>

ሕወሓት ሌባም ሆኖ የብልጽግናን ያህል አይን አውጣ - ይሉኝታ ቢስ አልነበረም...!!! (ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)

ሕወሓት ሌባም ሆኖ የብልጽግናን ያህል አይን አውጣ – ይሉኝታ ቢስ አልነበረም…!!!

ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

ሕወሓት በአገዛዝ ዘመኑ ለከተማ ነዋሪዎች ካመጣቸው ፀጋዎች አንዱ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ገንብቶ በአነስተኛ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ሕዝብ በእጣ ማድረስ ነው ። በአርግጥም ብዙዎች በፍጹም በስማቸው ቤት ሊኖራቸው የማይችሉ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ሆነዋል ። ይሁንና በሂደት እንደታሰበው ሳይሆን የትግራይ ተወላጆች የአዲስ አበባ ኗሪ ሳይሆኑ ከትግራይ እየመጡ በዘዴ ስማቸው እጣ ውስጥ እንዲገባና እንዲወጣም እንደሚደረግ አዲስ አበባና ነዋሪዎቿ ታዘቢዎች ናቸው ። ይሁንና ሕወሓት አሁን ብልጽግና በሰራው ልክ ይሉኝታ ቢስ አልነበረም ። ለራሱ ሰዎች ይስጥ እንጂ በዚህ መጠን ስግብግብ እና ሀፍረተ ቢስ አልነበረም ። ሲያታልል እንኳ መልክ ነበረው ።

ከወራት በፊት ከአንድ ሰው ጋር ወደ ቦሌ አራብሳ ሄደን ኦሮምኛ ተናጋሪ ለሆኑ ” የገበሬ ልጆች ” የተሰጡትን ቤቶች ማየት ችለን ነበር ። በሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ ባለ ሦስት መኝታ እና ከ1ኛ እስከ 3ኛ ፎቅ ያሉ ነበሩ ። ይህ ወዳጄ ያኔ ነበረ ኮንዶሚኒየሞቹን ሙሉዎቹን ለራሳቸው ሰዎች አድለው እንደሚጨርሱት እርግጠኛ የሆነው ። አሁን የታየው እሱ ነው ። የ1997 ተመዝጋቢዎች ባለ ሦስት መኝታ ተሰጥቶ ስላለቀ ብዙዎች የ2005 ባለሦስት መኝታ ክፍል ተመዝጋቢዎች ” ይደርሰኛል ” የሚል ተስፋ ነበራቸው ፤ ተስፋቸውን ውሀ በላው እንጂ ።

መቸም ብልጽግና የአፍሪካ መንግሥት ( ያውም በዘር የተደራጀ ) በመሆኑ የሀገሪቷን ሀብት በምንም ይሁን በምን ” የእኔ ” ለሚላቸው ማደሉ አይገርምም ። ግን በዚህ መጠን ይሉኝታ ያጣል ብሎ ያሰበ የለም ። ቅርብ ጊዜ ለባለስልጣናቱ በ18 ወራት ቅንጡ አፓርታማዎችን ሰርቶ ማስመረቁ ይታወቃል ።

       ኧረ ተዉ ሕዝብን በዚህ መጠን አትናቁት ። ይሄ ሕዝብ እንኳን ብልጽግናን ሕወሓትን የጣለ ሕዝብ ነው ። ተዉ ቆማችሁ ከሕወሓት ውድቀት ተማሩ !!!

Filed in: Amharic