>

በክብረወሰን የታጀበ ታሪክ ቀያሪ የማራቶን ድል!! (ቦጋለ አበበ)

በክብረወሰን የታጀበ ታሪክ ቀያሪ የማራቶን ድል!!

ቦጋለ አበበ

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ውድድሮች አውራ በሆነው ማራቶን በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ በሁለቱም ጾታ ድል በማድረግ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት።

ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ የወንዶች ማራቶን የአፍሪካውያን የድል ፋና ወጊ ነው። በሴቶች ደግሞ ታሪካዊቷ ፋጡማ ሮባ ፈርቀዳጅ ናት።

እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሊምፒክ የማራቶን ውድድሮች በሁለቱም ጾታ ደጋግመው ወርቅ ያጠለቁበት ታሪክ አላቸው።

ወደ አለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ስንመጣ ግን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማራቶን ድል በተለይም በሴቶች ከኦሊምፒክ አኳያ ደብዛዛ ነው።

በእርግጥ የወንድ አትሌቶችም ውጤት ያለፈውና የዘንድሮው ቻምፒዮና ድሎች ታሪክ መቀየር ቻሉ እንጂ ተመሳሳይ ነበሩ።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በየዘመኑ በማራቶን የግል ውድድሮች ስኬታማ መሆን ቢችሉም በአለም ቻምፒዮና መድረክ ግን ነጥረው መውጣት እንዳልቻሉ ያለፉት ውድድሮች ውጤታቸው ማሳያ ነው።

በዚህ መድረክ የኢትዮጵያ ብቸኛውና የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ እኤአ በ2015 የቤጂንግ የአለም ቻምፒዮና በማሬ ዲባባ የተመዘገበው ነው። ከዚህ ውጪ ሊጠቀስ የሚችለው ብቸኛ ሜዳሊያ እኤአ በ2009 የበርሊን ቻምፒዮና አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው ነሐስ ነው።

እነዚህ ሁለት ሜዳሊያዎች ብቻ ኢትዮጵያን ከአለም ስድስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠዋት ቆይተዋል። በአንጻሩ ኬንያ በ4ወርቅ፣ 4ብር እና 1 ነሐስ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች።

ጃፓን በ2 ወርቅ፣ 5 ብርና 4 ነሐስ ተከታዩን ደረጃ ስትይዝ፣ ፖርቹጋል 2 ወርቅና 2 ብር በታሪኳ አስመዝግባ ትከተላለች። ሮማኒያ 1ወርቅ፣ 1ብርና 3 ነሐስ ያላት አገር ስትሆን ቻይና በ1 ወርቅና 1 ብር ከኢትዮጵያ በላይ የሚቀመጡ አገራት ነበሩ።

ዛሬ በኦሪገን እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ቻምፒዮና ይህን ታሪክ የቀየረ ድል በወጣቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጎይተቶም ገብረስላሴ ተመዝግቧል፡፡

ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ በኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች የታክቲክ ጦርነት ልብ አንጠልጣይ በሆነ ፉክክር የታጀበው የሴቶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ የማታ ማታ ማረፊያውን ኢትዮጵያ አድርጓል፡፡

አትሌት ጎይተቶም በውድድሩ ታሪክ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ስታዝመዘግብ በእንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ ለዓመታት የቆየው የቻምፒዮናው ክብረወሰን 2፡18፡11 በሆነ ሰዓት ተሰብሯል፡፡

ትናንትም በተመሳሳይ በወንዶች ማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ ለኢትዮጵያ ወርቅ ሲያስመዘግብ የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ድሉ እጥፍ ድርብ ሆኗል፡፡

በአንድ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ የማራቶን ወርቆችን ስታስመዘግብም በታሪክ የመጀመሪያ ሆኗል፡፡

ጎይተቶም ምንም እንኳን በውድድሩ መሃል ህመም ተሰምቷት የነበረ ቢሆንም በታላቅ ፅናት እስከ መጨረሻ ለመጓዝ አላመነታችም፡፡ ይህም እኤአ በ2007 የኦሳካ የዓለም ቻምፒዮና ጥሩነሽ ዲባባ ሆዷን ይዛ ለወርቅ እንደበቃችው ሁሉ ጎይተቶምም ተመሳሳይ ታሪክ ደግማለች፡፡

ውድድሩ 8ኪሎ ሜትር እስኪቀረው ድረስ የነሐስ ሜዳሊ ለማጥለቅ የተፋለመችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አባብል የሻነህ ስኬታማ ሊባል የሚችል የቡድን ስራ ብትሰራም በህመም አቋርጣ ለመውጣት ተገዳለች፡፡

በዚህም በታክቲክ ጦርነቱ ከአርባ ኪሎ ሜትር በኋላ በጎይተቶም የበላይነት የተወሰደባት ኬንያዊቷ ጁዲዝ ኮሪር 2፡18፡20 በመግባት የብር ሜዳሊያውን ወስዳለች፡፡

በፅናትና ተስፋ አለመቁረጥ ከአባብል እጅግ ርቃ የነበረችው ትውልደ ኬንያዊት የእስራዔል አትሌት በመጨረሻም በ2፡20፡18 የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡

Filed in: Amharic