ለሰቆቃው ማብቂያ ነገ በጣም ሩቅ ነው …!!!
ቀለብ ስዩም
*…. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያካሄደው ስብሰባ በንቃት ተከታትያለሁ፡፡ አገሪቱ በምን አይነት ሰዎች እየተገዛች እንዳለች በመረዳቴ ህሊናዬ ቆስሏል. ነፍስያዬም አዝናለች፡፡ የነበረኝ እንጥፍጣፊ ተስፋም እስከ ወዲያኛው ነጥፎአል!!!
የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለምን ይኼን ይኼን ጥያቄ አንስተው አልሞገቱም የሚል ነቀፌታ ለመሰንዘር አልሞክርም፡፡ ምክንያቱም ሁሌም ቢሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በአፈ ጉባኤው አማካኝነት ድርጅታዊ ስራዎች ተካሂዶባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያውም ከአንድ ሳምንት በፊት አባላቱ የሚያቀርቡትን ጥያቄ አስመዝግበውና ከቀረቡት ጥያቄ ውስጥም በፕሮቶኮል ሹሞቹ ተመርጠው ይሆናል፡፡ ምክር ቤት ውስጥ ጥያቄ ያላችሁ ተብሎ የሚካሄዴው የእጅ አወጣጥ ስነ ስርአት ይዝብን የማጭበርበርና የማስመሰያ ፈንታ ነው፡፡ዴሞክራሲያዊ መሰረቱ የተናጋው ገና ከጅምሩ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
ስለዚህ የምክር ቤቱ አባላት የወከላቸውንና የመረጣቸውን ሕዝብ ሳይሆን የሚያገለግሉት ያስመረጣቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ይሆናል፡፡ ምንም አይነት እውነተኛ የሕዝብ ተወካይነት ሚና የሌላቸው በመሆኑ ለመነጋገርያነት አይበቁም፡፡ ስለዚህ ብቸኛው ተወቃሽም ሆኖ ተጠያቂ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሰውየው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን አስመልክቶ፦ “በሌሎች በአደጉ አገሮች በየአመቱ ብዙ ዜጎች ይሞታሉ፤ ከእዚህ ጋር ስናነፃፅረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገደለው ዜጋ በቁጥር ትንሽ ነው….” የሚል አይነት የድፍረት፣ የግድ የለሽነትና የንቀት ንግግር አሰምተዋል፡፡ ይህን መሰሉን የእብሪት ንግግር ጤነኛ አእምሮ ካለው ከአንድ አገር መሪ መስማት በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ መጪውንም ጊዜ በከፍተኛ ስጋትና ጥር እንድንመለከት የሚጋብዘን ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ መሰሉ ጨካኝ መሪ ነገ ከሥልጣን ይወርዳል ብንባል እንኳ ለእኔ ነገ በጣም ሩቅ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ አዎ፤ ነገ በጣም ይዘገያል፡፡ እንዲህ አይነቱ መሪ አገሪቱን ሰው አልባ እንዳያደርጋት ስልጣኑን መልቀቅ ያለበት ዛሬውኑ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የኦህዴድ ብልፅግና በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ የአማራ ሕዝብ ሁሉ ከሰው የተፈጠረም አይመሰለውም፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ ኦነግም ተባለ ሸኔ የኦሮሞ ነገድ (ጎሣ) ነው፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ የኦሮሚያን ክልልም ሆነ ኢትዮጵያ እየገዛ ያለው ኃይል የኦህዴድ ብልፅግና እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ወይም ደግሞ የኦሮሞ ጎሳ ካድሬዎች ስብስብ ነው፡፡ እናም በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ15 ሚሊዮን በላይ የአማራ ተወላጅ እንደሚኖር አንዳንድ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይሄ ቁጥር ደግሞ በክልሉ ገዢዎች በኩል እንደ ስጋት እንደሚታይ ውስት አዋቂ ምንጮች ያወሳሉ፡፡ ከእዚህ ሕዝብ ውስጥ የተወሰነው ክፍል አሰቃቂና ዘግናኝ ግድያ ከተፈፀበት ሌላ አካባቢውን ሳይወድ በግዱ ለቅቆ ይሄዳል የሚል እርምጃም ይመስላል፡፡ እየሆነ ያለው ይሔው ነው፡፡ በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በግፍ በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል፣ ዞንና ወረዳዎች የሚኙ የኦሮሞ ገዢዎች ማን ኦነግ ሸኔ እንደሆነና እንዳልሆነ በግለሰብ ደረጃ ለይተው ያውቃሉ፡፡ እያንዳንዱ ዝርዝር መረጃም እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አማራ የጋራ ጠላታችን ነው ብለው ስለሚያስቡ በእጅ አዙር መግደልና ማፈናቀል ነው የሚፈልጉት፡፡ በአንድ ወቅት ጄኔራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ እኒህ ሰው ፡- ለኦነግ ሸኔ የመሳሪያም ሆነ የሎጀስቲክ አገልግሎት የሚያቀርብለት በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደሆነ የተናገሩትን በተለያዩ ሚዲያዎች አዳምጠናል፡፡ ታዲያ!! ተረኛዎቹ የእዚች አገር ገዢዎች ማንን ነው የሚያታልሉት!?? የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የኦህዴድ ብልፅግና ባለሥልጣናት በአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቃቸው መቼም ቢሆን የማይቀር ጉዳይ ነው።
በአሮሚያ ክልል በአማራ ተወላጅ ላይ የሚደርሰውን ጅምላ ግድያና ማሳደድ ማስቆም የመንግሥት ፍላጎት ቢሆን ኖሮኮ መፍትሔው ሩቅ አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው የመከላከያ ሰራዊት በየቀበሌው መመደብ የመንግስት አቅም ላይፈቅድ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ እዚህ የአማራ ተወላጅ ገበሬዎችን የሚያገለግል ሚሊሺያ ተመልምሎ ቢሰለጥንና ቢታጠቅኮ ይሄ ሁሉ ግፍና ስቃይ እይደርስበትም ነበር፡፡ በእርግጠኝነት የሚገደለው እብሪተኛ አካል ሲዘምትበት ተገቢውን የመከላከል ምላሽ የመሰጠት ወኔውም ሆነ ብቃቱ አለው፡፡ ነገር ግን የአማራ ተወላጅ ከኦሮሚያ እንዲለቅ ስለሚፈልግ እንደዚያ ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡
ይሄኮ አዲስና እንግዳ ርእሰ ጉዳይ አይደለም፡፡ህወሓት-ብአዴን በመጀመሪያ ጉበኤው ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ፡- “…. ከክልላችን ውጭ ያለውን አማራ አንወክልም፤ ከክልላችን ውጪ ያለው አማራ የብሔር ብሔረቦች ጠላት ነው፤ ነፍጠኛ ነው፤ መቀጣትም መወገዝም አለበት….” የሚል ነበር፡፡ በቃ! ዛሬም የብልፅናም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሚያራምደው አቋም ይኸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የአማራ ተወላጅ በኦሮሚያ ክልል እንዲር ቢፈለግ ኖሮ የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች አስፈላጊው ነገር ተሟልቶላቸው ወደ ነበሩት ቀዬ እንዲመለሱ ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን አጀንዳቸው የህወሓትን ተልእኮ ማስፈጸም በመሆኑ አያደርጉትም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህደም በህዝብ ለመመረጥ እንዳደረጉት ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ፡- ስለ እናቶች ለቅሶ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሉአላዊ አንድነት፣ ስለ ፍቅርና ዴሞክራሲ የሚያቀርቡት የማባበያ ዲስኩር ከማታለያነት ያለፈ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላጅ እናታችው የሚወዱ ቢሆን ኑሮ በወለጋ በተለያዩ አካባቢዎችኮ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶችና ህፃናት በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ሲታረዱ ከገፅታቸው የሀዘን ምልክት ይታይ ነበር፡፡ ችግሩንም ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ በወሰዱ ነበር፡፡ የሀዘን አዋጅ ታውጆ ባንዴራ ዝቅ የሚልበትና የህሊና ጸሎትም ይደረግ ነበር ባይ ነኝ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በፓርላማ ንግግራቸው “ሰው እየሞተ ችግኝ አትትከሉ የሚለን ሰው ሁሉ ለእኛ ጠላት ነውና አትስሙት፡፡ በመሆኑም ሰው እየተሞተ የሞተበት ቦታ ላይ ችግኝ እንተክላለን ለአስከሬኑ ጥላ እንዲሆነው…..” የሚል አይነት ድምዳሜ ያለው ንቀት ነው ያስተላለፉት፡፡ ነገሩ ሁሉ “አዞ እየዋጠ ያለቅሳል” እንደሚባለው አይነት ይመስላል፡፡
ለእኔ ከእዚህ ይበልጥ የሚገርመኝ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ የእምነት ተቋማት ይህንን በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀም ግፍና መከራ ማውገዝ፣ የማስታረቅ ሚና መጫወት፣ ለሞቱትም ፍታት፣ ጾምና ጸሎት ማድረግ እንዴት ያቅታቸዋል!!?? መንግሥታዊ ወገንተኝነት፣ ፍርሀት ወይስ ሌላ ምን ነገር ይኖር ይሆን! የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያለውን መግለጫ እንኳ ለማውጣት አልቻሉም፡፡ ተዓምር ነው፡፡
በዲሞክራሲ ስርአት የተከለከለ ሰላማዊ ተቃውሞ
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት “የለውጥ መንግሥት” ለምን እንደተባለ ባስበው ባስበው ባሰላስለው ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ህወሓት አምባ ገነን ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰላማዊ ተቋውሞ ማድረግ በድርጎ ተሰፍሮም ቢሆን ይፈቀድ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አያሌ የተቃውሞ ሰልፎችን በአንፃራዊ ነፃነት አካሂደዋል፡፡ ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲው የተቃውሞ የእሞቱምና እየታሰሩ ጩኸታቸውን ያሰሙበትም በርካታ ጊዜያት ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ የብልፅግና መንግስት ወደ ስልጣን የመጣው በፋኖ እና በቄሮዎች … በሌሎችም ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ነበር፡፡ እንዳጠቃላይ ሕወሓት የታቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ባይፈቅድና ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን በጭልፋም ቢሆን ባይከተል ኖሮ ብልፅግና መንግሥት ሆኖ የመምጣት እድሉ አልነበረውም፡፡
አምባገነት ሕወሓት በአንፃራዊነት ሲለካ ከብልፅግና የተሻለ ነበር ለማለት የሚያስችሉ ነገሮችም ነበሩት፡፡ እንደሚታወቀው በ1997ዓ/ም በተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ አብዛኛው ህዝብ፣ በቃንት፣ አንፈልጋችሁም፣ ወደ ክልላችሁ ሂዳልን!…. በማት ተቃውሞውን ያሰማ ነበር፡፡ የወታደሩ ክፍል እንኳ “ሂዱልን!” በማለት ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን አሳይቷል፡፡ ያኔ የሕወሓት ኦህኦዴግ እሳት የላሱ ካድሬዎችን ወደ ህዝቡ ዘልቀው ገብተው በየቀበሌው ስብሰባዎች በማዘጋጀት፡- “አጥፍተናል. ለወደፊቱ እንታረማል! አይደገመንም!…” እያሉ ህዝብን ይቅርታ እንደጠየቁ ሁሉም ሕዝብ ያወቀዋል፡፡
አሁን ግን እየሆነ ያለው ሁሉ አበው “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደሚሉት ሆኖአል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምላሽ የሚሰጠው በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ሆኖአል፡፡ በህትመትና ኤሌሄክትሮኒክስ ሚዲያ የሚሰሩ ሙያቸውንና አገራቸው የሚወዱ ጋዜጠኞችን፣ ተማሪዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ማፈን፣ ማሰር፣ የደረሱበት እንዳይታወቅ አድርጎ መሰወር የእለት ተእለት ተግባር ከሆነ ውሉ አድሮአል፡፡
መንግሥት ባለበት አገር የአማራ ተወላጅ የሆነ ሕዝብ፣ ባዶ እጁን ያለና ለጥቃት የተጋለጠ ሕዝብ ጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድበት ማስቆም ያልቻለ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ግድያ በአደጉት አገራት ከሚፈጸመው በቁጥር ያነሰ ነው እያለ ማላገጡ ዴሞክራሲያዊነት ማለት ነው!??
37ተኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት “Richard M. Nixon” የሥልጣን ዘመናቸውን ሳይጨርሱ በቅሌት የተሰናበቱትኮ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ንግግር በምስጢር አስቀድተዋል በሚል ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ 42ተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት “William J. Clinton” የአንዲት የሁዋይት ሀውስ ኮረዳ ጭን ዳብሰዋል በሚል ቅሌት ከሥልጣናቸው ለማውረድ ጠርዝ ላይ ከደረሱ በኋዋላ ነበር በህዝብ አስተያየት መትረፍ የቻሉት፡፡ እርሳቸውም ድርጊቱን በማመናቸው ቢያንስ የመረጣቸውን ህዝብ አልዋሹም ለሕዝባቸው ታማኝ ናቸው በሚልም ሞገስ ተችሮቸዋል፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን ጆርጅ ፍሮይድን ከዘጠኝ ደቂቃ በላይ አንገቱ ላይ ረግቶ በገደለው ፖሊስ ምክንያት መላው አለም ዛሬም ድረስ ተቃወሞወን እያሰማና እያሰበው ይገኛል፡፡ እዚህ እኛ አገር የሚረዳውን ደግሞ ለአንባብያን ህሊና መተው ይመረጣል፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ እናቶችና ሕፃናት በግፈኞች መገደላቸው ሳያሳዘናቸው ጭራሽ እኛ አገር የሚገደሉ በአደጉት አገራት ከሚገደሉት በቁጥር ያነሰ ነው ይላሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ህዝብ ግብርና ቀረጥ ከጉሮሮው ነጥቆ የሚከፍለውኮ መንግሥት የተባለው አካል የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት እንዲያስረክቡ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተጠናና የተቀናበረ እልቂት በአዲስ አበባ ለማድረስ ጠላቶቻችን አቅደው እንደነበረ ያረዱናል፤ ይህች ገድምዳሜ አገላለጽ ለምን በዚህ መልኩ እንደቀረበች አድማጭ አይገባውም ካሉ በእኔ እይታ የተሳሳቱ ይመስለኛል፡፡
ከሕዝብ ምን ይጠበቃል!!!
ውድ ወገኔ! ወደህም ሆነ ተገደህ ባለሥልጣናቱን ለመንግሥትነት የምታበቃው አንተ ነህ፣ የምትገደለውም የምትዘረፈውን አንተ ነህ፡፡ በትናንሽ የመሸንገያ ንግግሮችም ተሸንፈህ የልብህን ጉዋዳ ወለል አድርገህ ለጠላቶችህ የምትከፍትላቸውም አንተ ነህ፡፡ ለአንተ ህልውና የታገሉትን ሲታገሉም የተዋደቁትን በማግለል ውለታ በል ሆነሃል፡፡ በትከሻህ ሊገለገል ከመጣው መንግስት ወይም ቡድን ጋር ሁሉ ሊያርድህ ሊገድልህና ሊዘርፍህ ካደባው ቡድን ጋር ሁሉ ታሸረግዳለህ፤ ታብራለህ፡፡ ግን ለምን!??… አባቶቻችን “ጅልን እባብ ሁለቴ ይነድፈዋል- አንዴም ሳያይ አንዴም ሲያይ” ይሉ ነበር፡፡ አንተም እንደዚያ የሆንክ አይመስልህም!?? መፍትሔው ያለው ከአንተ ዘንድ ነው፡፡ ተነጣጥለህ ከምትጠቃ በአንድነትና በጋራ መከላከሉ አያዋጣም ብለህ ነው!??….
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግስት ሕዝብን ከጅምላ ግድያ ማዳን አልቻለም፡፡ በእዚህም ምክንያት በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል፣ አፈናና ግድያ ተገልጾ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ማቆሚያ ያለውም አይመስልም፡፡ የብልፅግና መንግሥት የምርጫ ዘመኑን ይጨርስ ቢባል ገና አራት ድፍን አመታት ይቀሩታል፡፡ አሁን የሚደርሰው ጥቃት በእዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ አራት አመታት እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ምድር አንድም የአማራ ተወላጅ የሚተርፍ ይመስላችኋል!?? እኔ ጥያቄ ነው ያቀረቡት፤ ምላሹ የእናንተ ነው፡፡
በእኔ የግል እይታና ድምዳሜ ግን እንኳንስ አራት አመታት አይደሉም ነገ ራሱ በጣም ይዘገያል ባይ ነኝ፡፡ ዛሬን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ትግሉ ይቀጥላል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ