እያዘኑ በመርሳት፣ ከዚያም እየረሱ በማዘን የሚመጣ ለውጥ የለም…!!!
ልደቱ አያሌው
በዓለፉት የአራት ዓመታት ሃደት በማያከራክር መጠን እንዳየነው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የራሱንም ሆነ የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና አፍርሶ እስከሚጨርስ ድረስ በጥፋት ላይ ጥፋትን እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የመታረምና የመለወጥ ዕድል ያለው መንግሥት አይደለም።
መፍትሄ የማግኘት ዕድል የሚኖረን በዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ዙሪያ ያለን የተስፋ እንጥፍጣፊ ተሟጦ ሲያልቅና ከሱ የተሻለ ስርዓት የመፍጠር ብቃትና ኃላፊነት ያለን መሆኑን አምነን ስንቀበል ነው። ከዚህ ውጪ በወቅቱ መንግሥት ዕድሜ መራዘም ለበለጠ አደጋ የመጋለጥ እንጂ እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ሀገር ከህልውና አደጋ የመዳን ዕድል የለንም።
የቱንም ያህል ዕድለ-ቢስ እና ደካሞች ብንሆን በማንኛውም መመዘኛ ከዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የባሰ ደካማና ክፉ መንግሥት ሊያጋጥመን አይችልም፤ አንዳንዶች በየዋህነት ወይም በአውቆ አጥፊነት ሲሉ እንደሚደመጡት ኢትዮጵያ ከዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የተሻለ መንግሥት የመፍጠር ዕድል ከሌላት በእርግጥም ሕዝቧ ከጭፍጨፋ፣ እሷም ከመፍረስ የመዳን ዕድል የላትም።
እንዲህ ዓይነት ሀገርና ሕዝብ ከሆንም መጥፋታችን የማይቀር ብቻ ሳይሆን ልንጠፋም የሚገባን ነን የሚገባን የመሆኑና ያለመሆኑ እውነታ ደግሞ በሌሎች ደግነትና ክፋት ሳይሆን በራሳችን ምርጫ የሚወሰን ነው።
ይህንን እውነታ ከመረዳት ውጪ ጭፍጨፋ በተፈፀመ ቁጥር እያዘኑ በመርሳት ፣ ከዚያም እየረሱ በማዘን የሚመጣ ለውጥና መፍትሄ አይኖርም ።