>

ጥላቻና ዛፍ ተከላ፤ ቀይና አረንጓዴ አሻራ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጥላቻና ዛፍ ተከላ፤ ቀይና አረንጓዴ አሻራ….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም


የሕግ የበላይነት በአገራችን ተረጋግጦ ቢሆን ኖር ጠ/ር አብይ አህመድ በፓርላማው የመጨረሻው ቆይታቸው አዲስ አበባን እና የኦሮሞን ሕዝብን አስመልክተው ባደረጉት ንግግራቸው አንድ የጥላቻ እና አንድ የሐሰት መረጃ በማሰራጨት ሕግ በመተላለፍ ይጠየቁ ነበር፤

1ኛ/ “አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኦሮሞ ጥላቻ አለ” በሚል በተናገሩት ንግግራቸው የጥላቻና ሕዝብን ለግጭት የሚዳርግ ንግግር አድርገዋል፣ (አዲስ አበባ ውስጥ ለአንድ ወይ ለሌላ ብሔር ጥላቻ ያላቸው ግለሰቦች የሉም እያልኩ አለመሆኑ ይሰመርበት)

2ኛ/ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በስም በተጠቀሱ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የየአገሩ መዝሙር ይዘመራል የሚል የሐሰት መረጃ ለፓርላማውና ለሕዝብ አሰራጭተዋል፤

በእነዚህ ንግግሮቻቸው ብቻ እንኳ የጥላቻ እና የሐሰት መረጃዎች ስርጭቶችን ለመቆጣጠር እራሱ ፖርላማው ባወጣው ሕግ ሊጠየቁ ይገባ ነበር። ይህ ንግግር በአንድ ተራ ፖለቲከኛ ወይም አክቲቪስት ቢነገር በሕግ ማስጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙም ላያስደምም ይችላል። ነገር ግን መቶ ሃ ሚሊዬን ሕዝብ ያለባትን እና የብዙ ብሔሮችና ሀይማኖቶች ስብጥር ያለባትን ሀገር የሚመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን አይነት የጥላቻ እና ማህበረሰቦች መካከል ከፍተኛ ቅራኔን የሚፈጥር ንግግር፤ ሊያውም ፖርላማው ላይ ቀርበውና ሚሊዮኖች በሚያደምጧቸው መድረክ ላይ መናገራቸው ትልቅ የፖለቲካ ክሽፈት ብቻ ሳይሆን የህግ ጥሰትም ነው። በሌላው አለም ቢሆን ክሱንም ይቀምሳሉ፤ አፍንጫቸውንም ተይዘው ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃሉ።

ትላንት መለስ ዜናዊ የቀበረው የጥላቻ መርዝ ዛሬ እርስ በርስ እያባላን ነው። ዛሬ ጠ/ር አብይ ከዛፋ እኩል የሚቀብሩት መርዝ የነገ መጥፊያችን ይሆናል። ሁለት የሚጋጩ አሻራዎች አረንጓዴና ቀይ አሻራ በአንድ መዳፍ ነው የሚሆነው። የጥላቻ እና የሐሰት መረጃ ስርጭት ይቁም! ቢያንስ ሕዝብን ይቅርታ ይጠይቁ። በሕግ አምላክ!

Filed in: Amharic