>

ይድረስ ለብአዴን እንኩቶዎች....!!  (አሳዬ ደርቤ)

ይድረስ ለብአዴን እንኩቶዎች…. !!

አሳዬ ደርቤ


የአማራ ባንክ ሥራ በጀመረበት ቀን በኦሮሚያ ክልል ከተጨፈጨፉ አማራዎች መሀከል እስካሁን የ614 አማራዎች አስከሬን ተቀብሯል፡፡ እናንተ ግን በኦሮሚያ ክልል ከተነጠፈው አስከሬን ይልቅ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገለጽ ኀዘን የአገርን ሕልውና ያጠፋ ይመስል የሚሠራውን የማያውቅ ማቶ ተከትላችሁ መንዘላዘሉን ቀጥላችኋል፡፡

እውን ግን እናንተ ከአማራ አብራክ ወጥታችሁ፣ በአማራ ባሕል ያደጋችሁ አማራዎች ናችሁ? በፍጹም‼️ በሕይወቱ ፈንታ አሟሟቱ ያምር ዘንድ ከሚጸልየው ሕዝብ አብራክ የወጣችሁ ብትሆኑ ኖሮማ ኀዘኑን በማድበስበስ ፈንታ ፍትሕን አረጋግጣችሁ ደሙን ታብሱ ነበር፡፡ ‹‹ቀብሬን አሳምረው›› እያለ እድር ሲመሠርት የኖረው ሕዝብ በራቢስ እንደተለከፈ ውሻ በጅምላ መቃብር ውስጥ ሲገባ ድምጻችሁን አጥፍታችሁ አትመለከቱም ነበር፡፡

እውን ግን እናንተ የአማራን ሕዝብ የምትወክሉ አመራሮች ናችሁ?

በፍጹም‼️

አመራር ብትሆኑ ኖሮማ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን ትተው ግድያውን ያስፈጸሙ ባለሥልጣናት ቀብረር ብለው በኩራት ሲራመዱ እንደ ወንጀለኛ አንገት ደፍታችሁ ከኋላ ከኋላ አትከተሉም ነበር፡፡

እኔ እምለው ግን… ሞራላችሁን፣ ማንነታችሁን፣ ኅሊናችሁን፣ ጥላችሁ በፈርስ የተሞላ ጨጓራሁን እያሻሻችሁ ሕዝባችሁን ለማዋረድና በጅምላ ለማረድ አቅደው ከሚንቀሳቀሱ አረመኔዎች ጎን የምትርመጠመጡት ምኑ እንዳይቀር ፈርታችሁ ነው?

‹‹ሥልጣናችን እንዳይቀርብን›› እንዳትሉ መናገርን፣ ማዘንን፣ ማሰብን፣ ሰዋዊ ሥሜትን፣  የሚነጥቅ ሥልጣን ባርነት እንጂ ሹመት አይባልም፡፡ እኒህን ሁሉ ሰዋዊ ባሕርያት ያጣ ሰው የመቃብር ሳጥን ውስጥ የተጋደመ አስከሬን እንጂ ከአገር ወንበር ላይ የተሾመ ባለሥልጣን አይባልም፡፡

ባንድ ወቅት የቀድሞ ጌታችሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ አፈናውን ማጧጧፍ ሲያስብ ከኦሮሚያ ክልል የወጡ የሕዝብ ተወካዮች አዋጁን ሲቃወሙ እናንተ ግን እጃችሁን ወደላይ ከዘረጋችሁ በኋላ አንገታችሁን ወደ ኋላ አዙራችሁ በግርምትና በፍርሀት ስሜት ስትመለከቷቸው ነበር፡፡ ትናንትናም በዚያው ምክር ቤት ውስጥ ‹‹የሰባት መቶ አማራ ሞት ለአጀንዳ አይበቃም›› ሲባል መቃወሙ ቀርቶባችሁ ዳፍንት እንደያዘው በግ ዐይናችሁን አንሸዋራችሁ በዶክተር ደሳለኝ ድፍረት ስትገረሙ ነበር፡፡ አፈር ብሉ አቦ!

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ባያስበልጡት እንኳን እኩል የሚያደርጉት ሁሉም ጸጋዎች አሉት፡፡ እራሱን አስከብሮ ለመኖር የሚያስችል እውቀትም ሆነ ሐብት፣ የሕዝብ ብዛትም ሆነ የዳበረ እሴት አለው፡፡

ሆኖም ግን የሌሎች ክልል ወገኖቹ የሚወክሏቸውንና የሚታገሉላቸውን ልጆች ወልደው መንግሥት ሲያደርጉ ‹‹የሚከፋፍሉህንና የሚሸጡህን ወልደህ ተዋረድ›› ተብሎ የተረገመው የአማራ ሕዝብ ግን በመንግስት ወንበር ላይ እንደ እናንተ ያለ ጠላት በመሾሙ የተነሳ የማንም መቀለጃ ሆነ፡፡

ትናንት ክልሉ ሲወረር ከበላይ አካል ባገኛችሁት ፍቃድ ‹‹ተነስ›› ስትሉት ጨርቄን ማቄን ሳይል የተነሳውን ፋኖ ከተጠቀማችሁበት በኋላ ሕጋዊ ሆኖ የሚቀጥልበትን መንገድ በማመቻቸት ፈንታ ከዚያው አካል በመጣ መመሪያ መሠረት ‹‹ሕገ-ወጥ›› ተብሎ በአስር ሺህ የሚቆጠር ፋኖ በዘራፊ እጃችሁ ታፈነ፡፡

በቅርቡ ደግሞ በሕይወት መኖር የከለከላቸውን ሰባት መቶ አማራዎች ወደ መቃብር ያወረደው ኃይል ‹‹ለሞቱ ሰዎች ሲደረግ የነበረው የለቅሶ ባሕል ችግኝ በመትከል ተቀይሯል›› የሚል አዋጅ በማውረዱ የተነሳ ይሄንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንደፋደፋችሁ ነው፡፡

ሆኖም ግን ልታዋርዱት የምትሞክሩት ክቡር ሕዝብ ይሄን ውዳቂ አስተሳሰባችሁን የሚሸከምበት ጫንቃ ስለሌለው የኀዘን ቀን አውጃችሁ፣ ባንድራ ዝቅ አድርጋችሁ ተቃውሞውን እና ኀዘኑን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጽ ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻላችሁ ግን በቀጣይ ቀናት ያለእናንተ ይሁንታ ወደ አደባባይ ወጥቶ ኀዘኑን ብቻ ሳይሆን ቁጣውንም ጭምር የሚገልጽ ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic