>

ታሪክ ሠሪነት እና ታሪክ አውሪነት...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ታሪክ ሠሪነት እና ታሪክ አውሪነት…!!!

አሳፍ ሀይሉ

*…. ታሪክ ሠሪው ሊንከን፣ ታሪክ ሠሪው ምኒልክ፣ እና ታሪክ አውሪዎቹ እኛ…!!!

አዎ፡፡ “የተከፋፈለ ቤት ይፈርሳል”፡፡ የክርስቶስ ቃል ነው። አብርሃም ሊንከንም ብሎታል። የአሜሪካው መሪ አብርሃም ሊንከን ያን የተከፋፈለ ቤት በሁሉም ላይ ከመፍረሱ በፊት በአንድ ጠንካራ ምሰሶ ለማቆም የመረጠ ጀግና ነው፡፡

የሀገርን ምሰሶ ወዲህና ወዲያ ሆነን እየነቀነቅን ስንጓተት ሀገር ልትደረመስ ነው፡፡ ዓይናችን እያየ ሀገር አትከፈልም – እኛ ባይሆን በየያዝነው አቋም ጎራችንን ለይተን እንቁምና ቁርጣችን ይለይልን! ሀሳብ ተካፍለን ስለ ሀገር ለመስማማት ካልቻልን – በሀሳብ ተከፋፍለን ስለ ሀገር እንዋጋ፡፡…

ከእኛ ሁለት አንዳችን እንለፍ – እና አሸናፊው ሀገርን በመረጠው መንገድ ይምራ! እኛ ብናልፍ ቢያንስ ሀገራችንን እናተርፋለን! ሀገር አንድ ሆና ትቆይልን! ተከፋፍለን እንፈርሳለን! ተከፍለን እንዋጋና አሸናፊው በራሱ መንገድ ሀገሪቱን ያስተዳድር ብሎ መረጠ፡፡

እና አብርሃም ሊንከን ተገዶ በገባበት ጦርነት አሸነፈ፡፡ ደቡቦቹ ኮንፌዴሬቶች ተሸነፉ፡፡ እና የአብርሃም ሊንከኗ አሜሪካ ሳትፈራርስ በብልጽግና ጎዳና መገስገሷን ቀጠለች፡፡

ዛሬ የአብርሃም ሊንከን መታሰቢያ ኃውልት በዋይት ሃውስ በትልቁ ተቀርጾ የመጣ መሪ ሁሉ ይሳለመዋል፡፡

በደቡቦቹ የአሜሪካ የቀድሞ ኮንፌዴሬት ግዛቶች ውስጥ ግን እስከቅርብ ጊዜ የአብርሃም ሊንከን ኃውልት እኛን አይወክልም፣ ይፍረስልን – የሚሉ ተቃውሞዎች በየጊዜው ይነሳሉ፡፡

የአብርሃም ሊንከንን ግለ-ታሪክ በመጽሐፍ መልክ ሲታተም ሁሌም ገለልተኝነቱ ውዝግብ እንዳስነሳ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ፣ በአብርሃም ሊንከን ዙሪያ ፊልሞችን ለመሥራት የማይታሰብ ሆኖ ብዙ ዘመናት አልፈው ነበር፡፡ ጥቂት ፊልሞች ሲሰሩም የአሜሪካን ህዝብ ጎራ አስለይተው አወዛግበዋል!

አብርሃም ሊንከን ዛሬ ቆማ የምናያትን የታላቋን አሜሪካ ታሪክ ሠርቶ ያለፈ ‹‹ታሪክ-ሠሪ›› ሰው፣ እና ‹‹ታሪክ-ሠሪ›› ዜጋ፣ እና ታሪክ-ሠሪ አሜሪካዊ ልዕለ ሰብዕና ነው!

አብርሃም ሊንከን ፀረ-ባርነት መፈክርን ያነገበው አሜሪካንን አንድ ለማድረግ ስለሚያግዘው ነው! እኔ አይደለም ያልኩት። በራሱ አንደበት የተናገረው ነው። ፀረ-ባርነት መፈክርን ሲያነሳ፣ ዋናው ትልሙ ታላቋ አሜሪካ ነበረች!

ብዙዎች ተመሣሣይ ትልም ኖሯቸው – ዋጋውን መክፈል ፈርተው ሲሸሹ – አብርሃም ሊንከን ግን – ስለዚያች ስለሚያልማት ታላቋ አሜሪካ – የሚገባውን ዋጋ ከፍሎ አልፎላታል!

አብርሃም ሊንከን አሜሪካኖችን አንድ አድርጎ ያለፈ ታሪካዊ መሪ ነው፡፡ በአብርሃም ሊንከን መርህ በምትመራ ሀገር በአንድነት ይኖራሉ፡፡

አሜሪካኖች በታሪክ አንድ አይደሉም፡፡ በታሪክ ይጨቃጨቃሉ፡፡ በብልጽግና ጎዳና ግን እጅ ለእጅ ተያይዘው ቀን ከሌት ይታትራሉ፡፡ በሀገር ጉዳይ ‹‹አሜሪካኒዝም›› ከባድ የሀገራዊ አርበኝነት መጠሪያ ቃል ሆኗል፡፡ ሁሉም በኩራትና በእብሪት ‹‹አሜሪካዊ ነኝ!›› ነው የሚሉህ፡፡ በሀገራቸው ቀልድ የለም!

በታሪካቸው ግን ይነታረካሉ! ታሪክ የብዙ ነገሮች መሠረት የሆነውን ያህል – ሀገር እና ትውልድ ማለት ደግሞ – ሙሉ ለሙሉ ‹‹ታሪክ ብቻ›› አይደለም! ታሪክ ሁሉንም ነገር አይደለም!

በታሪክ የምናገዝፈውና የምናንኳስሰው ሊለያይብን ይችላል፡፡ የምናመልከው ሊለያይብን ይችላል፡፡ ሞዴሎቻችንና አይከኖቻችን ሊለያዩብን ይችላሉ፡፡ በብዙ ፍላጎቶቻችንና የታሪክ አረዳዶቻችን ተለያይተን – በመሠረታዊ አስፈላጊ ነገሮቻችን እና በሀገራችን ጉዳይ ግን አንድ ልብ ሆነን በአንድ ላይ ተያይዘን መቆም እንድንችል ሆነን መገኘትም እንችላለን፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያውያን – እንደ ሀገር ዜጋ – በዘመኑ ሀገር ይዘን እንደተገኘን ትውልዶች – እኛ ኢትዮጵያውያን ያጣነው ይሄንን ነው! ታሪክን የሚሠራ ትውልድ የሚፈለገውም በዚህና ለዚህ ምክንያት ነው!

ታሪክ ሠሪ ነበረን። ግን እሣት አመድ ወለደ። ሀገር እንዴት እንደሚሠራ፣ ትውልድ እንዴት እንደሚቀና፣ ከምኒልክ የቀደመ ምሣሌ አላገኝም። ምኒልክ የኢትዮጵያ አብርሃም ሊንከን ነው! ታሪክ ሠሪ ነው!

በብዙ የዓለም ተመልካች አስተያየት፣ ምኒልክ ከውጪም ከውስጥም ተጋፊዎቿ ጋር ተናንቆ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ በሁለት እግሮቿ ያቆመ ታላቅ ታሪክ ሠሪ፣ ታላቅ የጦር መሪ፣ ታላቅ ሀገር-መሪ ንጉሥ ነው! ምኒልክ ታሪክ ሠሪ ነው! ስለሆነም ነው ኃውልት የቆመለት፡፡

ዛሬ ታሪክ ሠሪ ትውልድ ሲጠፋ – ስለ ታሪክ ሠሪዎች – እና ስለ ታሪክ ሠሪዎች ኃውልት የሚነታረክ ትውልድ ሀገሩን ሞላው!

ይሄ አሁን የንትርካችን ምንጭ የሆነው ገናናው ምኒልክ ‹‹ዳግማዊ›› ነው፡፡ ምኒልክ ‹‹ቀዳማዊ››ን የፈጠረችው ታሪክን ለመሥራት የቆረጠች የኢትዮጵያ ንግሥት ሣባ ነበረች፡፡ በመቀመጥና በማውራት የተሠራ አንዳችም የዓለም ታሪክ የለም! ታሪክ የተሠራው እና የሚሠራው በተግባር ብቻ ነው!

አሜሪካ አብርሃም ሊንከን አላት፡፡ ጀርመን ቢስማርክ አለው፡፡ ፈረንሣይ ሻርለማኝ አለው፡፡ ናፖሊዮን፣ ደጎል አለው፡፡ እንግሊዝ ቸርችል አላት፡፡ ኢትዮጵያም ምኒልክ ዳግማዊ ነበራት፡፡ አሁን ማንም የላትም፡፡ ሌላ ታሪክ ሠሪ መሪ፣ ታሪክ ሠሪ ዜጋ፣ ታሪክ ሠሪ ትውልድ ያስፈልጋታል! ሌላ ‹‹ሣልሳዊ›› ምኒልክ ያስፈልገናል!

የኢትዮጵያ ወጣት ታሪክ ሠርቶ የራሱን ታሪክ ለማጻፍ ማሰብ አለበት፡፡ ማሰብ ብቻ ሳይሆን መዘጋጀትም አለበት! ከዚህ ትውልድ የወጣ ታላቅ ኃውልት የሚቆምለት ባለታላቅ ራዕይ ኢትዮጵያዊ ሊፈጠር የግድ ይላል!

ታሪክ አውሪዎች ብቻ ሳይሆን – ታሪክ ሠሪዎች ያስፈልጉናል! ወጣት ሳለህ እሩጥ – አባት ሳለህ አጊጥ ነው! ወጣቱ ለታላቅ ሀገራዊ ህልም እና ለታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ራሱን አጭቶ – ሩቅ አስቦ መነሳት የሚገባው ጊዜ አሁን ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ የሚያደርገው አባት መሪ የለውም! እንደ ሀገር ምሰሷችን እየተነቀነቀ ስንናወጥ፣ በውጪም በውስጥም ያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጦር አደርጅተው፣ ጉልበት አፈርጥመው፣ ነጋሪት ጎስመው ጦር እየነቀነቁ እያየን – ዓይናችንን ካልወጉት ምንም የማይጎረብጠን – ሀገር በላያችን እስክትፈርስ እጃችንን አጣጥፈን የምንጠብቅ – በዓለም ታሪክ ተሰምተንም ታይተንም የማናውቅ አስገራሚ የቅርብ ታሪክ ተመልካቾች ሆነናል!

ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ከተሰመረለት የጎሳና የመንደር መናኛ አስተሳሰብ ወጥቶ – እንደ ዳግማዊ ምኒልክ – ዳግም ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ሁሉ ጮራው የሚያንፀባርቅ ታላቅ ታሪክን ለመሥራት ራሱን በአዕምሮና በአካል ማዘጋጀት አለበት!

ስለ ታሪክ እያወሩ የቀድሞ አባቶቻችን በሠሩት ታሪክ ብቻ አሁኑን እና ወደፊቱን መኖር አይቻልም፡፡ ወይ ታሪክ ሠሪ አሊያም ታሪክ አውሪ ሆኖ ማለፍ ነው ያለው ምርጫ! ታሪክ ሠሪ ሆኖ ለማለፍ የቆረጠ ትውልድ ከዚህ ትውልድ መፈጠር አለበት!

አሁን – ከምንም ጊዜ በላይ – ኢትዮጵያ – ታሪክን ለማውራት ቆርጦ የተነሳ ትውልድ ብቻ ሳይሆን – ታሪክን ለመሥራት ቆርጦ የተነሣ ትውልድ ያስፈልጋታል!

ታሪክን ሥራ! እና ባለታሪክ ሁን! ባለ ታሪክ ሆነህ የጀግንነትህ ኃውልት እንዲገነባልህ ሁን! አንድ ቀን በትውልድ ሁሉ የምትታወስ – በሠራኸው ታሪክ የምትነሳ – የምትጠላም የምትወደድም – ታላቅ ታሪክ ሠሪ ለመሆን ተነሣ! ታሪክ ሠሪ ለመሆን ተነሺ!

ሀገር የሚቆመው በእልፍኝ ወሬና በጥቃቅን ምናምንቴ ህልሞች አይደለም! ታላቅን ነገር ለሀገራችን እንሠራለን ብለው  – ታሪክን ለመሥራት – የጀግኖቻቸውን አደራ ለመወጣት በተነሱ ቆራጥ ወጣቶች ተግባር ነው ሀገር የሚቆመው!

እናንት የኢትዮጵያ ወጣቶች – ዳግመኛ ታላቅ ታሪክን ለመሥራት – እና በታሪክ ፊት ለመታወስ – እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ለሀገራችሁ አብሩ! አብሩ ለሀገር! ተነሱ ለሀገር!

ተነሱ እና እንደ ምኒልክ በዓለም የምትታወሱበትን ታላቅ ታሪክ ሥሩ! እንደ ሊንከን በዓለም የምትታወሱበትን ታሪክ ለመሥራት አዕምሯችሁን አዘጋጁ!

አሊያ ግን ጥጋችሁን ይዛችሁ አውሩ! ሀገር አጥፊዎች ታሪክን ለመሥራት ሲጉተመተሙ ዝም ብላችሁ ያለፈን ታሪክ አውሩ! እጃችሁን አጣጥፋችሁ፣ አዕምሯችሁን አሸልባችሁ በምንቸገረኝ ኑሩ! እና በታሪክ ትዝታ ውልም ሳትሉ ከነታሪካችሁ ተረስታችሁ ቅሩ!

«እኛ በታሪክ የተገነባን ብቻ አይደለንም፡፡ ታሪክ ሠሪዎችም ነን እንጂ፡፡»

“We are not only made by history. We are makers of history.”

— Abraham Lincoln

አምላክ ኢትዮጵያችንን ይባርክ።

 

Filed in: Amharic