ህወሓት ተደራዳሪዎችን መሰየሙን ቃል አቀባዩ ገለፁ!!
መሀመድ አህመድ
የትግራይ አማፂያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደራደር ቡድን መሰየማቸውን የህወሓት ቃል አቀባይን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዛሬ ዘግቧል።
ይህ የተሰማው የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ስለሚደረገው ድርድር እንዲያጠና የሰየመው ቡድን የመጀመሪያ ስብሰባውን ባደረገ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑን ኤኤፍፒ ጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ የሚደረጉ ድርድሮች በሙሉ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ብቻ እንዲሆን በአፅንዖት መግለፁን ህወሓት ማጣጣሉ ለድርድሩ ሂደት እንደ ፈተና እንደሚታይ ዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት “ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅርበት አላቸው” ሲል ሥጋቱን የገለፀው ህወሓት ንግግሩ በኬንያ አስተናጋጅነትና በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት ቢካሄድ እንደሚመርጥ ማሳወቁን በዘገባው ተገልጿል።
የህወሓት ቃል አቃባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያሉበትን ተደራዳሪ ቡድን ወደ ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ እንሆናለን” ሲሉ የነገሩት መሆኑንም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
አቶ ጌታቸው አክለውም “ሁሉንም የድርድር ሂደቶች ለአፍሪካ ኅብረት ማቅረቡ ለኛ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ነገር ይሆንብናል” ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሶ “ንግግሩ በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ተሣትፎ ያላቸውን ኬንያታን ማሳተፍ ይኖርበታል” ሲሉ አክለው መናገራቸውን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰየመው ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ መሆኑ ተዘግቧል።