ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ቤተሰቦች
ያለበት አሳውቁን እያሉ በዋይታ እየተማጸኑ ነው – ሰሚ የለም…!!!
እናድን ኢትዮጵያን
ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ እስካሁን ያለበት አለመታወቁ እንዳሳሰባቸው የገጣሚው ቤተሰቦች ገለፁ።
ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ከሚገኘው ጊዮርጊስ ምግብ ቤት ” ትፈለጋለህ?!” ተብሎ እንደተወሰደ እህቱ ሰላም በቀለ ወያ ተናግራለች።
ማክሰኞ ዕለት ሰሌዳ በሌላቸው ተሸከርካሪዎች ውስጥ በነበሩና ሲቪል በለበሱ የፀጥታ አካላት ታፍኖ መወሰዱ እንደነገሯት ያስረዳችው ሰላም፤”በፌዴራል እና በየአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ እንዲሁም በየካ ክ/ከተማ ውስጥ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ብንጠይቅም አድራሻው ሊገኝ አልቻለም“ ስትልም በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፈችው የቪዲዮ መልዕክት ተናግራለች።
እህቱ አክላም “ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ወደ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሄጃ ባለ ፖሊስ ጣቢያ በዕለት መዝገብ አስመዝግበናል” ብላለች።
እናት እና አባቱ በድንጋጤ መታመማቸውን የገለፀችው ሰላም፤ እናቱ ጽጌ ገ/እግዚአብሔርም “ልጄ የት ነው ያለው?” ሲሉ አገር እና ሕዝብን መጠየቃቸውን ተናግራለች።
በመጨረሻም የወንድሟን ድምፅ ከሰማች ሦስት ቀናት እንዳለፉትና ያለበት አለመታወቁ መላው ቤተሰቡን ለከፍተኛ ጭንቀት እና ድንጋጤ መዳረጉን በመግለፅ፤ ጥፋተኛም ከሆነ በህግ አግባብ እንዲጠየቅና እንዲቀጣ ጠይቃለች።