>

ወልቃይት ጸገዴ የወደፊቷን ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆን ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ወልቃይት ጸገዴ የወደፊቷን ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆን ?

የወያኔ ሁለተኛው የጦርነት አላማ ነጻ ሀገር ለመመስረት ወይንስ ሌላ ተልእኮ ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

አዲስ አበባ ( ኢትዮጵያ)


ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፣ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ፣ የ13 ወር ጸጋ ያላት ውቢት ኢትዮጵያ፣በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ኢትዮጵያ፣የብዙ ነገዶች መኖሪያ የሆነችው፣ እንዲሁም የብዙ ባህል ባለቤት ኢትዮጵያ፣ የሶስት ዋና ዋና ሃይማኖቶች ተከታዮች ለብዙ ሺህ አመታት በሰላም እና አንድነት ተከባብረው የኖሩባት ኢትዮጵያ  በእኔ ህይወት ውስጥ በጥልቅ ታትማለች ወይም ተተክላለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ብረት ቀጥቅጦ ለሶስት አስርተ አመታት ገዝቶ የነበረው የወያኔ ዘረኛ የአገዛዝ ቡድን የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የኢትዮጵያን የረዥም ግዜ ታሪክ በመክዳት ኢትዮጵያ የ100 አመት ታሪክ ያላት ሀገር ናት በማለት በአደባባይ በመደስኮራቸው የተነሳ ፣በርካታ አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው እና ኢትዮጵያ ሀገራቸውን በሙያቸው ማገልገል የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ጎምቱ ምሁራን  ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ወያኔ ከልክሏቸው ስለነበር ልቤ በሀዘን ደምቶ ነበር፡፡ ( በነገራችን ላይ  የአባ ሰንጋ ክትባት ግኝት ባለቤት ፕሮፌሰር ጥላሁን እና በአለም ባንክ ለበርካታ አመታት ያገለገሉት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራን፣ እውቁ ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ ወያኔ ክልከላ አድርጎባቸው ነበር፡፡ )

የወያኔ ቡድን አሁን ድረስ የማእከላዊ መንግስት ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ቢቆይ ኖሮ የጎሳ ፖለቲካን ክፉኛ የሚተቹ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ መከልከሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአለም ባንክ ከ 30 አመታት በላይ ያገለገሉት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የጎሳ ፖለቲካን አደገኛ አካሄድ በመተቸታቸው ምክንያት ወያኔ ሀገር ቤት እንዳይገቡ ከልክሏቸው ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ሁላችንም እንደምናስታውሰው በ2008 ዓ.ም. የወያኔ ቡድን ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑ ተሽቀንጥሮ ወድቋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከአራት አመት በኋላ ዛሬም ኢትዮጵያ ከመከራ አዙሪት መውጣት አልሆነላትም፡፡ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተስፋ የተጣለበት የዶክተር አብይ ካቢኔ ተስፋ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ የሚገዙት ዶክተር አብይ ኢትዮጵን ዴሞክራቲክ ሀገር እንድትሆን የጀመሩት ጉዞ የተወሳሰቡ አሜኬላዎች ገጥመውታል፡፡

በርካታ ስመጥር ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት ጠበብት አበክረው እንዳስገነዘቡት ኢትዮጵያ ከጎሳ ፖለቲካ፣አክራሪነት፣ ከተገንጣይ አስተሳሰብ፣ከጠባብ ክልላዊ ስሜት መውጣት እስካልቻልን ድረስ በኢኮኖሚ ራሳችን መቻል ቀርቶ ህልውናችንም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ መዘጋት አለባቸው፡፡ ሀገሪቱ ጦርነት መሸከም አትችልም፡፡

ታሪክ እንደሚያስተምረን ያ ትውልድ በ1966ቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩትን ወጣቶች ማለቴ ነው ‹‹ መሬት ላራሹ ›› በሚል መፈክር ስር ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሲሉ ህይወታቸውን ቤዛ አድረገው አልፈዋል፣ ታስረዋል፣ የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው እንደ ጨው ዘር በአለም ላይ ተበትነዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላም ቢሆን የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት አልሆነም፡፡ መሬት የገበሬው የግል ሀብቱ ባለመሆኑ የተነሳ በግጥሾ፣ ውሃና ሌሎች ይገባኛል ምክንያት የተነሳ በተለያዩ ግዜያት በገበሬዎች መሃከል ግጭቶች መከሰታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤት የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን የያዘው ቡድን ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ለድንበር ዘለል ኩባንያዎች እና ለሀገር ውስጥ ባለወረቶች ሰፋፊ መሬቶችን እየሸጠ ይገኛ፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ እርሻው የተመሰረተው በትንሽ መሬት ላይ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ታሪካዊ ጠላታችን ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጣ በጦር ሃይል ከተቆጣጠረች በኋላ ያለምንም ከልካይ ሰፋፊ የእርሻመሬቶችን አስፋፍታለች፡፡ ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል እንዲሉ ሱዳንን ሃይ የሚላት በመታጣቱ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እንደ ኦነግ ሸኔ እና የወያኔ ዘረኛ ቡድን የመሰሉ አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ ቡድኖች ሁነኛ ወሳኞች እየሆኑ መምጣታቸው መጪውን ግዜ አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ዶክተር ማሪና ኦታዋይ (Dr. Ottaway opined ) እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 2019 ‹‹“Ethiopia: can the future hold?” በተሰኘ ጥናታዊ ወረቀታቸው ላይ እንደጠቀሱት ከሆነ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስር የሰደደው የጎሳ ፖለቲካ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት እድገት ከመግታቱ ባሻግር ሀገሪቱን የበለጠ ለድህነት የሚዳርግ ነው፡፡ የወደፊቷ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ መልካም ሊሆን የሚቻለው በሀገሪቱ ላይ ሰላም መስፈን ከተቻለ ነው፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ዶክተር በፍቃዱ በቀለ፣ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌን የመሳሰሉ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ጠበብት፣ እንዲሁም በአለም ባንክ ድርጅት የኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ዳይሬክተሮች በተለያዩ ግዜያት ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ እንደጠቀሱት የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት የሚበጅ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጎሳ ተኮር ግጭቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ኋላ አስቀርቶታል፡፡ 

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ማንበር ቢሆንላት ህዝቧን በምግብ አቅርቦት ችላ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የምትችል ሀገር መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህ ባሻግር በአመት ሁለቴ ስንዴ ማመርት የሚያስችል የአየር ጸባይ እና መሬት፣ የውሃ ሀብትም ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአለም ባክ ድርጅት በዚሁ በመስኖ እርሻና ዘመናዊ እርሻ አኳያ ኢትዮጵያን ለመርዳት መልካም አስተሳሰብ ያላቸው የባንኩ የስራ ሃላፊዎች እንዳሉ ጠቅሰው  ፕሮፌሰር አክሎግ በአንድ የጥናት ወረቀታቸው ላይ ያሰፈሩትን ቁምነገር ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ግዜ ውስጥ የአለም ገንዘብ ድርጅት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት መዋለ ንዋይ ሀብታቸው ለወደመባቸው፣የአፋር፣የአማራ እና ትግራይ ክልሎች መልሶ ግንባታ ይውል ዘነድ 300 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ለአምራች ሀይሉ አቅም ግንባታ ይረዳ ዘንድ( ተቋማትና የሰብዓዊ ካፒታልን ለማሰደግ የሚደረግ እርዳታ ለእውቀት ሽግግር የሚረዳ ነው፡፡)  ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ መመደቡ እንደ መልካም ዜና የሚታይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአለም ባንክ የእርዳታ ገንዘብ ለታቀደለት አላማ እንዲውል የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ እውን መሆን ግድ ነው፡፡ እንደ ወያኔ፣ኦነግ ሸኔ የመሳሰሉ አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ባሉበት ሁኔታ የአለም ባንክ ውጥን ገቢራዊ መሆን አይቻለውም፡፡ ማእከላዊ መንግስቱን የተቆጣጠረው የፖለቲካ ሀይል ደግሞ ኢትዮጵያን ከጎሳ ፖለቲካ ለመገላገል መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ካልሆነለት የአለም ባንክ የገንዘብ ገንዘብ እርዳታ ኢትዮጵያን ከድህነት ነጻ ሊያወጣት አይቻለውም፡፡

ዋነኛው ነጥብና ሊሰመርበት ያለው ቁምነገር የአለም ባንክ አላማና ግብ እንዲሰካ  ሰላምና መረጋጋት መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ 

እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የመሰሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ጉምቱ ኢትዮጵያውያን በመጪዎቹ ሳምንታት አስጨናቂውን የኢትዮጵያ ሀገራችንን ነብስ ውጭ፣ነብስ ግቢ ጉዳይ በተመለከተ ካላቸው የህይወት ተሞክሮና ጥልቅ ጥናት በመነሳት ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ገለጻ ለማድረግ ማሳባቸውን ከጽሁፎቻቸው ላይ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ በእውነቱ ለመናገር የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው በወረበላዎችና መዳረሻቸውን በማያውቁ ግሰለቦች፣አልጠግብ ባዮች የፖለቲካ ምህዳሩን እስከተቆጣጠሩት ድረስ እድገታችን የኋልዮሽ የመሆኑ ጉዳይ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ፊተኞች እንዳልነበርን ዛሬ ከኋለኞቹ የመጀመሪያውን እረድፍ ይዘናል፡፡ ኢትዮጵያን ለመፍረስ የቋመጡትን ንፍጥ አንጎሎች ወጊዱ ማለት ተገቢ ነው፡፡ እልፍ አእላፍ ዜጎች ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው  ያለፉት እነኛ እልፍ አእላፋት ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው ያለፉት ለላንቲካ እንዳልነበር የአሁኑ ትውልድ ማወቅ አለበት፡፡

በነገራችን ላይ ዘረኛውና ጎሰኛው የወያኔ ገዳይ ቡድን ዳግም ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት ላይ ስለመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመዘገቡ ጉዳይ እጅጉን አሳሳቢ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ዋነኛ አላማቸው የወልቃይት ጸገዴ ተቆጣጥሮ ወደ ሱዳን የሚወስዳቸውን ስትራቴጂክ ኮሪደር መክፈት ይሆናል፡፡ ይህን እኩይ አላማቸውን እውን ለማድረግ የወያኔ ቡድን መሪዎች የኤርትራን ወታደራዊ ሀይል፣ የአፋርና አማራ ሚሊሻዎችን፣ የፋኖ ሀይልን በሃይል ለማሸነፍ መወሰናቸውን ከተለያዩ የዜና አውታሮች እየተሰማ ይገኛል፡፡ 

የወያኔ ሀይል ይሄን ለመፈጸም ብቻውን አይደለም፡፡ አንባቢው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ ይቻለዋል፡፡ የትኛው የውጭ ሀይል ነው ለወያኔ መሳሪያ የሚያቀርበው ? ማነው ስትራቴጂክ ወዳጃቸው ? አላማቸው ምንድን ነው ?

ወያኔ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣልና ኤርትራን ለመውጋት ያስችለው ዘንድ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ግብጽና ሱዳን፣ እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረትና ከተባበረችው አሜሪካ ድጋፍ እንደሚደረግለት የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሚያጠነጥኑ የተለያዩ የጥናት ወረቀቶች ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡

ከዚህ ባሻግር የዚህ ትራጄዲክ ኮንሰርት ደጋፊዎችና አዘጋጆች ዋነኛ አላማቸው ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የሀገሪቱን አንድነት ማስከበር አልቻለም ብለው ያምናሉ፡፡

there is no doubt in my assessment that the concert of bad actors wishes to “Balkanize” Ethiopia. They are also convinced that Ethiopia’s center will not hold the country together. 

ስለሆነም በሀገር ውስጥና በመላው አለም እንደ ጨው ዘር የተበተናችሁ  ውድ ኢትዮጵያውያን ሆይ ኢትዮጵያ የገጠማትን ከባድ ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት እና የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር ሲባል ስትራቴጂክ ያልሆኑትን ልዩነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ አንድነታቸውን ማጥበቅ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ አንድነታቸው ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ከወያኔ ሁለተኛው ጦርነት በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ወይም ሞቲቭ ( the motive ) ?

ለዚህ አጭሩ መልሱ ጂኦፖለቲካል አላማ ያለው ነው የሚለው ነው፡፡ (Simply put; it is geopolitical ) ትግራይ አለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራት የወያኔ ቡድን ቅዠትና ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ ለዚህ አጥፊ አቅዳቸው እውን መሆን ደግሞ ወልቃይት ጸገዴ፣ጸለምትን መቆጣጠር ታላቅ ህልማቸውና አላማቸው ነው፡፡ ወያኔ ወልቃይት ጸገዴና ጸለምትን በሃይል መቆጣጠር ከቻለ የታላቋን ትግራይ ትግሪኝ መንግስት እመሰርታለሁ ብሎ ካቀደ አመታት ነጎዱ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን የወያኔን እኩይ እቅድ ለማክሸፍ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መሰባሰብ አለባቸው፡፡ በጎሳ ተቧድኖ ኢትዮጵያን ለማዳን እጅጉን የሚያዳግት ይመስለኛል፡፡

ወያኔ ለውጭ ሀይሎች ቃል የገባው ነገር አለ፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያ አንድነት ከተናደ ብሔራዊ ጥቅሞቻችሁን አስጠብቃለሁ የሚለው ነው፡፡ ለአብነት ያህል ግብጽ ወያኔን የምትደግፈው በተዳከመች እና በፈረሰች ኢትዮጵያ መቃብር ላይ ቆማ የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር ከላት የብዙ ሺህ አመታት ህልምና አላማ የተነሳ ነው፡፡ ይህም ካልተሳካላት ታላቁ የአባይ ግድብ የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን በተመለከተ ወሳኝ ( አስተዳዳሪ ) ለመሆን ነው፡፡ ግብጽ ለትግራይ ህዝብ የሚደማ ልብ የላትም፡፡ ይህቺ ሀገር ዋነኛ ፍላጎቷ የውሃ ጥማቷን ለዝንተ አለም ማርካት ነው፡፡ ሱዳንም እንዲሁ የራሷን ስትራቴጂክ ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል ከግብጽ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከሚያደሙት ሀገራት አንዷና ዋነኛዋ ናት፡፡ ሱዳን ኢትዮጵያ ተዳክማለች ባለችበት ግዜ ( እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2020) ላይ የኢትዮጵያን ድንበር 50 ኪሎሜትር ወደ ውስጥ በወታደራዊ ሀይል ተጠቅማ ጥሳ በመግባት ለም መሬታችንን የተቆጣጠረች ሀገር ናት፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንገት ያስደፋና ሀዘን ላይ የጣለ ነው፡፡ ዛሬም ባይሆን ነገ ተነገወዲያ በታሪክ እና ህሊና የሚያስጠይቅ ነው፡፡

የተባበረችው አላማና እቅድ ወይም ወያኔን የምትደግፈው የራሷን ስትራቴጂክ እና ብሔራዊ የጸጥታ ጉዳይ ለማስከበር ስትል እንጂ እርሷም ብትሆን በትግራይ ህዝብ ፍቅር ወድቃ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን ስለመደገፋቸው በይፋ አይናገሩም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የተባበረችው አሜሪካና የምእራቡ አለም በይፋ ባይናገሩትም የወያኔ ሀይልን ተጠቅመው የኤርትራን አገዛዝ ከስልጣኑ አሸቀንጥረው ለመጣል እየሰሩ ስለመሆኑ በርካታ የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡

አንዳንድ የኢትዮጵያ አስጨናቂ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያዊ ምሁራን በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ የተባበረችው አሜሪካና ምእራባውያን የወያኔ ቡድንን መደገፍ የአፍሪካውን ቀንድና የቀይ ባህርን ለመቆጣጠር ያስችለናል ባይ ናቸው፡፡ የተባበረችው አሜሪካና የአውሮፓው ህብረት ወያኔ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ መናገር ወይም መገሰጽ ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ ወያኔ የአፍሪካው ቀንድ ሰላም አደፍራሽ ወይም ስጋት ስለመሆኑ በአደባባይ መናገር አይፈልጉም፡፡ ከእነርሱ ጀርባ ያሉት ሌሎች ሀይሎች ደግሞ ቻይና፣ ሩሲያና ቱርክ ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡

ወያኔ ከውልደቱ ጀምሮ አሁን ድረስ የወልቃይት መሬትን ተቆጣጥሮ በሱዳንና ኤርትራ ድንበር በኩል አለም አቀፍ ድንበር በማስመር አዲሲቷን የትግራይ ሀገር እውን እንድትሆን ያልበጠሰው ቅጠል፣ ያልቆፈረው መሬት እንዳልነበር የአሁኑ ትውልድ በአንክሮ በህሊናው እንዲመዝነው ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡

ለኢትዮጵያ ይህን ስትራቴጂክ ስፍራ ማጣቷ ህልውናዋን የሚፈታተን ነው፡፡ ምክንያቱም የወልቃይት ጉዳይ የአማራ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ስትራቴጂክ ስፍራ ( ወልቃይት ጸገዴ ማለቴ ነው፡፡) የወደፊቷ ኢትዮጵያ አንደኛውና ዋነኛው አካል ሆኖ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ወልቃይት ከታሪካዊ ባለቤቱ የጥንቱ ቤጌምድር ዛሬ በአማራ ክልል ጎንደር መሬት ላይ ተቆርሶ ከተወሰደ ግብጽና ሱዳን የሚፈልጉት ምኞት ተሳካ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ግብጽና ሱዳን የችግሩ አካል ናቸው ብዬ የማምነው፡፡

በእኔ የግል አስተያየት ዛሬ የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን የተቆጣጠረው አገዛዝ በወልቃይት ላይ ቀይ መስመር በማስመር የኢትዮጵያ አካል ስለመሆኗ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብና ለአፍሪካው ህብረት በግልጽ በአደባባይ፣ በታወቁ ሚዲያዎች ቀርቦ ማሳወቅ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ወይም ታሪካዊና መንግስታዊ ግዴታው ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

አብዝሃው ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ልሂቃንና የማህበራዊ ልሂቃን አጭር የማስታወስ ችሎታ አላቸው፡፡ በቅርብ የተፈጸሙ ድርጊቶችን ይረሳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያ የጋራችን፣ ትግራይ የግል ናት የሚለውን የሸፍጥ ፖለቲካውን መናገሩን ረስተነዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ወያኔ ኢትዮጵያን ለ 27 አመታት በገዛበት ግዜ የነጻ አውጭነት ስያሜውን አለመቀየሩን፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ብረት ቀጥቅጦ  መግዛቱን ረስተነዋል፡፡ እርግጥ ነው በወያኔ የ27 አመታት የግፍ አገዛዝ ዘመን ህጋዊ እንዲሆን ተባባሪዎቹ የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በመላው ኢትዮጵያ የበቀሉ የጎሳ ኤሊቶች ተባባሪዎች ነበሩ፡፡ የወያኔ ደጋፊዎች ከመላው ሀገሪቱ የተገኙ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞችና ሌሎች ጥቅም አነፍናፊዎች ነበሩ፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች የወያኔ ደጋፊዎች አልነበሩም ዛሬም አይደሉም፡፡ የወያኔን ታሪካዊ ስህተት እና አላማ የማይደግፉ ትላንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፡፡ ነገም ይኖራሉ፡፡ 

ቀሪዎቻችን ኢትዮጵያውያን ምን አደረግን ( የወያኔ ደጋፊ ያልነበርነው ማለቴ ነው፡፡) ምንም ቁምነገር ሰርተን አልነበረም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ባይቻልም፡፡ አብዛኛዎቻችን ተመልካቾች፣ ጎመን በጤና፣ ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ የምንል ባዮች ነበርን፡፡ በሟቹ ጠቅላይ ሚንሰትር መለሰ ዜናዊ ዘመነ መንግስት በርካታ የወያኔ ኤሊቶች ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሲገነቡ፣ውድ ሆቴሎች፣ የሚያማምሩ ቪላ ቤቶች፣ እና ሌሎች የሚዳሰሱ ውድ እቀዎችን ሲዘርፉ አብዛኛው ህዝብ ተመልካች ነበር፡፡ እኔ እንደማውቀው በሀገር ቤት ወያኔን ፊትለፊት ከመጋፈጥ አኳያ ፣ ወንጀሉን በማጋለጥ የነት ፕሬስ አርበኞች፣ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( ነብሳቸውን ይማር) የማይዘነጉ ናቸው፡፡ 

በነገራችን ላይ የወያኔ የጥፋት ቡድን ፊትአውራሪዎችና ጋሻጃግሬዎቻቸው እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ግብጽና ሱዳን፣ የተባበረችው አሜሪካና የአውሮፓው ህብረት የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት፣ የተዳከመች ኢትዮጵያን ለማየት ሲሉ እቅድ 2፣3 ወይም 4 አውጥተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ በርካታ አስርተ አመታት መቆጠራቸውን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስበን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ ስለ ወልቃይት አሳዛኝ ሁኔታ በተመለከተ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ደጋግመው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያን ህልውና ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡

በተባበረችው አሜሪካና በአውሮፓው ህብረት አኳያ የወልቃይት መሬት በምእራብ ትግራይ የጂኦግራፊ ክልል  እንደሚገኝ በየግዜው መወትወታቸው የሚያሳየን ነገር ቢኖር ያሳለፉት ውሳኔ ፖለቲካዊ አምድምታ እንዳለው ነው፡፡ ውሳኔው በእውነትና ታሪክ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ወያኔ ‹‹ አማራው የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ›› ነው የሚለው ትርክት ፍጹም ስህተት ነው፡፡ የአማራና የትግራይ ህዘብ ለብዙ ሺህ አመታት በፍቅርና አንድነት ተከባብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ይህ ከባድ ስህተት ነው፡፡ ወያኔ ሀሰትን ደጋግሞ በማስተጋባት እውነት ለማስመሰል የሚጥር እኩይ ድርጅት ነው፡፡ ሀሰትን ደጋግሞ በመስበክ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ለእኩይና ለጥፋት አላማው ማሰለፉ ግን እሙን ነው፡፡ በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ ወልቃይት በምእራብ የትግራይ ጂኦግራፊያዊ ክልል ይገኛል ማለታቸው የሚያመላክተን ነገር ቢኖር በአካባቢው ስልታዊ ፍላጎት እንደላቸው ነው፡፡

The EU and the USA accepted “Western Tigray” as fact because it is in their strategic interest.

የውጭ ሀይሎች አንተን ፍላጎት የሚደግፉ ከሆነ ህጋዊነትን ትጎናጸፋለህ፡፡ ከህዝብ የተዘረፈን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ረብጣ ዶላር በማፍሰስ ተከራካሪዎችን ቀጥሮ ሀሰትን እውነት በማስመሰል በሚደረግ ደባ እውነትን ለግዜው ማሸነፍ ይቻል ይሆናል፡፡ እውነት ስትደበቅ ሀሰት በአጭር ግዜ ውስጥ አለምን ትዞራለች፡፡ ወያኔ በገንዘብ የገዛቸው ሎቢስት ለግዜውም ቢሆን የወያኔን አሳዛኝ የሀሰት ድራማ በማራገብ አለምን አሳስተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት ሀሰቱን ማጋለጥ ካልቻልን ለኢትዮጵያ ህልውና አደገኛ ነው፡፡ ወያኔ፣ ሌላው አሳዛኙ ቅጥፈት  የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበረችው አሜሪካ፣ ግብጽና ሱዳን የአማራ ሀይሎች፣ የኤርትራ ሃይሎች በምእራብ ትግራይ ጦርነት ከፍተዋል የሚሉት ትርክት ነው፡፡ በእነርሱ የሀሰት ልብወለድ መላምት ከሆነ በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ወንጀል የተፈጸመበት የአማራ ህብረተሰብ እንደ አጥቂ ሀይል መቆጠሩ አሳዛኝ ሁነት ነው፡፡ ያለምንም ጥርጥር ይህ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ነው፡፡ አንድ እግሩን ኢትዮጵያ፣ ሌላውን የምኞት አዲስ ሀገሩ ላይ ያነበረው ወያኔ ግን ወራሪ መሆኑ ለእነርሱ አይዋጥላቸውም፡፡ 

እስቲ አሁን ደግሞ እውነታውን ላስምርበት፡-

 1. ታሪካዊውና ተፈጥሯዊው የትግራይ ወሰን የተከዜ ወንዝ ነው
 2. ሱዳንን በምእራብ ፣ ኤርትራን በሰሜን፣ የትግራይ ክልልን በምስራቅ፣ አቅጣጫዎች የሚያዋስነው የወልቃይት ጸገዴ፣ ጸለምት ሰፊ መሬት በቀድሞው አጠራር ቤጌምድር፣ስሜን ዛሬ የሰሜን ጎንደር አካል ነው፡፡
 3. በዚህ መሬት ላይ የሚነገረው ዋነኛው የሰዎች መግባቢያ ቋንቋ፣ ትግርኛ ሳይሆን  የአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ የአካባው ነዋሪ ለዘመናት በጋብቻ፣  ወደ አካባቢው የቀን ስራ ለመስራት በሚመጡ ሰዎች  እና  ከሱዳን ጋር ባለው የንግድ ግንኙነት ምክንያቶች የተነሳ የትግርኛና አረብኛ ቋንቋዎች መናገር የተለመደ ነው፡፡
 4. አብዛኞቹ የወልቃይት፣ጸገዴ፣ ጸለምት ነባር ነዋሪዎች ከትግርኛ ማንነት ይልቅ የአማራ ማንነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ እኛ አማራ ነን ይላሉ፡፡ ለአብነት ያህል በዘመነ ወያኔ የአማራ ማንነታቸውን የተነጠቁት የወልቃይት ነዋሪዎች ‹‹ የወልቃይት ጸገዴ አማራ አስመላሽ ኮሚቴ ›› የሚል ስያሜ ያለው ማህበር አቋቁመው ሲታገሉ እንደነበር በዚህም ምክንያት የኮሚቴው አባላትና በርካታ አንጋፋዎች፣ ለሞት፣እስርና ስደት መዳረጋቸውን የቅርብ ግዜ አሳዛኝ ትዝታ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የወልቃይት፣ጸገዴ፣ ጸለምት ነዋሪዎች ጥያቄ የማንነትና የሰብዓዊነት ጥያቄ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
 5. የቀድሞው የትግራይ ተቅላይ ግዛት አገረ ገዢ የነበሩት ክቡር ራስ መንገሻ ስዩም፣ በአደባባይ እና በታወቀ መገናኛ ብዙሃን አበክረው እንዳሳወቁት በታሪክ ውስጥ ወልቃይት የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ( ዛሬ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ) አካል ሆና አታውቅም፡፡ ይህንኑ መራር እውነት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን እንደሚቀበሉት እሙን ነው፡፡ ለአብነት ያህል  የወያኔ ቡድን ፋይናንስ ሃላፊ የነበሩት ሀገር ወዳዱ አቶ ገብረመድህን አርአያና፣ የወያኔ ቡድን መስራች አባላት የነበሩት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ይህኑን እውነት ከሚቀበሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
 6. የወያኔ ቡድን በኢኮኖሚ ጥቅም ምክንያት የተነሳ ይህን አካባቢ ( የወልቃይት ምድር ማለቴ ነው) የተቆጣጠረው ገና የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ሳይጨብጥ የነጻ አውጭ ግንባር በነበረበት ግዜ መሆኑን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም መሬቱ እጅግ ለም ከሆኑት የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በአካባቢው በቆሎ፣እጣን፣ ጥጥ እና ሌሎች አዝርእቶችን ማብቀል ይቻላል፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ደግሞ በተለይም በሴቲቱ ሁመራ የቢሮ ሰራተኞችና ወታደራዊ ማእረግ ያላቸው ኦፊሰሮች በትራክትር ያሳርሱ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡ የዛሬውን አያድርገውና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የቀን ሰራተኞች ከኤርትራ፣ትግራይና ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ ሴቲቱ ሁመራ በማቅናት ኑሮአቸውን ያሻሽሉ ነበር፡፡ የደርግ ወታደራዊ መንግስት በበከሉ በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ድሬዳዋና ከመሳሰሉት ከተሞች ውስጥ የነበሩትን ስራፈት ወጣቶች በመሰብሰብ በሁመራ የጥጥ ለቀማ እርሻ ላይ አሰማርቷቸው ነበር፡፡
 7. እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 ላይ ወያኔ የምኒሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ዘው ብሎ ለመግባት በለስ እንደቀናው ግዜ ሳይወስድ ወዲያውኑ ያደረገው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን መሰረቱን ጎሳና ቋንቋ ባደረገ ከከፊል ራስ ገዝ ክልሎች መከፋፈል ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ባንቱስታናይዜሽን አኳያ ከፋሎ እንድትዳከም ያደረገ እኩይና መሰሪ ድርጅት ከመሆኑ በሻግር የወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ጸለምት፣ ሁመራና ራያ አካባቢዎችን ክልል አንድ ወይም ትግራይ ክልል ብሎ በሰየመው ክልል ውስጥ እንዲካተቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ምክንያት የትግራይ ክልል ድንበር የሚዘረጋው እስከ ተከዜ ወንዝ ብቻ መሆን ሲገባው እስከ ሱዳን ድንበር ድረስ እንዲዘረጋ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ይህ ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ታቅዶ የተሰራው ሸፍጥ ጥልቅ የሰብዓዊ መብት ገፈፋና አለም አቀፍ ባህላዊ ህግን የጣሰም ነበር፡፡ ይህን ከባድ ወንጀል የፈጸመው ወያኔ የመንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም፣ የኢትዮጵያን ህዝብ መብትም ገፏል፡፡
 8. በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት በአካባቢው ( በተለይም ሁመራ መሬት ላይ) ተጀምሮ የነበረው ዘመናዊ የእርሻ ስራ ወታደራዊው የደርግ መንግስት የባለ ሀብቶችን መሬት በመውረሱ ምክንያት መክኖ መቅረቱ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በቀድሞው ዘመን የነጻ አውጭ ድርጅቶች የነበሩት የወያኔ እና ሻቢያ ሀይሎች፣ ሌሎችም እንደ ኢህአሰ የመሰሉ የደርግ ተቃዋሚዎች የነበሩ ሀይሎች እነደልባቸው ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ነበር፡፡ በተለይም ወያኔ ከሱዳን የመሳሪያ፣መድሃኒትና ሌሎች እርዳታዎችን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ኮሪደር ለመከፍት አስችሎታል፡፡ ቅርብ ግዜው የሰሜኑ ጦርነት ከመከፈቱ እረጅም አመታቶች በፊት ከፌዴራል መንግስቱ እውቅና ውጭ የትግራይ ክልል እንደ አንድ እውቅና እንደሌላት ሀገር ከሱዳንና ግብጽ ሀገራት ጋር ግንኙነት መስርታ ነበር፡፡
 9. እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1984 ወልቃይት፣ ጸገዴና ጸለምትን ተቆጣጥረው የነበሩት ወያኔዎች ሰፊ የህዝብ አሰፋፈር ለውጥ አድርገዋል፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይበል የአካበቢውን ገድለዋል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሱዳንና ሌሎች አካባቢዎች እንዲሸሹ አስገድደዋል፡፡ ነባር የአካበቢውን ነዋሪዎች ከአፈናቀሉና ከገደሉ በኋላ ደግሞ የቀድሞ ተወጊዎቻቸውን ከእነ መሳሪያ ትጥቃቸው፣ እንዲሁም ሌሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ገበሬዎችን አስፍረዋል፡፡ የአማራ ልጃገረዶችና ሴቶች የትግራይ ተወላጅ ወንዶችን እንዲያገቡ ተገደዋል፡፡ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአማርኛ ቋንቋ የማስተማሪያ ቋንቋ እንዳይሆን በማገድ የትግርኛ ቋንቋ የትምህርት ቋንቋ እንዲሆን ወስነው ገቢራዊ አድርገውት ነበር፡፡ ይህ እኩይ ድርጊታቸው የሚያደሳየን  ነገር ቢኖር በአካባቢው የጎሳ ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ምእራብ ትግራይ የሚለው ድንበር የተሰመረው ዛሬ ሳይሆን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 ጀምሮ መሆኑን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡
 10.  ወያኔ በቅርብ ግዜ ውስጥ በሚያቀነቅነው ናሬቲቭ መሰረት አካባቢው ( ወልቃይት ) የትግራይ ሉአላዊ ግዛት ነው፡፡ ይህን የማይቀበል ሰው ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ዘይገረም ሻሸመኔ የሚል አባባል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የታሪክ ፌዝ ሆነና ወያኔ ሀይል አግኝቶ የፈለገውን ለማድረግ መቻሉ አሳዛኝ ነው፡፡ የጎንደር ዩንቨርሰቲ ምሁራን በህይወት ያሉ አንዳንድ የአካባቢውን ተወላጆች የአይን ምስክርነት ዋቢ አድርገው በቅርቡ ባደረጉት ጥልቅ ጥናት የትግራይን ማንነት ያልተቀበሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የወልቃት ተወላጅ አማርኛ ተናጋሪ አማሮች  በወያኔ ጨካኝ ቡድን ተገድለው የተቀበሩባቸውን ሰፋፊ የጅምላ መቃብሮችን ማግኘታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን የተሰማ መራርና አሳዛኝ ሁነት ነው፡፡ ሌሎች ገና ያልተገኙ የመቃብር ስፍራዎች እንዳሉም ተነግሯል፡፡ ሞት አፍ አውጥቶ ቢናገር ኖሮ የወያኔንን ጭካኔና አረመኔ ተግባር እንዲሁም የሰውን ጭካኔ ጥግ የበለጠ መረዳት ይቻል ነበር፡፡ 
 11.  ወያኔ ታርጌት ( ትኩረት) አድርጎ ከገደላቸው ሰዎች መሃከል እውቀት ያላቸው ሰዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ አስተማሪዎች፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የወያኔ ተቃዋሚዎች፣ ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ወያኔ የነገ ሀገር ተረካቢ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ወጣቶችን ለማጥፋት አልሞ የገደላቸው ቤት ይቁጠራቸው፡፡
 12.  የወያኔ ቡድን የሴት እህቶቻችንን ባለቤቶች ( የትዳር ጓደኞች) ከገደለ በኋላ እነኚሁ ሴቶች በትግራይ ተወላጆች ተደፍረው እንዲወልዱ በማስገደድ የሚወለድ ህጻን የትግራይ ማንነት እንዲኖረው እና ትግርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲኖረው  ማድረጉን በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የአቶ ገብረመድህን አርአያና የእውቁም ምሁር አቻምየለህ ታምሩን ዘመን አይሽሬ ጽሁፎችን ማንበብ ይቻለዋል፡፡
 13.  ወያኔ የታወቁ ባህላዊ የእምነት ተቋማትን ( ማለትም ቤተክርስቲያኖችንና መስጊዶችን ) በመጠቀም የሀሰት ትርክት ለህዝቡ እንዲሰበክባቸው ያስደርግ ነበር፡፡ በእነኚህ ተቋማት በተለይም በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቅዳሴ ስርዓት በትግርኛ ቋንቋ ይከናወን ነበር፡፡
 14.  ወያኔ የወልቃይት ጸገዴ ነባር ነዋሪ የበአል አከባበር ስርዓት፣ የእምነት ስርዓት፣የቀብር ስርዓት፣ ክንዋኔዎችን  በአማርኛ ቋንቋ እንዳያከብር ክልከላ አድርጎበት ነበር፡፡ ወያኔ ይህን የባህል ማጥፋት ውሳኔ ( cultural genocide ) የሚቃወሙ ወይም የማይቃበሉ  ማናቸውንም ሰዎች ገድሏል፡፡ አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አስገድዷል፡፡ ለአብነት ያህል በግዜው  አባ ገብረመድህን 

የተባሉ ቄስ የወያኔን ትእዛዝ አልቀበልም በማለታቸው አሰቃቂ አካላዊ ጉዳት እንደረሰባቸው ከአንዳንድ መረጃዎች ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

 1.  የወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ጸለምት መሬት በፖለቲካዊ ውሳኔ እና ምህንድስና በትግራይ ምእራባዊ የጂኦግራፊ ክልል ውስጥ እንዲካተት ከተደረገ 40 አመታት አልፎታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በዚህ  በሀይል የምእራብ ትግራይ አካል እንዲሆን በተደረገው  የወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ጸለምት መሬት ላይ ነባር የአማራ ተወላጆች በወያኔ ብረት አንጋቾች የጎሳ ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በውጤቱም እጅግ በረቀቀና ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ፣በድብቅና ሳይሰማ  በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢውን የአማራ ተወላጆች ከተወለዱበት መንደር በማፈናቀል፣ በመግደል ሰፊ የህዝብ አሰፋፈፈር ለውጥ አድርጓል፡፡ በአጭሩ ነባር የአማራ ተወላጆችን ከአካበቢው በማጥፋት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግርኛ ቋንቋ ተነጋሪ ኢትዮጵያውያን  እንዲሰፍሩ አድርጓል፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡
 2.  ለእኔ የተባበረችው አሜሪካና የአውሮፓው ህብረት አካባቢው በምእራብ ትግራይ ክልል ይገኛል ማለታቸው አግባብ አይመስለኝም፡፡ ህጋዊም አይደለም፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ‹‹ ጀርባዬን እከክልኝና እኔም ያንተን ጀርባ አክልሃለሁ ›› የሚለው የምእራባውየን ዲፕሎማሲ በአፍሪካ ውድቀት ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሌላው የተባበረችው አሜሪካና የአውሮፓው ህብረት በአንድ ሉአላዊት ሀገር ላይ ጣልቃ የመግባት ሌላው ዘዴ ነው፡፡ አሁን ወደ ጽሁፌ ማጠቃለያ ልውሰዳችሁ፡፡

ማጠቃለያ

 1. የወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ጠለምት ነባር ነዋሪ ፍትህ ሊጎናጸፍ ይገባል፡፡ በዚች ምድር ላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰላም፣ በነጻነት መኖር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በወልቃይት ምድር ለመኖር አማራ፣ ትግሬ፣ ወይም ኦሮሞ፣ ጉራጌ ወዘተ ወዘተ ማንነት መሰረት መሆን የለበትም፡፡ እኔ ጠባብ ስልቻ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ በወልቃይትም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ምድር ለመኖር ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህን ደፍሮ ለመጻፍ ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ለማናቸውም ( ግራም ነፈሰ ቀኝ ) ወያኔ በድጋሚ ወረራ በመፈጸም ወልቃይትን የመያዝ እኩይ አላማና ሴራ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ 
 2.  የኢትዮጵያን ማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑን የጨበጠው የብልጽግና ፓርቲ የወልቃይት ምድር ለነባሩ ነዋሪ ለመመለስ ዳተኝነት በማሳየቱ  ወይም የሚያሳየው ቸልተኝነት፣ እንዲሁም ለወልቃይት ነዋሪዎች ባጀት አለመመደቡ፣ እኔን በእጅጉ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱም ለረጅም ግዜ ቅሬታ የፈጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ይቅርታ የሚደረግለት አይደለም፡፡ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ወልቃይት ስትራቴጂክና እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ከታመነበት ( በርግጥ ሁለቱም ትክክል ናቸው፡፡ ) የኢትዮጵያ መንግስት የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ ወሳኝ ፖሊሲ መቅረጽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ትክክለኛው መንገድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ ስላለው አቋም ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ገና አላሳወቀም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ማእከላዊ መንግስቱ በወልቃይት ጉዳይ አኳያ በታክ ፊት ቆሟል፡፡
 3. ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ መንግስት ወልቃይትን በተመለከተ ከወያኔ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ የአውሮፓ ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ አኳያ የሚያራምደው ግልጽ ያልሆነ ፖሊሲ ነባር የወልቃይት ነዋሪና ኢትዮጵያን ከባድ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል፡፡
 4. አሁን ወደ ርእሳችን እንመለስ፡፡ ወያኔ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ የለውም፡፡ ለዘለቄታ ሰላምም የቆመ አይደለም፡፡ አሁን ከቅርብ ወራት ወዲህ በአፋር ያካሄደው ጦርነት፣ በወልቃይት ምድር በየግዜው የሚቀሰቅሰው ግጭት፣ ከኤርትራ ጋር ያለው የጦርነት ፍጥጫ ታስቦበት ታቅዶ የሚደረግ ነው፡፡ የወያኔ ዋነኛ አላማ ወልቃይትን ዳግም ለመቆጣጠር ያለመ ነው፡፡ ወልቃይት፣ ጠገደተ፣ ጠለምት የወያኔ ዋነኛ የመገንጠል አጀንዳ ነው፡፡ ይህ ለአፍሪካው ቀንድ ሰላም የማይበጅ የወያኔ እብሪት ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው የወያኔ የጦርነት አቅድ የትግራይ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችንን ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ ስቃይ ውስጥ የሚዶል ነው፡፡ ስለሆነም የትግራይ ወንድሞቻችን ካንሰር የሆነውን የወያኔ ቡድን መጣል አለባቸው፡፡
 5. አለመታደል ሆኖ የተባበረችው አሜሪካ እና የአውሮፓው ህብረት ለአፍሪካወ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እውን መሆን የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት እንድነቷ እንዲጠበቅ ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት ወያኔን ለመደገፍ ሲሉ ዳግም ስህተት ውስጥ እንዳይወድቁ ለማሳሳብ ነው፡፡ የታፈረችና የተከበረች፣ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ለአፍሪካው ቀንድ ሰላምና መረጋጋት መጠበቅ እጅጉን አስፈላጊ በመሆኗ ሃያላኑ ዳግም በኢትዮጵያ ላይ የጫኑትን ፖሊሲያቸውን እንዲመረምሩ ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ወያኔን መደገፍ ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝ እንጂ ዘለቄታ የለውም፡፡
 6. አሁን ከገጠመን ውድቀት ለመነሳት ጦርነት መፍትሔ አያመጣም፡፡ የሚያዋጣው ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መንገድ መነጋገገር፣መደማመጥ ነው፡፡ ይህም ንግግር ወይም ውይይት በአፍሪካ ህብረት ተመልካችነት መሆኑ ደግሞ ውጤት ያስገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡
 7. ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር መጠነ ሰፊ ናቸው፡፡ ለፌዴራል መንግስቱ የማቀርበው ምክረ ሃሳብ ቢኖር ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት ከክልል ፕሬዜዴንቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር፣ ከሲቪል ማህባራት ተወካዮች፣ አካዳሚሻን፣ ከእምነት አባቶች፣ ከወጣትና ሴቶች ተወካዮች፣ ጋር በመሆን ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ በተመለከተ መነጋገር አለበት፡፡ ይህ ግዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡
 8. ጎሰኝነት፣ አክራ ብሔርተኝነት፣ጉበኝነትና ንቅዘት ኢትዮጵያን ከባድ አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህን አደጋ መክላት የአዲሱ ትውልድ ሃላፊነት ነው፡፡ እነኚህ ሁላችንንም ያጠፉናል፡፡ የጠቀስኳቸው ችግሮች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያውያን ጥቅም እንዳይውል የሚያደርግ ነው፡፡
 9. በመጨረሻም በረዥም ግዜ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚሰጥ ህገመንግስት ማንበር ይገባቸዋል፡፡ ሃብት ለማፍራት፣ ለመደሰት፣ በማናቸውም የሀገሪቱ ክፍሎች ማናቸውም የሀገሪቱ ዜጎች መኖር እንዲችሉ፣ድህነትን ለመክላት፣ ሀብትን ለማሳደግ፣ መጪው ትውልድ ያለ ስጋት እንዲኖር  ህገመንግስቱ መሻሻሉ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
 10. ሰላም እና መረጋጋት ከሰፈነ ፣ ዲሞክራቲክ መንግስት እውን ከሆነ፣ ይህን ማሳካት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የተቋማት ማሻሻያ ማድረግ፣ ቀና አመለካከት እና የመንግስትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ለማናቸውም የኢትዮጵያን ክፉዋን አያሳየን፡፡

ለእውነት ብለን ብንጎዳም፣ ለውሸት መቆም የለብንም

ጥቅም አይገዛኝም በህይወት እስካለሁ፣

ውሸት አይገዛኝም ለእውነት እሞታለሁ፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም.

 

 

 

 

 

 

References  

(Wolkait: Tears of Blood by Dagnachew Teshome)  

Report by Photojournalist Jemal Countess, ENA, April 17, 2022 

Ann Garrison. April 27, 2022: https://blackagendareport.com/notes-wartorn-ethiopia-part-iii-crimestigrayan-peoples-liberation-front 

Ethiopian Human Rights Commission (EHRC)/Office of the United Nations High Commissioner for Human Rights (OHCHR) Joint Investigation into Alleged Violations of International Human Rights፡ https://www.un.org/sexualviolenceinconflict/wp-content/uploads/2022/02/report/report-of-theethiopian-human-rights-commission-ehrc/OHCHR-EHRC-Tigray-Report.pdf 

The Potential of Democratization in Ethiopia: The Wolkait Question as a Litmus Sonja John First Published August 2, 2021, Research Article https://doi.org/10.1177/00219096211007657 

Wolkait Mass grave: Researchers say TPLF had killed and …https://borkena.com 2022/04/05 › Wolkait mass-grave… 

Apr 5, 2022 — Twelve mass grave are uncovered in Wolkait, Ethiopia but researchers. … tortured and killed to be thrown into the water. 

Amnesty International and Human Rights Watch Report On …https://zehabesha.com › amnesty international-and-hum… 

Apr 27, 2022 — … Amhara victims have been discovered in several mass graves in Wolkait. Yet, the joint report does not reference the team’s report, … 

Discussion with Dr Aklog Birara, Wolkait Tegede and Kimant …https://www.youtube.com › watch 

A BIASED WESTERN NARRATIVE OF ATROCITIES IN ETHIOPIAhttps://nilejournal.net  

May 22, 2022 — By Dr. Aklog Birara, a retired World Bank Senior Advisor … Countess’s reporting on the 

Wolkait massacre of indigenous Amhara that I had reported

Filed in: Amharic