ያለ መክሰስ መብታቸው የተነሳው ዶ/ር ሙሉቀን ሃብቱ ላይ፤ ፍርድ ቤት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ…!!!
በሃሚድ አወል
*… “በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ተጠርጥረው ነው
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው ባለፈው ሳምንት አርብ የተነሳው ዶ/ር ሙሉቀን ሃብቱ ላይ፤ ፍርድ ቤት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ከአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊነታቸው የተነሱት ዶ/ር ሙሉቀን፤ ባለፈው አርብ በፖሊስ ቁጥጥር ከዋሉ በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የቀድሞው የቢሮ ኃላፊ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 11 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት፤ “በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ተጠርጥረው ነው። ዶ/ር ሙሉቀንን ለእስር ያበቃቸው ከ10 ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወጣው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል የተባለው የማጭበርበር ወንጀል ነው።
ሐምሌ 1፤ 2014 በተካሄደው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሂደት ጥቅም ላይ የዋለው “ሲስተም” “ዓለም አቀፍ የመልማት ስታንዳርዱን ያልጠበቀ እና የሚና መደበላለቅ የታየበት” እንደነበር ለፍርድ ቤት ባቀረበው ሰነድ የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ፤ ዶ/ር ሙሉቀን ይህ “ሲስተም ስራ ላይ እንዲውል አድርገዋል” በሚል ወንጅሏቸዋል። ተጠርጣሪው “ ‘ቴክኖሎጂው በኢንፎርሜሽን መረብ እና ደህንነት አገልግሎት (INSA) ተፈትሾ ችግር እንደሌለበት ማረጋገጫ የተሰጠበት ነው’ ብለው የከተማ አስተዳደሩን አሳስተዋል” የሚል ውንጀላም ቀርቦባቸዋል።
ዶ/ር ሙሉቀንን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የፌደራል ፖሊስ፤ ተጠርጣሪው ከቴክኖሎጂ ልማቱ ጀምሮ እስከ ዕጣ አወጣጡ ድረስ የመከታተል ኃላፊነት ነበረባቸው ሲል በሰነዱ አመልክቷል። ሆኖም ተጠርጣሪው “የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፤ ህዝብ እና መንግስትን በማጭበርበር፤ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ እና በተቀናጀ መልኩ ድርጊቱ እንዲፈጸም አድርገዋል” ሲል ፖሊስ ወንጅሏቸዋል።
መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ሰኞ ረፋድ በነበረው የችሎት ውሎ “ከወንጀሉ ጋር ተያያዥ ጉዳዮችን ለመስራት እና ምርመራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ለማረጋገጥ” የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ችሎትን ጠይቋል። የተጠረጠሩበትን ጉዳይ እና የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ በችሎት ተገኝተው የተከታተሉት ዶ/ር ሙሉቀን፤ በዳኞች የመናገር ዕድል ተሰጥቷቸዋል።
ተጠርጣሪው ረዘም ያለ ደቂቃ በወሰደው ንግግራቸው፤ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሂደት የተከሰተው ችግር እርሳቸውን የማይመለከት እና ሊያስጠይቃቸውም እንደማይገባ ማሳያዎች በመጥቀስ ለማስረዳት ሞክረዋል። የቀድሞው የቢሮ ኃላፊ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞበታል የተባለው ሶፍትዌር “መልማት ከጀመረ በኋላ” ወደ ስራ መምጣታቸውን ለችሎቱ ተናግረዋል።
እርሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በመልማት ላይ የነበረውን ቴክኖሎጂ በተመለከተም፤ ለሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲሁም ለኢንሳ ደብዳቤ መጻፈቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በታህሳስ ወር ካገኙት “ምክረ ሀሳብ” ውጭ ከኢንሳ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል። “ቴክኖሎጂው በኢንሳ የተረጋገጠ ነው” ብለዋል በሚል በመርማሪ ፖሊስ የቀረበባቸውን ውንጀላም አስተባብለዋል።
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣው ከወጣ በኋላ በተደረገው ኦዲት ላይ አለመሳተፋቸውን ያነሱት ዶ/ር ሙሉቀን፤ ተከሰተ የተባለው ችግር በሌላ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል። ዶ/ር ሙሉቀን “እኛን ከብሔራችን ጋር በማያያዝ ለመወንጀል ነው የታሰበው” ሲሉ ከእርሳቸው እስር ጀርባ “ሌላ የተዘጋጀ ነገር” አለ የሚል ግምት እንዳላቸው ለችሎቱ አስረድተዋል።
ዶ/ር ሙሉቀንን ወክለው በችሎቱ የተገኙት ሁለት ጠበቆች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያከብርላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ አድያምሰገድ አጥናፉ የተባሉት ጠበቃ፤ ፖሊስ ያቀረበው የምርመራ ጊዜ “የህግ መሰረት የለውም” ሲሉ ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቀዋል። “ተጠርጣሪው በዋስትና ቢወጡ በማስረጃ አሰባሰብ ላይ ምን አይነት እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚለው አልቀረበም” ያሉት ጠበቃው፤ በዚህም ምክንያት ደንበኛቸው በእስር ሊቆዩ እንደማይገባ ተከራክረዋል።
ሌላኛው ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ በበኩላቸው “ተጠርጣሪው፤ ተጠርጣሪ ለመሆን ብቁ የሚያደርጋቸው ምክንያት አልተጠቀሰም” ብለዋል። አቶ ሞላልኝ ፖሊስ ያቀረበው የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ “በአሳማኝ ምክንያት ተደግፎ የቀረበ ስላልሆነ” ውድቅ ተደርጎ ደንበኛቸው በዋስትና እንዲወጡ ችሎቱን ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ ለጠበቆች መከራከሪያ በሰጠው ምላሽ፤ ተጠርጣሪው “ከሲስተሙ ፈጠራ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ ለተሰራው አሻጥር የእሳቸው እጅ አለበት” ብሏል። “ተጠርጣሪው ማስረጃ ለማጥፋት አቅም አላቸው” ሲልም የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል። ፖሊስ “ምርመራው ጅምር ስለሆነ፤ መስመር እስከምንይዝ ድረስ የዋስትና መብታቸው ተገድቦ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልን” ሲልም ችሎቱ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድላቸው ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ “ምርመራው ጅምር በመሆኑ እና የሰው እና ሰነድ ማስረጃ ማሰባሰብ ስለሚያስፈልግ” በሚል የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል። መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የፈቀደው ችሎቱ፤ ሐምሌ 25 በሚኖረው ቀጠሮ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ከአስር ወራት በፊት የአዳነች አቤቤን ካቢኔ ከመቀላቀላቸው በፊት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈጻሚ ነበሩ። በሰላም እና ደህንነት የሁለተኛ እና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ዶ/ር ሙሉቀን፤ ከዚህ ቀደም በመከላከያ ሚኒስቴር እና በቀድሞው የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአሁኑ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)