>
1:23 am - Saturday March 25, 2023

ሰውም - ኮንደሚኒየምም፤ የሚጨፈጨፍበት - የሚዘረፍበት አገር...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ውም – ኮንደሚኒየምም፤ የሚጨፈጨፍበት – የሚዘረፍበት አገር…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

“አገሬ መምጫሽ ናፈቀኝ” አለ ጠቢቡ


የኮንደሚንየም ዝርፊያ ግርግር ከሳምንት በፊት በመቶች በማንነታቸው የተጨፈጨፉበትን ዘግናኝ ወንጀል መሸፈኛና ማዘናጊያ ርዕስ ከመሆኑ በዘለለ ምን አዲስ ነገር አለው?

ሙስና (እኔ professional ሌብነት ነው የምለው) አድጎናና ተንሰራፍቶ ቀንድ ካበቀለባቸው ጥቂት አገራት መካከል

ኢትዮጵያ አንዷ ከሆነች አመታት ተቆጠሩ። መርከብ፣ ሕንጻዎች እና ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከነነፍሳቸው ሙሉ በሙሉ ከመሰወር አንስቶ መሬት እየተወረረ በሚሊዮን የሚቸበቸብበት፣ ኮንደሚኒየሞች የብሔር ፖለቲካ ማሳለጫ የሆኑበት፣ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ከዘበኛ እስከ ሚኒስትር ከተገልጋዩ ሕዝብ ላይ የየአቅማቸውን የሚቦጭቁበት፣ ባለስልጣናት የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ሚሊዮኖች ሜዳ ላይ በፈሰሱበትና መከራዋ እጅግ በበዛ አገር ከነአጃቢዎቻቸው በአሥራ – ሚሊዬኖች በሚገመቱ V8 መኪኖች  ታጅበው የሚፈላሰሱባት፣ ሕዝብ እየተራበ ሹሞችና ታዳሚዎቻቸው በሕንጻና በፓርክ ምረቃ በድግስ የተጠመዱባት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎቿን በየሳምንቱ በግፈኞች እጅ የሚቀሉባት ጉደኛ አገር ይዘን የት ልንደርስ ይሆን?

የብልሹ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ መዋቅራዊ ቅርጽ የያዘ ሙስና ነው። ዛሬ በወ/ሮ አዳነች አስተዳደር የተፈጸመው ሰቅጣጭ የሌብነት ወንጀል ትላንት ታከለ ዑማን ከስልጣን ገሸሽ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አንዘንጋ። መሬትና ኮንደሚንየም በተዘረፈ ማግስት ነው ከሚዲያ ገሸሽ ወደሚያደርጋቸው ሌላ ሹመት እንዲዛወሩ ተደርጎ ወ/ሮ አዳነች የሌባ መዳኒት ተብለው የተሰየሙት። ሌብነቱ በወ/ሮዋ ዘመን ደሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ እና መጠኑን ጨምሮ አግጦ መጣ። ለዚህ ነው Professional ሌብነት ኢትዮጵያ ውስጥ መዋቅራዊ ቅርጽ ይዟል ያልኩት። ነገ ሌላ ከንቲባ ቢመጣም ሌብነቱ ይቀጥላል።

ከሁሉ ታዲያ የሚያስደምመኝ ዝርፊያው ሲጋለጥ ሹሞቹ ወደ አደባባይ ብቅ ብለው እና አይናቸውን በጨው አጥበው፤ እገሌን አሥሬያለሁ፣ እገሌ አታለለኝ፣ እገሌ ሌባ ነበር ለካ እያሉ እራሳቸው የሾሟቸውን ግልገል ካድሬዎች የመስዋት በግ ያደርጉና እራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ የሚጋጋጡት ነገር ነው። እኔ የሾምኩት፣ እኔ የማዘው፣ በእኔ መዋቅር ስር ያለ ሰው በሌብነት ሕዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ እሱ በጥፋቱ ቢጠየቅም በእኔ አስተዳደር  ለደረሰው ጉዳት እኔም ተጠያቂ ነኝ። ባጭሩ ታከለ ዑማም፣ አዳነች አበቤም በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።

ልክ ወለጋ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አማራዎችን ጭዳ ያደረገው በማንነት ላይ ላነጣጠረው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሽኔ በወንጀሉ ቢጠየቅም የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ እና በየደረጃው ያሉ የክልል እና የፌደራል ባለስልጣናት ለሕዝብ ጥበቃ ባለማድረግ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው መሆኑን ደጋግሜ እንዳሳሰብኩት  ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ አሳሳቢ  ችግሮች ሥርዓቱም፣ አገሪቷም፣ ሕዝባችንም የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃችንን ማሳያዎች ናቸው። ከመወነጃጀሉ ባለፈ ግን መውጫ መንገዱን በጋራ ቁጭ ብሎ መመካከር የግድ ይላል።

#በቃ

#ግፍ_በቃን

#ቀይ_አሻራ

እንዳልነው ሁሉ

#በቃ_ሌብነት

“Corruption can have a devastating impact on the availability, quality and accessibility of human rights-related goods and services. Moreover, it undermines the functioning and legitimacy of institutions and processes, the rule of law and ultimately the State itself.” UN- OHCHR:

Filed in: Amharic