ስንታየሁ ቸኮል የፕሮፖጋንዳ ስራ ለመስራ ወህኒ ቤት የሄደውን መንግስታዊ ልኡክ አሳፍሮ መለሰ…!!!
ዘሚካኤል ጆርጅ
*…. በፋኖ ላይ ብሎም በመላው የአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን መንግሥታዊ ሽብር ሕጋዊ የሚያስመስል ቀለም መለቅለቅን አላማው ያደረገው ይህ ቡድን በአቶ ስንታየሁ እምቢተኝነት ሳይሳካለት ተመልሷል።
በሰባታሚት ወህኒ ቤት ውስጥ በእነ ስንታየሁ ቸኮል ላይ ፕሮፖጋንዳውን ለመሥራት የሄደው የወራሪው አገዛዝ ሥልጣን ማስቀጠያ ቡድን ሳይሳካለት ተመልሷል። ዛሬ ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ራሱን “በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ማስከበር ዘመቻ አጣሪ ኮሚቴ” ሲል ያስተዋወቀው ከ5 እስከ 6 የሚደርሱ አባላት ያሉት ቡድን በባሕር ዳር፤ ሰባታሚት ወህኒ ቤት ውስጥ እነ ስንታየሁ ቸኮልን ለመሰብሰብና ለማወያየት ሞክሯል። በፋኖ ላይ ብሎም በመላው የአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን መንግሥታዊ ሽብር ሕጋዊ የሚያስመስል ቀለም መለቅለቅን አላማው ያደረው ይህ ቡድን በአቶ ስንታየሁ እምቢተኝነት ሳይሳካለት ተመልሷል።
ስንትሽ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት የቡድኑ አባላት ራሳቸውን እና አጀንዳቸውን እንዲያስተዋውቁት ጠይቋል። ካስተዋወቁ በኋላም “ገለልተኛ የሕዝብ ተወካይ አይደላችሁም። ብትሆኑ ኖሮ ይህ ሁሉ ግፍ ባልተፈፀመም ነበር። መንግሥት ለሚያደርጋቸው ሕገ ወጥ ድርጊቶች ተባባሪዎች ናችሁ። ከእናንተ ጋር አብሬ አልቀመጥም” ብሎ አብሯቸው ሊሰበሰብ እንደማይችል ነግሯቸዋል።
በዚህ ሁኔታ የቡድኑ አባላት የእጅ ስልካቸውን አውጥተው ስንታየሁን ጨምሮ እስረኞችን ቪዲዮ መቅረፅ ጀመሩ። በእስረኞች ተቃውሞ ቀረፃው የተቋረጠ ሲሆን የቀረፁት ሰነድም ተደምስሷል።