነው፡፡ “ነፍስ ይማር” ማለት ለጠላትም ለወዳጅም የሚባል ለነፍስ ድኅነት የሚሰነዘር ምኞት ነው፡፡ ነፍስ ይማር ተብሎ ስለተነገረም ነፍስ ይማራል ማለትም አይደለም – ቢማርም ያስደስታል እንጂ አያስቆጭም፡፡ ነፍስን የሚያስምረውና የሚያስኮንነው ሥራችን እንጂ የሰዎች ልመናና ጸሎት ብቻም አይመስለኝም፡፡ አንዲት ነፍስ ብትማርስ እስከዚህ አገር ትንዳለች እንዴ? 

ታገሰ ጫፎ አቢይ ጌታውን ላለማስቀየም ሲል ወይንም ያስደሰተ መስሎት በማሙሽ አቢይ የሚመራው ፌዴራል መንግሥቱ ላስገደላቸው አማሮች የኅሊና ጸሎት ከለከለ፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም ዓለም ያልታዬ የመጨረሻ ወራዳ እደግመዋለሁ ወደር የማይገኝለት ወራዳ ተግባር ነው፡፡ ከአንድ አገር መሪ እንዲህ ያለ አድልዖና ጭፍንነት አይጠበቅም፡፡ አንድን ትልቅ ሕዝብ ለማዋረድ የተሞከረበት ይህ ክልከላ ብቻውን ይህን መንግሥት በሌላ መንግሥት የሚተካ ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ አቢይ አህመድ በመሠረቱ የአማራን ሕዝብ ገድሎ ለመጨረስ እንደመነሳቱ ከሥሩ የኮለኮላቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሟሎች ሁሉ ፀረ አማራ ሊሆኑ መቻላቸው አይገርምም፡፡ ታገሰ ጫፎም በግልጽ ያስመሰከረው ይህንኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከእንግዲህ ይህ ፓርላማም ሆነ የመንግሥት ሹመኞች ሁሉ አማራን እንደማይወክሉ መታወቅ አለበት፡፡ እንጂ ለይምሰልም እንኳን ቢሆን ለሁለት ሽህ ሟች አይደለም ለአንድም በግፍ ለተገደ ሰው የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት ሲያንስ እንጂ አይበዛበትም፡፡ በሌሎች ሀገሮች እኮ እያየን ነው፡፡ ለምሣሌ በአሜሪካ ለጆርጅ ፍሎይድ የተደረገውን እናስታውሳለን፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ራሱ ተንበርክኮ አይደለም እንዴ እናቱን ይቅርታ የጠየቀው? 27 ሚሊዮን ዶላርስ አይደለም እንዴ ለቤተሰቡ የተሠጠው? ታዲያ ለነዚህ ምስኪን አማሮችስ ቢያንስ ነፍሳቸውን ይማር ተብሎ የኅሊና ጸሎት ቢደረግ ክፋቱ ምንድን ነው? እስከዚህን ይሉኝታቢስ መሆንንስ ከየት ተማሩት? አበስኩ ገበርኩ!!

እንደውነቱ አብኖችን ሳይጨምር ራሱንና ጌታቸውን አቢይን ትዝብት ውስጥ ከመክተት ባለፈ ይህ የአቢይ አሻንጉሊቶች የሞሉበት ፓርላማ ጸሎት አደረገ አላደረገ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ እንኳንስ የነሱ ጸሎት የበቁ አባቶች ዕጥረት ባጋጠመን በዚህ የኃጢኣትና የክፋት ዘመን የብዙዎቻችን ጸሎትና ምህላ ከዳመና በታች እየቀረ ችግሮቻችን ከመቀነስ ይልቅ እየከበዱና ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተዋል፡፡ እንደጸሎቱማ ቢሆን ኖሮ በየአብያተ ክርስቲያን ቀን ከሌት የሚደረገው ሰዓታትና ማኅሌት እንዲሁም ቅዳሴና ሽብሽባ ከአንዲት ደቂቃ የኅሊና ጸሎት አይበልጥም ነበርን? በየመስጂዱ የሚደረገው ሶላትና ስግደትስ ከአንዲት ደቂቃ ጸሎት መብለጥ አቅቶት ነውን? ስለዚህ አቢይ ምንም ሳይቸግረው እንዲሁ ነው የደከመው፡፡ ለነገሩ እንኳንም የነሱ ጸሎት ለሟቾች ቀረባቸው፡፡ ምን ሊጠቅማቸው? ከወንጀለኞች ዋሻ የሚወጣ ጸሎት ለመብረቅ እንጂ ለጽድቅ አያበቃም፡፡ ከአቢያውያን የኅሊና ጸሎት ይልቅ በንጹሓን ደም የጨቀየው የተራሮችና የወንዞች ጩኸት የፈጣሪን ልብ ይበልጥ ያራራል፡፡ ከወንጀለኞቹ አብያውያን የማስመሰልና የታይታ የኅሊና ጸሎት ይልቅ የታራጆቹ ሕጻናት የዋይታ ልቅሶ በጽርሃ አርያም ዘንድ ቀጥተኛ ተቀባይነት አለው፡፡ ስለሆነም አቢይና ታገሰ ጫፎ ሰይጣናዊ ባህርያቸውን ገለጡ እንጂ፣ የክፉ ክፉ ጠባያቸውን አሳዩን እንጂ የከለከሉን ነገር የለም፡፡ መጥፎ ጠባይ ደግሞ ሳያስቀብር አይለቅምና እንዲሁ እንደተጃጃሉና ዓለምን እንዳሳቁ ቀናቸው ትደርሳለች፡፡

አማራም ሆነ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ያለው ሁሉ ከዚህ የክፋት ድርጊት ብዙ መማር ይገባዋል፡፡ ከኅሊና ጸሎት ያነሰ ዋጋ የማይጠይቅ ስጦታ የለም፡፡ ለዚህች ስጦታ ይህን ያህል ትዝብትንም ንቀው እንዲህ ከሆኑ አማራ ላይ ያላቸውን ጥላቻ በሚገባ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ከዚህ አኳያ ለአማራ የሚመደብን በጀትና መሰል ቁሳዊና መዋቅራዊ ድልድል በተመለከተ አማራን እንዴት ሊበድሉበት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡ አንዲት ደቂቃ የኅሊና ጸሎት የነፈጉትን ሕዝብ ለአንድ ከረጪት ማዳበሪያ አራትና አምስት ሽህ ብር ቢያስከፍሉት አይገርምም፡፡ እነሱ ጸልየው ገና ለገና ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይምራል ብለው የፈሩት እነዚህ ጉዶች አንዲት ደቂቃ የኅሊና ጸሎት የከለከሉትን ሕዝብ ለወደፊቱ በያለበት እየሄዱ በጠራራ ጸሐይ እንደማይረሽኑት ማንም እርግጠኛ አይደለም ብቻ ሳይሆን ይህን ታሪካዊ ተልእኳቸውን በቅርቡ በሁሉም የአማራ አካባቢዎች ጭምር እንደሚያቀላጥፉ ከምልክት በዘለለ በተግባር እያየን ነው፡፡

ስለሆነም አማራው ላለመጥፋት ከፈለገ በተለይ በየከተማው “ያዝ እጇን፣ ዝጋ ደጇን” እያለ ዳንኪራ የሚረግጥ የአማራ ወጣት ሁሉ ጮቤ ረገጣውንና ሼሼ ገዳሜውን አቁሞ መታገል ይኖርበታል፡፡ የፋሲካው በግ በገናው በግ እየሳቀ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ሁሉም አማራ ለማለቅ ጥቂት ወራት ብቻ ይበቃሉ፡፡ አንድ እረኛ አንድ ሽህ ከብቶችን እንደሚነዳ ሁሉ ሽመልስና አቢይ የሚመሯቸው ጥቂት ሸኔዎች ይህን ሁሉ ሚሊዮን አማራ ሁሉንም ግን በየተራ አርደው አይጨርሱም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነውና አማራ በየተራ ላለማለቅ አሁኑኑ ይነሳ፡፡ ሌላው ይደረስበታል፡፡ ኅልውናን ማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጠው፡፡ ዛሬ ወለጋ ያለው ሸኔ በመንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ነገ ጧት ጎንደርንና ባህር ዳርን እንዲሁም ደሴንና ወልዲያን አያነድም ማለት አንችልም፡፡ አያያዛቸው ሲዖላዊ ይዘት ያለው ነውና አማራ በቶሎ ከእንቅልፉ ይንቃ፡፡ አማራ እያለቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሙዚቃ ከፍተው የሞንታርቮው ላንቃ እስኪበጠስ ድረስ እያስጮሁ የሚጨፍሩና የሚደንሱ አማሮች ደንቆሮ ናቸው፡፡ እውነቴን ነው እልም ያሉ ደናቁርት  ማይማን ናቸው፡፡ እንኳንስ አማራና ሰው ነኝ ብሎ የሚያስብ የሌላው ነገድ አባል ሁሉ እግዚኦ እያለ ወደላይ መጮህ ይገባዋል፤ የተላከብን የአጋንንት ኃይል ቀላል አይደለምና፡፡ ነገ ደግሞ ተረኛውን ሟች አናውቀውምና፡፡ ያም ከአሁኑ ያስጨንቃልና፡፡ እንዳለ የሚኖር ነገር መቼም የለም ወገኖቼ፡፡ እያየነው!! ስለዚህ ለራሳችን እንዘን፤ ለራሳችን እናልቅስ፡፡ ጊዜው ከፍቷል፡፡

አማራ “ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ” ነው ከሚባለው ብሂል ራሱን አውጥቶ ለማይቀረው የኅልውና ዘመቻ ራሱን ያዘጋጅ፡፡ ብዙ ሆኖ ሳለ ለዚህ መከራ የተዳረገው ርስ በርስ መናበብ ባለመቻሉና ሁነኛ አመራር ባለማግኘቱ ነውና ከሰሞኑ የኦሮሙማ ዕኩይ ድርጊቶች በመማር ኅልውናውን ለማስጠበቅ ጥረት ያድርግ፤ አለበለዚያ “አማራ የሚባል ዘር በዚህች ኦሮምያ ግዛት ውስጥ ይኖር ነበር” ተብሎ በታሪክ ሊጻፍ የሚችልበት አጋጣሚ ከፊት ለፊታችን በአማራጭነት ተገትሮ በግልጽ እየታዬ ነው፡፡ “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይባላልና ኦሮሙማ አማራን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቀላል ትግል አይደለም የተያያዘው – የኅሊና ጸሎትን ከመከልከል ቀላል ነገር ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ ነው አማራን የወጠረው፡፡ አማራ በሰማይም እንዳይጸድቅ እኮ መሆኑ ነው! ምን የመሰለ ጅልነት ነው ግን ወንድሞቼ፡፡ ሰው አእምሮውን ሲስት ለካንስ እንዲህና እስከዚህም ይጃጃላል፡፡ በስማም!! “መጥኔ ለወለደሽ ያገባስ ይፈታሻል” አሉ እመት ዘለቃሽ፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ በሉ እየተገረማችሁ ሰንብቱልኝማ፡፡

Filed in: Amharic