ባልደራስ
የፋኖ አደረጃጀቶች ወለጋን ጨምሮ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንዲሰማሩ ጠየቀ!!
የአማራ ህዝባዊ ኃይል (ፋኖ) በምዕራብ ወለጋ በአማራ ላይ የተፈፀመዉን የዘር ጥቃት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
“የአማራ ህዝብ በሀገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ህዝብ መብቱ ተከብሮ እንዳይኖር የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች መዋቅራዊ የዘር ፍጅት ወንጀል ካወጁበት ቆይቷል” ብሏል።
በተለይም የአማራ ማህበረሰብ በብዛት በሚኖርበት የወለጋ አካባቢ፣ ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ በሽህ የሚቆጠሩ ንፁሃን አማራወች በማንነታቸው ምክንያት እየተጨፈጨፉ ናቸው ብሏል።
በዚህ ድባብ፣ “መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ አደረኩ የሚልባቸው የፋኖ አደረጃጀቶች በሙሉ አመራር ያላቸው እና የፖለቲካ ጥያቄም ያላቸው በመሆኑ፣ የተጀመረው ዘመቻ ተቋርጦ ከእነኝህ የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር ውይይት እንዲጀመር፣ ጥያቄው ፖለቲካዊ ምላሽ እንዲያገኝ እና የፋኖ አደረጃጀቶች ወለጋን ጨምሮ ችግር ባለባቸው ሁሉም አካባቢወች ተሰማርተው የህዝባቸውን ህልዉና የሚጠብቁበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ እንዲሁም እስካሁን በተደረገው ዘመቻ ያለአግባብ በየማጎሪያ ካምፖች እና እስርቤቶች የገቡ ንፁሃን ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል።
በመጨረሻም፣ በዘር ማጥፋት ወንጀሉ ሰለባ በሆኑ የወለጋ አማራወች እልቂት ምክንያት ሀዘን ላይ ላሉት ሁሉ መፅናናትን ተመኝቷል።