>
5:13 pm - Thursday April 18, 3371

"የደርግን "አፈሣ"  በ"አፈና" ቀይሮ ያመጣው ብልጽግና የአዲስ አበቤን  ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎታል...!!! (ዘሪሁን ገሠሠ)

“የደርግን “አፈሣ”  በ”አፈና” ቀይሮ ያመጣው ብልጽግና የአዲስ አበቤን  ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎታል…!!!

ዘሪሁን ገሠሠ


“ለልዩ ኦፕሬሽን ስልጠና” በሚል ምክንያት  በምሽት ታፍነው ወደወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚላኩና  ለህገ-ወጥ እስር የሚዳረጉ ዜጎች  ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል!

ከአዲስአበባ የተለያዩ አካባቢዎች ታግተው የተሰወሩ በርካቶቹ ወጣቶች  ለልዩ ወታደራዊ ስልጠና ከጅግጅጋ አልፎ “ጎዴ” ከሚባል ማሰልጠኛ ተገደው እንዲገቡ መደረጉን   ፥ ታግቶ በጠፋ በሳምንቱ ፥ በነበረበት ህመም ምክንያት እንዲመለስ የተደረገ ወጣት ተናገረ!

ታዳጊው ከሳምንት በፊት ምሽት ላይ ከሚኖርበት አዲስአበባ ከተማ ወደጓደኛው ቤት በእግሩ ሲጓዝ ፥ ቀይ ቦኔት ያደረጉ ወታደሮች አፋፍሰው መኪና ላይ እንደጫኑት የገለፀ ሲሆን እሱን ጨምሮ ከአዲስአበባ ከየጎዳናውና እንደሱ በድንገት ምሽት ሲንቀሳቀሱ ከተያዙ ወጣቶች ጋር ተጭነው ወደ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እንዲጓዙ መደረጉን ገልፇል፡፡

በቀጣይ ቀን ከጅግጅጋ አልፎ ወደሚገኝ “ጎዴ” የተሠኘ ወታደራዊ  ማሠልጠኛ መወሰዳቸውን የገለፀው ወጣቱ ፥ ማሰልጠኛ ካምፕ ከደረሱ በኃላ ህመምተኛ መሆኑንና ያለበትን የአካል ጉዳት አሳይቶ አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ ከማሠልጠኛ እንዲወጣ  መደረጉን አስታውቋል፡፡

ጅግጅጋ በመመለስም አድራሻው ጠፍቷቸው ሲጨነቁ የነበሩት ቤተሰቦቹ ጋር በመደወል ፥ የትራንስፖርት ገንዘብ ተልኮለት ወደቤቱ መመለስ እንደቻለ ገልፇል፡፡

ይህ ወጣት እሱን ጨምሮ አብረውት ከነበሩት መካከል  ከጎዳና የታፈሱና እድሜአቸው 18 አመት የማይሞላቸው ታዳጊዎች እንደሚገኙበት የገለፀ ሲሆን ፥ ጎዴ ማሠልጠኛ ከደረሱ በኃላ  ስለተያዙበት ምክንያት ባደረገው ማጣራት ” ለልዩ ተልዕኮ አጋዚ እንደሚባለው ጦር አይነት  ወታደራዊ ስልጠና ሊሠጡን እንደሆነ ነው የተረዳሁት!” ብሏል፡፡

ባለፉት ሳምንታት በአዲስአበባ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚታፈኑ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በተየጋጋሚ የተገለፀ ሲሆን  ፤  ለአብነትም ከቀናት በፊት በደረሰኝ መረጃ መሠረት በተመሳሳይ መንገድ ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘሩትና ከምእራብ ጎጃምና አዊ ዞኖች ለስራና ለዘመድ ጥየቃ የሄዱ 17 ወጣቶች ደብዛቸው በጠፋ በ12 ቀናቸው ደብረዘይት ፖሊስ ጣቢያ ተሰባስበው መታሠራቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ከአዲስአበባ የታገቱ ወጣቶች  ያለምክንያት መታፈናቸው አንሶ ፥ ከሁለት ሳምንት እስር በኃላም ከታገቱበት ለመለቀቅ በነፍስወከፍ አስር ሺህ ብር ከፍለው መውጣት እንደሚችሉ እንዲጠብቋቸው በተመደቡት የፀጥታ አካላት በመጠየቃቸው ፥ የሚከፍሉት ገንዘብ አጥተው እስካሁን በእገታ ስር እንደሚገኙ  ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው  ገልፀውልኛል፡፡

እነዚህ በስም ተለይተው የታወቁት ታጋቾችም ፦

1ኛ. ቻሌ ገነት

2ኛ.መዝገብ አወቀ

3ኛ. ስለሽ ጌታነህ

4ኛ. መልካሙ ዋለ

5ኛ. ይበሉ ታደስ

6ኛ. ገነቱ ቻሌ

7ኛ. አዲሱ ተፈራ

8ኛ. ምስጋነው ተፉራ

9ኛ. ዘመኑ በላይነህ

10ኛ. ሞላልኝ አቡታ

11ኛ. አዲሱ ትላሁን

12ኛ. እያሱ ሙለታ

13ኛ. ድርስ

14ኛ. በልያውቃል አማረና ሌሎች ስማቸው ያልተገለፁ 3 ወጣቶች መሆናቸውንም የመረጃ ምንጮቼ ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ይህን መሠሉን አፈናና ፈቃደኝነት ሳይጠየቅ ብሎም ቤተሰብ እንኳ ሳያውቅ አስገድዶ ለልዩ ወታደራዊ ስልጠና በሚል እየወሰደበት ያለው አግባብ ስርአቱ ፍፁም ወደለየለት አንባገነንነት እየተሸጋገረ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡

Filed in: Amharic