ታዴዎስ ታንቱ እና አቤ ጉበኛ!
ጌጥዬ ያለው
ዛሬ ሰኔ 25 ቀን ሞገደኛው ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ የተወለደበት ቀን ነው። አቤ፣ ሐቀኛ፣ ደፋር፣ ብዕሩ እሳት የሚተፋ የዚያ ዘመን ብርቅዬ ክስተት ነበር። በዘመኑ የደረሰበትን ብቻ ሳይሆን ገና ያልደረሰበትን ስርዓት እንደሚመጣ አስቀድሞ ተንብዮ ይተቻል። ብሩህነቱ ወደ ፊት የሚመጣውን ስርዓት ከእነ ድክመቶቹ አበጥሮ እስከ ማወቅ ነበር። “አልወለድም” የሚያስረዳን ይህንን ነው። ይህ መፅሐፍ ንጉሳዊ ስርዓቱን በሰላ ብዕር ይተቻል። ከዚያ ቀጥሎ ይመጣል ያለውን ወታደራዊ ስርዓት ደግሞ እጅግ በመረረ መልኩ ይተቻል። ደርግ ሊመጣ እንደሚችል ከ10 + ዓመታት ቀድሞ አቤ ተንብዮ ነበር። ድክመቶቹንም አስቀድሞ በማየት ተችቷል። በእኔ እምነት አቤ ነገሩን አስቀድሞ ማወቅ የቻለው የ1953ቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በአግባቡ ስለተረዳ ነው። ምክንያቱም የወቅቱን ፖለቲካ ላወቀ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወታደሮች እንቅስቃሴ እየጠነከረ መምጣቱን ማወቅ ይቻላል።
አቤ ጉበኛ በዚህ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጉዳዮች የወቅቱን ፖለቲካ በመተንበይ የተሳካለት ነበር። ለዚህም ነው ነብዩ ደራሲ የሚባለው።
አቤ ዛሬ በሕይዎት የለም። መንፈሱ ግን በሐቀኛው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ውስጥ አለ። ሐቀኝነታቸው፣ ደፋርነታቸው፣ ሞገደኝነታቸው፣ ቀጥተኛነታቸው እና ጽናታቸው በእጅጉ ይመሳሰልብኛል። ጋሽ ታዴዎስ በአንድ ወቅት ለረጅም ጊዜ በወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና አድራሻቸው ሳይታወቅ ታፍነው ከቆዩ በኋላ ወደ ማያውቁት ቦታ በሌሊት ይወሰዳሉ። ይህ ቦታ በኋላ አዋሽ ሰባት መሆኑ ተረጋግጧል። በሌሊት ብቻቸውን ኦሮሞዎች ሲወስዷቸው የተሰማቸው ጊዜው ካለፈ በኋላ ተፈተው ነገሩኝ። “ሊረሽኑኝ ነው የሚል ሃሳብ ነበረኝ። ከረሸኑኝ አይቀር ሕዝብ በተሰበሰበበት ቢረሽኑኝ ጥሩ ነው የሚል ሃሳብ ነበረኝ”
ሐቀኛው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ከአቋማቸው ዝንፍ የሚሉ አይደሉም። በፍፁም ልበ ሙሉነት ነው የሚጓዙት። በቀን አንድ ዳቦ ብቻ እየተሰጣቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እንዳይጠይቋቸው ተከልክለው፣ ለወጉ እንኳን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእርሃብ ጭምር እየተቀጡ ከሦስት ወር በላይ ታግተው ቆይተው ሲፈቱ እውነትን መናገራቸውና መፃፋቸው ባሰበት እንጂ ፈርተው ዝም አላሉም። ቤታቸውን በሌሊት የወታደሮች ቡድን በመክበብ አግቶ ሲሰውራቸው ከሐቅ ማማ ላይ አልወረዱም። ይህ ባህሪያቸው አቤ ጉበኛ “እንደገና ብወለድ፤ እንደገና ብትገድሉኝ። ሺህ ጊዜ የገደላችሁኝ መሆኑን ባስታውስ ይህ መቀጣጫ ሆኖኝ ዝም ልላችሁ አልችልም” በማለት ፅፎት ራሱም ከኖረው መርሆው ጋር ያመሳስላቸዋል። ታዴዎስ እንደ አቤ ጉበኛ ሞትን የናቁ ጀግና ናቸው። ሞትን የናቀ ማንንም አይፈራም። ምቾትን የናቀ አድር ባይነት አይነካካውም። ለዚህም ይመስላል ታላቁ እስክንድር ነጋ “የምንፀየፈው ምቾትን ነው” የሚለው።
አቤ ጉበኛ በማስታወቂያ ሚንስቴር ጋዜጠኛ ሆኖ ተቀጠረ። በአዲስ ዘመን ጋዜጣም ሥራውን ቀጠለ። ሆኖም ጋዜጣው እውነት ማይፃፍበት እየሆነ አስቸገረው። ትቶት ወጣ። ከዚያም በጤና ሚንስቴር ውስጥ የሕዝብ ግኝኙነት አባል ሆኖ ተቀጠረ። እዚህም ውስጥ ስርዓቱን ከማገልገል ውጭ ሙያዊነት ጠፋ። ይህንም ትቶ ወጣ። ከዚህ በኋላ ጥቃቅን የንግድ ሥራዎችን እየሠራ ትዳሩን በመምራት የሙሉ ጊዜ ደራሲነቱን ተያያዘው። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሙሉ ጊዜ ደራሲም ሆነ። በዚህ መሃል ብዙ ተንገላቷል። አድር ባይ ቢሆን ኖሮ ግን በድሎት ተንበሻብሾ መኖር ይችል ነበር። በወቅቱ በነበረው የሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ውጥረት አሜሪካኖችን ደግፎ ቢፅፍ ጥቅም በእጁ ነበር። በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥትም በተደጋጋሚ ለሥልጣን ታጭቶ ነበር። ሆኖም ስብዕናው ለዚህ ምቹ አልነበረም።
የጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ታሪክም ከዚህ ብዙ የሚርቅ አይደለም። በወያኔ ጊዜም ሆነ በኦሕዴድ-ብልፅግና በእየእስር ቤቱ እየተንከራተቱ ያሉት በእምቢ ባይነታቸው ነው።