>

ኸረ በስንቱ እንፈር??? በስንቱስ እንጨቃጨቅ??? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኸረ በስንቱ እንፈር??? በስንቱስ እንጨቃጨቅ???

ያሬድ ሀይለማርያም


በጦርነት በተጎዳች፣ የግጭት ቀጠና በሆነች እና በግፈኞች እጅ የንጽሐን ደም በየቀኑ በከንቱ በሚፈስበት አገር ሰብአዊነት የተሰማቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቴዲ አፍሮን ልደት አስታከው በየአመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ትላንት እሁድ ደም ሊለግሱ  ፕሮግራም ይዘው ወደ ቀይ መስቀል ሲሄዱ ‘ከላይ በመጣ ትዕዛዝ’ በሚል ደም ልገሳ ፕሮግራሙ መከልከሉን አዘጋጆቹ በቅሬታ መልክ ገልጸዋል። አሁን ይሄ ምን የሚሉት ፓለቲካ ነው? ደም ለግሱ፤ እጥረት አለ እየተባለ በሚለመንበት አገር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዛ ጥሪ ቀና ምላሽ ሲሰጡ ደንቃራ መሆን ማንን ለመጉዳት ነው? እንዲህ ያለውንስ ትዕዛዝ የሚሰጡት ምን አይነት ሹሞች ናቸው? ኸረ እባካችሁ እየተስተዋለ። አገር በብሽሽቅ አይመራም። ኸረ በስንቱ እንፈር? በስንቱስ እንጨቃጨቅ? ደም መለገስ የፖለቲካ አጀንዳ መሆን የለበትም። 10 አመት ያስቆጠረን የደም ልገሳ ፕሮግራም ማስተጓጎል ቴዲ አፍሮን ሌላ “እያመመው መጣ” ቁ.3 ዘፈን እንዲያወጣ ያደርገው ይሆናል እንጂ ግፍን ከመቃወም አያስቆመውም።

Filed in: Amharic