>

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪ...!!!

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪ…!!!

“በአማራ ላይ የሚፈፀመውን ጭፍጨፋ ሁሉም የክልል መስተዳድሮች በግልጽ እንዲያወግዙት” ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ…!!!

ፓርቲው ዛሬ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የብልጽግና መንግሥት ሕግን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ማጥቂያ አደረገው እንጂ የሕግ የበላይነትን ማስፈን አልቻለም” ብሏል።

ፓርቱው ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት፣ ለተለያዩ የሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ፣ ለአህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ባደረገው ጥሪ “መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ ስልታዊ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ዘመቻ እያደረገ ነው” ሲል ገልጿል። ድርጊቱ

“በመንግሥት ውስጥ በተሰገሰጉ ሰርጎ ገቦች የሚደገፍ ነው” በማለት ባልደራስ ባወጣው መግለጫ ተናግሯል።

ፓርቲው አክሎ ” እየተፈፀሙ ያሉ የዘር ፍጅቶች፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት ፣ ጎሰኝነት፣ አድር ባይነት እና ቅጥ ያጣ ሙስና የሥርዓቱ መክሸፍ ማሳያዎች ናቸው ” ብሏል።

መንግሥትን እያገለገሉ የሚገኙ ባለሥልጣናት ከሕግና ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማይድኑ የሚገልጸው የባልደራስ መግለጫ ባለሥልጣናቱ “አቋም እንዲያስተካክሉ” ጠይቋል። አክሎም አማራን ለሚጠሉ ያላቸው ኃይሎች የፖለቲካ ሽፋን እየሰጡ ነው ያላቸው የአማራ ክልል ባለስልጣናት አካሄዳቸውን እንዲያርሙ ጠይቋም።

ባልደራስ እየደረሰ ላለው ግድያ ችግሩን ይፈታል በሚል ” በኦሮሚያ ክልል የአማራ ልዩ ዞኖች እንዲቋቋሙ” በማለት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን የተፈቀደበትን ራስን በራስ የማስተዳደር የአሥተዳደር መዋቅር በመፍትሔነት ለአብነት ጠቅሷል። ፓርቲው ልዩ ልዩ አህጉራዊ ( አፍሪካ ሕብረት ) ፣ ዓለም አቀፍ ( የተባበሩት መንግሥታት ) ድርጅቶች

” በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የዘር ፍጅት እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ” በማለት የገለፀውን ወንጀል እንዲያወግዙ እና በመንግሥት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ እንዲያሳድሩ ብሎም ወንጀሉ ቆሞ ወንጀለኞችም ለፍትሕ እንዲቀርቡ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ “በዘር ፣ በሃይማኖት ፣ በብሔር ሳይከፋፈል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአገር ለዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ፀንቶ እንዲቆም ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

ዘገባ ፤ ሰለሞን ሙጬ DW ከአዲስ አበባ

Filed in: Amharic