>

የተድበሰበሰውና እውነትን የደፈጠጠው የዶክተር ዳንኤል ሪፖርት...!!! (ዘላለም ግዛው)

የተድበሰበሰውና እውነትን የደፈጠጠው የዶክተር ዳንኤል ሪፖርት…!!!

ዘላለም ግዛው


* … ዶ/ር ዳንኤል  በአማራ ህዝብ ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል  ለማድበስበስ እየሰራ ላለው አራጅ ቡድን እያደረክ ያለው ትብብር እጅግ የከፋ ወንጀል ነው።  አለም እየጠየቀ ያለውን ጥያቄ ለማዳፈን ይሄ ሁሉ መውተርተር ከማዋረድ ከፍ አያደርግህም።  እባክህ ተመከር  ከወንጀለኞች ጋር መተባበር ተው !

*… በሪፖርቱ ይህ ተቋም ከባለጊዜዎች ጋር በመተባበርና ለፖሊቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ያበረከተው አስተዋጽኦ አብሮ ለምን አልተካተተም ?ይህ ድፍጥጥ ሪፖርትም የቀረበውና ግፎችን ለመዘርዘር ያልተፈለገበት ዓላማው የሆነ አካላትን ተጠያቂ ስለሚያደርግ አይደል የፈራችሁት?

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአይነቱና በይዘቱ የመጀመሪያ ነው ያለውን ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አደርጓል፡፡

ሪፖርቱ የሚሸፍነው ጊዜ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም አንስቶ እስከ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ድረስ ሲሆን፤ ይሄንኑ ሪፖርት ለጋዜጠኞች ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ናቸው።

እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤  በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተፈጸሙ የተለያዩ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተከስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአመቱ ባከናወናቸው ተግባራት የበርካታ ሰዎች ሞት፣ የአካልና ስነ ልቦና ጉዳት፣ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ ንብረት ውድመትና ጥሰቶች መፈጸማቸውን ማረጋገጡን አመልክተዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሕይወት የመኖር መብት፣የአካል ደኅንነት መብት፣ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ከጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶች ጥሰቶች  ተፈጽመዋል ብለዋል።

በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የተካሄደው ጦርነት በአካባቢዎቹ በመሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ፣ በጤና እና በትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም በግል ንብረቶች ላይ ያደረሰው ውድመት፣ እንዲሁም ጦርነቱ ባስከተለው  መፈናቀል ሳብያ በተከሰተው የእርዳታ  ፈላጊዎች መጨመር፣  በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ምርት መስተጓገሉ  በተለይም ምግብ የማግኘት መብት፣ በጤናና ትምህርት አገልግሎት የማግኘት መብቶችን ጨምሮ በሁሉም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ከልሎች የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በድርቅ በመጠቃታቸው ምክንያት በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ድጋፍ የመስጠት አቅም ላይ ጫና ያሳደረ መሆኑንን ገልጸዋል።

“በአጠቃላይ በሀገሪቷ የተከሰተው ጦርነት፣ ግጭት እና የተስፋፉ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች መንስዔያቸው የፖለቲካ አለመግባባት/አለመረጋጋት ውጤት ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው” ብለዋል  ዶ/ር ዳንኤል።

“የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ኮሚሽኑ ለአንድ ዓመት ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ሥራ አማካኝነት በምርመራ፣በክትትል፣ በጥናት እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ትምህርት ተግባራት የሰነዳቸውን ጉዳዮች የሚዳስስ እንደመሆኑ የአካባቢያዊ፣ የጊዜና የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ሽፋን ውስንነቶች ቢኖሩበትም፣

እጅግ አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ የሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያመላክት ነው። ስለሆነም በተለይም ለፌዴራል እና ለክልል መንግሥታዊ ባለድርሻ አካላት በየዘርፋቸው የሚመለከታቸውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ለማድረግ እና ለማሻሻል ተገቢውን ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ ነው” ብለዋል ዶክተር ዳንኤል በመግለጫቸው።

Filed in: Amharic