>

አብይ አህመድ አገር መምራት አልቻለም፣ መሄድ አለበት...!!! (ግርማ ካሳ)

አብይ አህመድ አገር መምራት አልቻለም፣ መሄድ አለበት…!!

ግርማ ካሳ


የብልጽግና መንግስት ሕወሃት ይጠላ ከነበረው በባሰ ሁኔታ በሕዝብ እየተጠላ የመጣ ስለመሆኑ የሚከራከር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

እነ አብይ አህመድ ከኦሮሞ ድርጅት የመጡ ናቸው፡፡ ግን ምን ያህል የኦሮሞ ማህበረሰብ ይደገፋቸዋል ብለን ብንጠይቅ መልሱ ከባድ አይመስለኝም፡፡ በምርጫው ወቅት ብቻቸውን ተወዳድረው 100% አሸነፍን ያሉት እንደማይመረጡ ስለገባቸው ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅትም አብዛኛውን የኦሮሞ ወጣት እየገደሉ፣ እያሰሩ፣ እያፈኑ ጨፍልቀው ነው የያዙት፡፡  የተወሰኑትን በጥቅም በመያዝ፣ በነ አዲስ አበባ ስራዎችን በመስጠት፣ በኦሮሞ ልዩ ኅይል ውስጥ በማስገባት ወዘተ የነርሱ መጠቀሚያ እያደረጓቸው ነው፡፡ ቀላል የማይባሉ ሌሎች ደግሞ ኦነግን እየተቀላቀሉ ነው፡፡

የኦሮሞ ክልል አራቱ የወለጋ ዞኖች (ምስራቅ፣ ምእራብ፣ ቄሌምና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ)፣ ከሸዋ አራት ዞኖች (ምስራቅ፣ ሰሜንና ምእራብ ሸዋ)፣ የጉጂና የጉጂ ምእራብ ዞኖች፣ የቦረና ዞን ፣ ሲደመሩ ከሃያ አስር የሚደርሱ የኦሮሞ ክልል ዞኖች ሰላምና መረጋጋት የሌለባቸው ናቸው፡፡

በቅርቡ  በም እራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የተፈጸመው፣ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ የሞቱበትን  አሰቃቂ የአማራዎች ጭፍጨፋን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፡፡

የአብይ አህመድ ኦህዴድ ብልጽግና በኦሮሞ ክልል  በሕዝብ መጠላት ብቻ አይደለም፣ በክልሉ ሰላም፣ መረጋጋትና አስፍኖ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አልቻለም፡፡ አንድ በሉ፡፡

ትግራይ ሙሉ ለሙሉ ከብልጽግና ቁጥጥር ውጭ ናት፡፡ ከትግራይ ማህበረሰብ ጋር ብልጽግናዎች ላይታረቁ ተፋተዋል፡፡ መብራት፣ ኔትዎርክ ወዘተ እንዲዘጋ አድርገው ሕወሃት በሚፈጽመው ግፍ ላይ፣ እነርሱም ተጨምረው የትግራይን ሕዝብ መከራ አባዝተውታል፡፡  ወይ ሕወሃትን አሸንፈውና ደምስሰው ህዝቡ እንዲረጋጋ አላደረጉም፤ እንደ እንድ  አገር መንግስት፤  ወይም ተደራድርው ችግሮችን አልፈቱም፡፡ ነገሮች በእንጥልጥል ይዘው፣  የሕዝብ ስቃይን እያስቀጠሉና እያራዘሙ ነው ያሉት፡፡

የአብይ አህመድ፣  የትግራይ ማህበረስብ ክብር የሚነኩ ፣ ብዙ ጸያፍ ንግግሮቹ በተጋሩ አይምሮ ውስጥም  አሉ፡፡ በትግራይ ተወላጆች ላይ በጅምላ ብልጽግና ያደረገው እስርና እንግልትም የሚታወስ ነው፡፡

ብልጽግና በትግራይ ሕዝብ መጠላት ብቻ አይደለም፣ በክልሉ ሰላም፣ መረጋጋትና አስፍኖ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አልቻለም፡፡ ሁለት በሉ፡፡

ወደ አማራው ማህበረስብ ስንሄድ  በበልጽግናች  ላይ ያለው ጥላቻ በሚያስገርም መልኩ ጣራ መድረስ አይደለም፣ ጣራዉን በጥሶ ወደ ላይ እየተተኮሰ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብልጽግና መሆን አይደለም፣ ከብልጽግናዎች ጋር በአንድ መድረክ መቀመጥ እራሱ ችግር ውስጥ የሚከተበት ጊዜ ሆኗል፡፡

እነ አብይ አህመድ፣ እንደ አማራ  ማህበረሰብ የደገፋቸው አልነበረም፡፡ አሁን ግን ከአማራው ማህበረሰብ ልብ ውስጥ ተሰርዘዋል፡፡ የአብይ አህመድ አገዛዝ፣ በኦሮሞ ክልል፣ በቤኔሻንጉል ወዘተ ያላቋረጠው የአማራዎች መዋቅራዊና ስራዓታዊ ጭፍጨፋ እንኳን ሊያስቆም እንደውም በተዘዋዋሪ መንገድ እየደገፈ መሆኑ ብዙዎችን እያበሳጨ ነው፡፡ የሕዝቡ ልጆች በሆኑ ላይ፣ በፋኖዎች ላይ ጦርነት መክታቸው በሕዝቡ እንደ ጠላትና አማራ ጠል እንዲቆጠሩ አድርጓቸዋል፡፡

በአማራ ክልል በኦሮሚይ ብሄረሰብ ዞን ኦነግ፣ በዋገመራ ዞን እና በስሜን ጎንደር ዞን ባሉ በርካታ ወረዳዎች አሁንም በሕወሃት ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡  ጠለምትና ራያም እንደዚሁ፡፡   በሕወሃትና ኦነግ ስር ካሉ የአማራ ክልል ዞኖችን ወረዳዎች ውጭ ያሉ አካባቢዎች ደግሞ ብልጽግናዎች  ከፋኖ ጋር በጀመሩት ጦርነት በሉት ግጭት ወደ ሰላም መታወክ እየሄዱ ነው፡፡ በአጭሩ በመላው የአማራ ክልል አለመረጋጋት የተከሰተበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ብልጽግና በሕዝብ መጠላት ብቻ አይደለም፣ በአማራ ክልል ሰላም፣ መረጋጋትና አስፍኖ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አልቻለም፡፡ ሶስት በሉ፡፡

ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ አብይ አህመድና ብልጽግና በአንዳንድ ማእዘናት አዎን የተወሰነ  ድጋፍ ቢኖራቸውም፣ አብዛኛው አዲስ አበቤ ግን  በነርሱ ላይ ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡

መንግስት እንደመሆናቸው፣ ባንኩ በእጃቸው ስንደመሆኑ፣ የስርዓቱ ተጠቃሚ ፣ በገንዘብና በጥቅም ከነሱ ጎን ያሰለፏቸው ቀላል አይደለም፡፡ በብልጽግና ደሞዝ የሚከፈላቸው ፣ ኮንዶሚኒየሞች የተሰጣቸው፣ በተረኛው የኦህዴድ መንስት ፖሊሲ ተጠቃሚ የሆኑ ይደግፏቸዋል፡፡ የተወሰኑም ደግሞ ከፍርሃት የተነሳ፣ እነ አብይ ከሌሉ ምን ሊኮን ነው በሚል ስጋት፣  ተስፋቸውን እነ አብይ ላይ  አሁንም ማድረጉ የቀጠም አሉ፡፡ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ ቢመጣም፡፡ በሃሰተኛ አጭበርባሪ ነብያት ነን ባዮች፣  የተወናበዱ፣ አብይ አህመድን “ጌታ የሰጠን ነው” ብሎ ተታለው የሚያምኑ፣ በመጽሃፍ ቅዱስና በክርስትና እምነት ላይ ላዩን እንጂ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸው፣ የወንጌላዊ ቤተ ክርስቲያን የተወሰኑ አማኞችም አሉ፣ ተታለው አሁን   ብልግጽግና የሚደገፉ፡፡ ነገር ግን  ብዙዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአብይ አህመድና በብልጽግና  DISGUSTED መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ሕወሃት አስር እጥፍ ትሻል ነበር እስከማለትም እየደረሱ ነው፡፡  አራት በሉ፡፡

በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች ተመሳሳይ ነገር ነው ያለው፡፡ አፋር ብትሄዱ በብልጽናዎች ላይ ቂም አላቸው፡፡ ወላይታ ብትሄዱ ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ጉራጌዎችም በይፋ ከወጡ የኦሮሞ ኃይሎች  እንዳይጨፈልቋችው ፈርተው እንጂ ደስተኛ አይደሉም፡፡ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ሰላምና መረጋጋት የለም፡፡ በቅርቡ ኦነጎች ጋምቤላ ከተማን እስከመቆጣጠር ደርሰው እንደነበረም የሚታወስ ነው፡፡  አምስት በሉ፡፡

ምን አለፋችሁ የአብይ አህመድ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ከዳር እስከ ዳር ፣ አንደኛ እጅግ በጣም የተጠላ አገዛዝ ሆኗል፡፡ሁለተኛ አንድ መንግስት መስራት ያለበት ስራ እየሰራ አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ደካማ፣ የበሰበሰ፣ በዉሸት ላይ የተመሰረተ፣ ዘረኛና አገር አውዳሚ ቡድን መሆኑ ነው የተረጋገጠው፡፡

ለዚህ ነው፣  “እነ አብይ ከሄዱ አገር ትፈርሳለች” የሚለውን የተደማሪ ተለጣፊዎች፣ እየነ ዶር ብርሃኑ ነጋን አይነት  አባባል ትትን፣  አገር እያፈረሱት ያሉት እነ አብይ አህመድ፣ ኦህዴዶች ስለሆኑ፣  አገር ከነርሱ እጅ እንዴት እናውጣት ወደሚለው አቋም መሸጋገር ያለብን፡፡

አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ፣ ብልጽግናዎች በርግጥ ሰሞኑን እየደጋገሙ የሚለፍፉት እውነት ሆኖ፣ የኢትዮጵዖያን አንድነት አስጠብቀው፣ ሰላምና መረጋጋት አስፍነው፣ በወለጋ ጊምቢ ያየነውን አይነት  ሰቆቃ እንደማይቀጥል የሚያሳዩ መሰረታዊ ለውጦችን አድርገው በቁርጠኝነት ቢነሱ ደስ ነው የሚለኝ፡፡

የኔ ፍላጎት አገር እንድትድን፣ ዜጎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ የሚፈሰው የንጹህ  ደም መፈሰሱ እንዲቆም እንጂ፣ “ማን ገዛ ?  ማን ስልጣን ያዘ ?”  የሚለው አይደለም፡፡ ብልጽግናዎች ያሉት የሚያደርጉ ከሆነ በአስር ጣቴ ፈርሜ ድጋፍ እሰጣለሁ፡፡ ግን ያንን ማድረግ አልቻሉም፣ አይችሉም፡፡ ክንፉ የተቆረጠ አሞራ መብረር እንደማይችለው፣ ብልጽግናዎችም ክንፍ የሌላቸው አሞራዎች ሆነዋል፡፡

ስለዚህ እነ አብይ አህመድ ገለል ብለው፣ ጊዚያዊ  ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት አገርን እንዲያስተዳደር መደረግ አለበት፡፡ አስፈላጊ ከሆነም የብልጽግና  መንግስት የሽግግሩ  አካል ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡

Filed in: Amharic