>

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬም አልተፈታም! (ታሪኩ ደሳለኝ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬም አልተፈታም!

ታሪኩ ደሳለኝ


ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን እንዲያከበር እንጠይቃለን

በእንቢተኛው ፖሊስ ላይ አቤቱታ ቀረበ

ትናንት፦

ትናንት ሰኔ 27/2014 ዓ.ም 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈታ መወሰኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ለዋስትን የተጠየቀውን ብር አስይዘን የመፈቻ ወረቀቱን ይዘን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (ሦስተኛ) ብንመጣም ፍቺውን የሚያስፈፅም አካል ባለመኖሩ ፖሊስ ጋዜጠኛ ተመስገንን ሳይፈታው አሳድሮታል::

ዛሬ፦

ዛሬም ሰኔ 28/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (ሦስተኛ) ብንገኝም እስካሁኑ ሰዓት ድረስ አራት የሚሆኑ መርማሪ ፖሊሶች፥ የመርማሪ ፖሊስ ሀላፊዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩን ማግኘት አልቻልንም:: በመሆኑም፣ አሁንም ፍርድ ቤቱ የወሰነው የፍቺ ጉዳይ መቋጫ አላገኘም።

የሚመለከታችሁ አካላት ሕግ እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲከበር ጫና እንድትፈጥሩ እንጠይቃለን!

በእንቢተኛው ፖሊስ ላይ አቤቱታ ቀረበ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመተላለፍ ጋዜጠኛ ተመስገንን አልፈታም እንዳለ ነው። በጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ በኩል “የተከበረው ፍርድ ቤት በ27/10/2014 ዓ.ም የሰጠውን ትዕዛዝ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲደርሰው እና የክፍሉ ኃላፊ ኮሚሽነር ጸጋዬ ባልቻ ተገደው ቀርበው እንደመፍቻው ትዕዛዝ መሰረት ያልፈጸመበትን ምክንያት እንዲያስረዱ እንዲታዘዝልኝ አመለክታለሁ” የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤት መግባቱን አረጋግጠናል። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለነገ 29/10/2014 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጥቷል።

Filed in: Amharic