>

ቀውጦስ የት ነው...??? (በእውቀቱ ስዩም) 

ቀውጦስ የት ነው…???

(በእውቀቱ ስዩም) 

*…. እምቢ በል!

እንኩዋን ከአለቃ ከፈጣሪ ቢመጣ የክፉ ተግባር ተባባሪ አትሁን! እምቢ በል! ክፋትን እምቢ በልና የሚመጣውን ተቀበል!

ከጥንት አዋልድ መጻህፍት ባንዱ ያነበብኩት ታሪክ ይህንን ይመስላል፤  ባንዱ መንደር በሚገኝ ቤተክርስትያን ውስጥ ቅዳሴ ይካሄዳል፤ ወላጆቻውን ተከትለው የመጡ ጥቂት ህጻናት  ወድያ ወዲህ እየተራወጡ ቅዳሴውን መረበሽ ጀመሩ፤ እግዚር ከላይ ሆኖ ሲያይ  ተቆጣ፤ ረባሽ  ህጻናትን እንዲቀስፉ መላእክትን ላካቸው፤ መላእክት ወርደው የህጻናቱን አንገት በሰይፍ መቅላት ጀመሩ፤ በዚህ መሀል አንድ መላእክ ካንድ ህጻን ጋር ተገጣጠመ፤  መላእኩ፥ ህጻኑን የሚቀስፍበት አንጀት አልነበረውም፤ እና የእግዜርን ትእዛዝ ቸል ብሎ ህጻኑን ማረው፤ አሁን የእግዜር ቁጣ ከህጻናቱ ላይ ተነስቶ ትእዛዙን ባልፈጸመው መላእክ ላይ ሆነ ፤ የመላእኩን ክንፍ አሽመደመደው!  መላእኩ ለመብረር ሲሞክር ክፎቹ ከዱት ፤ በቅጡ አስታውሸው ከሆነ ይህ መላእክ ሰሙ ቀውስጦስ ይባላል፤ ከተሳሳትሁ ዲያቆን ሄኖክ ያርመኛል፥

በጥንታዊ ተረካዎች ውስጥ ከማገኛቸው  አንጸባራቂ የሞራል ጀግኖቼ መሀል ግንባር ቀደሙ ነው ፤

የዚህ ትረካ ደራሲ ሊነግረን የፈለገው ምንድነው ? አንኩዋን ከአለቃ ከፈጣሪ ቢመጣ የክፉ  ተግባር ተባባሪ አትሁን! እምቢ በል!  ክፋትን እምቢ በልና የሚመጣውን ተቀበል!

በ1968 አም ማርች ወር ፥ የአሜሪካ ወታደሮች በአንድ ማይ ላይ  በተባለች የቤትናም መንደር ውስጥ ገስግሰው ደረሱ፤ ብዙም ሳይቆዩ ሰላማዊውን መንደርተኛ  አሰልፈው መረሸን ጀመሩ፤ ህጻን ፥ ሴት ፥ አሮጊት ፥ ውሻ አልቀራቸውም፤ በጭካኔ የተለከፈ ፍጡር በመግደል ብቻ አይረካም፤   እንኳን ላይን ሰለጆሮ የሚቀፉ ጭካኔዎችን ሁሉ ፈጸሙ’

ባካባቢው በሂሊኮፍተር ሆኖ ቅኝት ሲያደርግ የነበረ ሌላ አሜሪካ የጦር መሪ ሲያልፍ የባሩድ ጭስ ተመልክቶ ወረደ፤  መሬት ላይ  የሚካሄደውን ሲመለከት አይኑን ማመን አቃተው፤  ወገኖቹ ግድያውን ባስቸኳይ  እንዲያቆሙ ጠየቀ! በደም የሰከረው  የገዳይ ወታደሮች አለቃ  ይህንን ጥሪ መስማት አልፈቀደም፤  ቶምሰን ጭፍሮቹን አሰልፎ “ ግድያውን አቁሙ !   አለበለዝያ ወታደሮቼ በአናንተ ላይ እንዲተኩስ አዛቸዋለሁ ፤ ‘ሲል ለፈፈ  ፤ በሁለት የአሜሪካ የጦር ክፍሎች  መካከል ውጥረት ሰፈነ፤ ከብዙ  ፍጥጫ  በሁዋላ አምስት መቶ ሰላማዊ ሰዎችን የፈጀው ጭፍጨፋ ተገታ፤

የሚገርመው እነዚያ በጭፍጨፋው ላይ ከተሳተፉት ወታደሮች አንዳንዶቹ ሁኔታው ካለፈ በሁዋላ ጸጸት ረፍት ነሳቸው ፤ ጥቂቶቹ  ራሳቸውን እየገደሉ ተገላገሉ፤  ገዳይም ብትሆን ከሰውነት መስፈርቶች ጥቂቶችን የምታሟላ  ከሆንህ የሚወቅስ ህሊና ይኖርሀል ፤

ባገራችን ጭካኔ የባህላችን አንዱ ዘርፍ ቢሆንም ባለፉት አራት አመታት የተደረገውና የሚደረገው ስም አይገኝለትም፤ ስነምግባር  የነጠፈበት አገር መሆኑ ታይቷል፤  በቡድን መግደል፥ በቡድን መድፈር የተለመደ ነው ፤ ግን ከገዳዮች መካከል አንዱ እንኳን “ ወገኖቼም ብትሆኑ እንድትገደሉ አልፈቅድላችሁም፤ ወገኖቼ  ባይሆኑም እንዲሞቱ አልፈልግም “  የሚል ድምጽ ያለው ሰው  መጥፋቱ አያሳዝንም? እንደ ቀውጦስ “    ከአምላክ  እንኳ ቢመጣ ክፉ ትእዛዝ ክፉ  ነውና አልፈጽምም “ የሚል አለመኖሩ አይገረምም?  ጠመንጃ የታጠቀ ግዙፍ ሰውየ በህጻን ልጅ ላይ ሲተኩስ ሌላው ከቦ የሚጨፍርበት  ክፋት ላይ የደረስነው በምን በኩል ተጉዘን ነው?

Filed in: Amharic