>

"መላ ሀገሪቱን ያቀጣጠለ ማዕበል እንፈጥራለን" የዩኒቨርስቲ መምህራን ማስጠንቂያ!! (ባልደራስ)

“መላ ሀገሪቱን ያቀጣጠለ ማዕበል እንፈጥራለን” የዩኒቨርስቲ መምህራን ማስጠንቂያ!!

ባልደራስ

በአርባ አምስት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን ከደሞዝ ጭማሪ፣ ከቤት ኪራይ አበል እና ከደረጃ እድገት ጋር በተያያዘ ለረጅም ወራት ቅሬታቸውን አቅርበው ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥያቄዎቻቸው ተግባራዊ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ፤ ከነሐሴ 5 ጀምሮ ተማሪዎችንም ባካተተ መልኩ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እና አድማ እንደሚያደርጉ አሳስበዋል።

“መላ ሀገሪቱን ያቀጣጠለ ሀገራዊ ማዕበል እንፈጥራለን” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ቀደም ሊደረግ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ “አሁን ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አኳያ መንግሥትን ችግር ውስጥ ይከተዋል” በሚል በመምህራን ማሕበር ሸምጋይነት ተራዝሞ ቆይቷል።

በሂደት እንደታየው ግን፣ ማህበሩ ከአገዛዙ ጋር በመወገኑ፣ ለመምህራኑ ጥያቄ ትኩረት አለመስጠቱን መምህራኑ ተናግረዋል። መምህራኑ ደምወዝ እንዲጨምርላቸው፣ የማዕረግና የደረጃ ዕድገት አሰጣጡ ፍትሐዊ እንዲሆን፣ የቤት ኪራይ አበል እንዲሰጣቸውና የሚሰጣቸው አበልም የወቅቱን የኪራይ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን ትምህርት ሚንስቴርን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ ተቋማትን ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በቢሮ ደረጃ ሲቀርብ የነበረውን ጥያቄ ወደ አደባባይ በማምጣትም የማሕበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን ሊጀምሩ መሆኑን ተናግረዋል።

Filed in: Amharic