>

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ  መግለጫ፤

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ  መግለጫ፤

 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አስመልክቶ የወሰደው አቋም የተጣለበትን ኃላፊነት የማይመጥን እና ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

1. ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተከትሎ የፓርቲያችን አመራር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ምክር ቤቱ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት አስመልክቶ በአስቸኳይ አጀንዳነት ይዞ ውይይት እንዲያደረግ ጥያቄ ቢያቀርቡም የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የሆኑት የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ምክር ቤቱ በአጀንዳነት ከተያዙ ጉዳዮች ውጭ ያሉ አሰቸኳይ ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር በሕግ የተፈቀደለት ሲሆን ፣ አስቸኳይ ጉዳዮችን በተመለከተ በሕግ ያልተገደበ እና ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ሲፈቅድ ጥያቄውን ማስተናገድ እንደሚቻል በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በክቡር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ እና በክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ መካከል ከተከናወነው ምልልስ ቪዲዮ ላይ በግልጽ እንደሚታየው የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ ጥሰው “በአጀንዳ ባልተያዘ ጉዳይ ላይ አንወያየም” በማለት በአስቸኳይ ጉዳይነት እንዲያዝ የተጠየቀውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ ውድቅ አድርገዋል፡፡

በፓርቲያችን አመራር እና የምክር ቤቱ አባል በሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የቀረበው ጥያቄ ምክር ቤቱ የሚመራበትን ደንብ እና ሥርአት መሰረት አድርጎ የቀረበ አስቸኳይ ጉዳይ ሲሆን ፣ ምክር ቤቱ በይፋዊ ማኅበራዊ ድረገጾች ባወጣው አጭር መግለጫ በአጀንዳነት ከተያዙ ጉዳዮች ውጭ ያሉ አስቸኳይ ጉዳዮችን ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር በሕግ የተፈቀደለት ለመሆኑ የሚያረጋግጠውን የሕጉን ክፍል የለጠፈ ቢሆንም ፣ “ምክር ቤቱ የውይይት እና የምክክር እንጅ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ መሆን የለበትም” በማለት የዘር ማጥፋት ወንጀልን በሚመለከት የቀረበን አጀንዳ ተራ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ ነው ሲል ተሳልቋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ በአጀንዳነት ያልተያዘ አስቸኳይ ጉዳይን የማስተናገድ በሕግ የተፈቀደ እና ያልተገደበ ሙሉ ሥልጣን እያላቸው ፣ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው ፣ ምክር ቤቱ ባወጣው አጭር መግለጫ የብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ስጋት የሆነውን እና ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ የሚከትን የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚመለከት ጉዳይ “ተራ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ” ሲል መሳለቁ ፣ ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ፣ የአማራን ሕዝብ እና መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውንን ያሳዘነ፣ ምክር ቤቱ የተጣለበትን አደራ ያጎደለ ተግባር ሆኖ አግኝተንዋል፡፡

2. ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ እጅግ አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ መንግስት እየወስድኩት ነው ከሚለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ካሉ ቅሬታዎች ጋር ተዳብሎ እንዲጣራ የጤና ፣ ማኅበራዊ ፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አጣርቶ እንዲቀርብ የሰጡት ቀን ያልተቆረጠለት ትዕዛዝ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የማይመጥን እና እጅግ የዘገየ ከመሆኑም በላይ ፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪ በሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን እልቂት አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ባለስልጣናት ባልካዱበት ሁኔታ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከሚነሱ ቅሬታዎች እኩል ተጣርቶ እንዲቀርብ ማዘዛቸው ክቡር አፈጉባኤው እና የተከበረው ምክር ቤት ጉዳዩን የያዘበትን አግባብ ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች የደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል አስመልክቶ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የሰጡት የይጣራ ትዕዛዝ ቀን ያልተቆረጠለት እና ብዙ ውስንነት እያለበትም ቢሆን ጥረቱን የሚያበረታታ ሲሆን ፣ ክቡር አፈጉባኤው እና የተከበረው ምክርቤት እስካሁን ሀገር ባወቀው ጉዳት ልክ የሚመጥን ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ዳተኛ መሆናቸው ፓርቲያችንን አሳስቦታል፡፡ በበርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ዘገባ መሰረት እና ከታመኑ ምንጮች በተገኝ መረጃ እስካሁን ድረስ ቢያንስ 600 (ስድስት መቶ) የቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ተገድለው በጅምላ ቀብራቸው የተፈጸመ ፣ ሌሎች በርካቶች ተጠቂዎች ቀብራቸው ተፈጽሞ ያላለቀ ስለመሆኑ እና በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተገቢውን እርዳታ እና ድጋፍ አጥተው እየተንገላቱ ስለመሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ፣ ምክርቤቱ እስካሁን በታወቀው ጉዳት ልክ ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወስድ በተገባው ነበር፡፡  ስለሆነም አብን ለክቡር አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና ለተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚከተለውን ጥሪ ያስተላልፋል፦

1. የተከበሩ አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ በምክር ቤቱ አባል ክቡር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የቀረበላቸውን አስቸኳይ ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲቀበሉ እና ምክር ቤቱ በቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች በተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አስመልክቶ ውይይት እንዲያደረግ እና በጉዳዩ ላይ ተገቢውን አቋም እንዲያዝ እንዲደርግ፤

2. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና የሚመሩት መንግስታቸው የሀገራችን እና ሕዝቦቿን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እና በቂ የጸጥታ ኃይል የገነቡ ለመሆኑ በተደጋጋሚ ማረጋገጫ እየሰጡ ባለበት ወቅት ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ሳያቋርጥ እያሰለሰ የቀጠለውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለማስቆም ያልቻሉበትን እና የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ተፈናቃዮች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረስ ያልቻሉበተን ምክንያት በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ እንዲታዘዙልን፤

3. በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በተከታታይ እና በመደበኛ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የዘር ፍጅት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጨባጭ ፣ ግልጽ እና ተገማች አደጋ (Clear and Present Danger) በመሆኑ ፣ የችግሩ ምንጭ የሆኑ የሕግ ፣ የመዋቅር እና የሥርአት-አቀፍ ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ እና ችግሩ ወደለየለት እና አጠቃላይ የዘር ፍጅት (Full-Scale Genocide)ከመድረሱ በፊት አደጋውን መከላከል የሚቻለው የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ ፣ ስትራቴጅ ፣ ሕግ እና አሰራር (National Mechanism for the Prevention of Genocide and other Atrocious Crimes) ሥራ ላይ በማዋል በመሆኑ ፣ የተከበረው ምክር ቤት ፖሊሲውን እና አሰራሩን ሥራ ላይ በማዋል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ፣ በማያበራ የዘር ፍጅት እልቂት ውስጥ ለሚገኝው የአማራ ሕዝብ እና ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን እንመኛለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ

ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም

Filed in: Amharic