>

ባልደራስ ቀድሞ የታገለለት ጥያቄ በተባበሩት መንግስታት ምላሽ አግኝቷል— ትግሉ ይቀጥላል....!!!

ባልደራስ ቀድሞ የታገለለት ጥያቄ በተባበሩት መንግስታት ምላሽ አግኝቷል— ትግሉ ይቀጥላል….!!!

 

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ አኦነግ/ሸኔ እና በኦሮሞ ብልፅግና ውስጥ ያሉ አጋሮቹ የፈፀሙትን ጭፍጨፋ የተባበሩት መንግስታት ሊያጣራ መሆኑ ሰሞኑን ተዘግቧል።

የመርማሪዎቹን መምጣት አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት ገለፃ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች 338 ነው ብለዋል።

በአኦነግ/ሽኔ ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት ከመሆናቸው ሌላ፣ ቁጥራቸው በሺህዎች ውስጥ እንደሆነ የተለያዩ አካላት መግለፃቸው ይታወሳል።

ጥቃቱን ተከትሎ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ተቋም ባሻገር፣ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በኦሮሚያ ያለውን ጭፍጨፋ የተባበሩት መንግስታት እንዲመረምር ከሁሉም አስቀድሞ የጠየቀው ባልደራስ መሆኑ ይታወሳል። የድርጅቱ እመራር አባላት ወደ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ተመላልሰው በአካል ጥያቄውን በተደጋጋሚ አቅርበዋል። ሌሎች አካላት ከአደረጉት ጥረት ጋር ተደማምሮ ጥያቄው አሁን ምላሽ አግኝቷል።

በኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ የሚመረምረው ቡድን፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ተፈጽመዋል የተባሉ ጥሰቶችንም ይመረምራል።

እየተከሰተ ያለው ዘር- ጥቃት በአገሪቱ “ሊከሰቱ ለሚችሉ ተጨማሪ ጭፍጨፋዎች ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ” ነው ብሏል መርማሪ ቡድኑ።

Filed in: Amharic