ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ተበየነ…!!!
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
*…. ዛሬ ሰኔ 27/2014 ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፍረድ ቤት ቀርቧ #በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች የፌደራል ከፍተኞው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ የ100 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ብይኑን በአብላጫ ድምጽ ያስተላለፈው በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ነው። ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የሚያቀርበውን የክስ መቃወሚያ ለመስማትም ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 11፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል።
የጋዜጠኛ ተመስገንን የወንጀል ክስ በመመልከት ላይ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስትና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለዛሬ ሰኞ ሰኔ 27፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ተከሳሽ በጠበቃው አማካኝነት ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ነበር። የተመስገን ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ የዋስትና ጥያቄውን ያቀረቡት ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 22 በዋለው ችሎት ነበር።
ጠበቃ ሄኖክ በወቅቱ ባቀረቡት ማመልከቻ፤ ደንበኛቸው የተከሰሱባቸው ሶስት የወንጀል አይነቶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ በመሆናቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ያቀረባቸው ሶስት ክሶች፤ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ ገልጿል”፣ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል”፣ “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ወንጀሎችን ፈጽሟል” የሚል ነው።