>

የባልደራስ መግለጫ~~ሰለ ሰኔ 27ቱ ጭፍጨፋ እና ሌሎች!!

የባልደራስ መግለጫ~~ሰለ ሰኔ 27ቱ ጭፍጨፋ እና ሌሎች!!

 

ጉዳዩ—

1– በወለጋ ሰኔ 27 2014 በአማሮች ላይ ሰለተፈፀመው አዲስ ጭፍጨፋ

2—ዳግም ስላገረሸው አፈና አና ማዋከብ

3—የባልደራስን ፕሬዚዳንት በሚመለከት

 

የጎሰኝነት ነቀርሳን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተክሎ የሄደውን የህወሓት ራዕይ ወራሽ በሆነው የኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ መንግስት፣ ያለፉት አራት ዓመታት የንፁሃን አማሮች ደም ያለማቋረጥ በወለጋ፣ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣በምእራብ ሸዋ፣ በአርሲ፣በሐረር ያለ ማንም ከልካይ እየፈሰሰ ይገኛል። በዚህም መሰረት፣ ሰኔ 27 2014 ዓ.ም በወለጋ በአማራዎች ላይ አዲስ ዙር ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።

በትረ-ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የመንግስትነትን ኃላፊነት መወጣት ያልቻለው ይህ መንግስት፣ በማህበረሰቡ ላይ እየፈጠረ ካለው ኢኮኖሚያዊ፣ ህልውናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ቀውሶች ባሻገር፣ በፋኖ፣ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላት ፣ በጋዜጠኞችና ማህበራዊ አንቂዎች፣ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ማዋከብ ከጀመረ ውሎ አድራል፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ለስራ ጉዳይ ወደ ባህር ዳር በሄዱበት ታፍነው ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በእስር ከቆዩ በኃላ፣ በሰላሳ ሺ ብር ዋስ እንዲፈቱ መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ዳሩ ግን፣ በተሰጠው ዋሰትነና መሰረት ከእስር ሲፈቱ፣ ፌድራል ፖሊስ ማረሚያ ቤት በር ላይ አፍነው ወደ አዲስ አበባ ወስደው ለዳግም እስር ዳርገዋቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የፓርቲያችን አባል የሆኑት አቶ ኢሳያስ ጥጉ ታፍነው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም፣ የፓርቲያችን አባል ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው በባህር ዳር  ታፍነው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ሌላኛው የድርጅታችን አባል ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው፣ በፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ በሚገኘው የታዲዮስ ታንቱ መዝገብ በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸዋል። አባላችን የሆነው ድምፃዊ አሌክስ ሸገር ትላንት ታታፍኖ ለእስር ተዳርጓል። ሌሎች አባሎቻችን ደግሞ፣ ቀደም ብለው ታስረው እስካሁን ድረስ በዋስ ሊወጡ አልቻሉም።

በአጠቃላይ፣ በፓርቲያችን አባላት ላይ እስርና አፈናው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የፓርቲያችን አባላት የካራማራን የድል በዓል ሊያከብሩ ወጥተው ለእስር ከተዳረጉበት ጊዜ ጀምሮ ለዋስ የሚሆን ከሶስት መቶ ሺ ብር በላይ ተከፍሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላት እና በአዲስ አበባ ወጣቶች እስር ምክንያት ከመቶ በላይ  የታሳሪዎች የእጅ ስልኮች እና  የባልደራስ ካሜራ  እና ቪድዮ ካሜራ ተመላሽ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

በዚህም መሰረት:-

1—ትላንት ሰኔ 27 2014 በወለጋ በአማሮች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በጥብቅ እናወግዛለን። እንዲሁም፣ ሰኔ 11 ቀን 2014ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ፣ በቶሌ ቀበሌ፣ ከሁለት ሺ በላይ ንፁሀን አማራዎች በግፍ ህይወታቸው ያጡበትን አሰቃቂ የዘር ማጥፋት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች (በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣በደብረ ብርሀን እና በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች) ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን እስርና ማዋከብ እናወግዛለን፡፡

2—መንግስት በፋኖ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት ላይ የሚያደርገውን ወከባ እና ጫና  በፅኑ እንቃወማለን፡፡ እንዲሁም፣ መንግስት በፓርቲያችን ላይ እያሳደረው ያለውን የኢኮኖሚ ጫና አበክረን እናወግዛለን፣

3—ህግን አክበሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እያካሄ ባለዉ ፓርቲያችን ላይ የብልጽግና መንግስት እያደረሰ ያለዉን ህገወጥ የአፈና እንዲያቆም የሀገርም የውጭም አካላት ደምፃቸውን እንዲያሰሙ እንጠይቃለን፣

4—በመጨረሻም፣ አቶ እስክንድር ነጋ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዘዳንት፣ ቤተሰብን ለመጠየቅ  እና ለድርጅታዊ ስራ በሰሜን አሜሪካ  ለሁለት ወራት ቆይተዋል፡፡  በውጭ ሀገር ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ፓርቲው ቢያምንም፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ አቶ እስክንድር ነጋን አስቸኳይ ለሆኑ ድርጅታዊ ስራዎች ስለሚፈልጋቸው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ወሳኔ አስተላልፏል፡፡

ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም.

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

Filed in: Amharic